ወጣቱ አለመግባባቱን በራሱ የፈታበት ሒደት

0
1889

የሠላምና ልማት ማዕከል ለትርፍ ያልተቋቋም፣ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሌላ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በአገሪቱ የሠላም ባህል እንዲስፋፋ፣ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ማሕበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከተመሰረተበት 1982 ዓ/ም አነስቶ በተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ግጭትን ለመፍታት እና የሠላም ባህልን ለመገንባት የሚያስችሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማዳበር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በቦታ እና በሁኔታ አለመመቸት ምክንያት ለብዙ ተቋማት ለመድረስ አመቺ አይደሉም የሚባሉ የአገራችን አካባቢዎች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከታችኛው የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳ እንደአገር ያለብን ችግር ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም የአቅሙን በማበርከት ላይ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ተቋሙም አሁን ያሉ ፕሮጅክቶችን በማስፋት እና ወደተጨማሪ ቦታዎች በመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማሕረሰብ አቀፍ የሆኑ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ እንዲሁም አቅማቸውን ጭምር በመገንባት ለችግሮች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የሚቀጥል ይሆናል።
ሠላምና ልማት ማዕከል

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ ግጭቶች በየዘመኑ ተስተውለዋል። እነዚህ ግጭቶች ሥር እንዳይሰዱና ወደትውልድ እንዳይተላለፉ ሽማግሌዎችና ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ትልቅ ሚና ሲጫወቱ ኖረዋል። ምንም እንኳ አነኚህ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች አሁንም ድረስ ውጤታማ ሆነው የቀጠሉ ቢሆንም፣ ዘመኑን የዋጀ እና በወጣቱም ዘንድ ተቀባይት ያላቸው የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ጎን ለጎን መጠቀም የተሻለ ውጤታማ እንደሚያደርግ እሙን ነው። በተለይም ደግሞ በግጭቶች ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑ ወጣቶች እርስ በራሳቸው በመወያየት በመካከላቸው የነበረን አለመግባባት አስወግደው እንዲቀራረቡ በማድረግ ሒደት ውስጥ የሠላም እና ልማት ማዕከል ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ማዕከሉ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች ባለሙያዎችን በአካል በመላክ እና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ አጋር አካላት ጋር በመተባበር፣ አለመግባባት የፈጠሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እርስ በርሳቸው ተቀራርበው ችግራቸውን እንዲፈቱ ዕድል በማመቻቸት ውጤታማ ሥራ ሲሠራ እንደቆየ ይነገርለታል።

ማዕከሉ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል በቡራዩና አዲስ አበባ ወጣቶች መካከል ተከስቶ የነበረውን አለመግባባት የሚያረግብና በግጭቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶችን አቀራርቦ የሚያወያይበት የማቀራረቢያ መድረክ አንዱ ነው። የቡራዩ እና የአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወጣት ተወካዮች ከ5 ዙር በላይ የሆነ ውይይት በማካሄድ ወጣቶቹ ችግራቸውን ፈተው ለመቀራረብ የሚችሉበትን ዕድል ሞክሯል። ማዕከሉ ባዘጋጃቸው መድረኮች ላይ የተወሰኑ ወጣቶችን ለየብቻቸው እንዲወያዩ ከተደረገ በኋላ፣ አንድ ላይ ተቀላቅለው በያዟቸው ሐሳቦች ላይ እንዲወያዩ በማድረግ፣ የማቀራረብ ሥራን ተሳታፊዎችን በማቀያየረ ሲያከናውን ቆይቷል።

በውይይቱ ላይ ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል የቡራዩ ወጣቶችን ወክሎ የተገኘው ገረመው ታፈሰ አንዱ ነው። ከሐሮማያ ዩኒቨርስቲ በኮምፒውተር ሳይንስ ተመርቆ ላለፉት ኹለት አመታት ሥራ ሲያፈላልግ የቆየው ይህ ወጣት፣ ከውይይቱ በፊት በወጣቱ ዘንድ የነበረው ድባብ ጥሩ እንዳልነበር ያስታውሳል። በአዲስ አበባና ቡራዩ ወጣቶች መካከል የነበሩ ክፍተቶችና አለመግባባቶችን ለመፍታት በማዕከሉ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ ትልቅ ጠቀሜታ እንደነበረው ይናገራል።

ወደ ውይይቱ እንዲገባ ሐሳቡ ሲቀርብለት ውጤታማ ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው ገረመው፣ እንደጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ ያልገመተውን ውጤት እንዳገኘበት ይመሰክራል። መጀመሪያ የቡራዩ ልጆች እንዲወያዩ ሲጠራ እንደተለመደው ስለከተማዋ ሠላም መስሎት እንደነበር ያስታውሳል። በውይይቱ ላይ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር ውይይት ሊደረግ እንደታሰበ ሲነገር፣ አንዳንዶች እንዴት ይሆናል ብለው አጉረምርመው እንደነበር ይናገራል። “ከእነሱ ጋር እንዴት እንቀመጣለን? አብረንስ እንዴት እንሰራለን?” ሲሉ የነበሩት በኋላ ላይ ሁኔታውን ሲያዩት ራሳቸው ግንባር ቀደም ሆነው ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር ብሏል። ይህ የሆነው ያነሱት የነበረውን ሐሳብ በሐሳብ ማሸነፍ ስለተቻለ ነው ይላል።

በመጀመሪያው ሒደት የማንስማማበት ምክንያት ምንድን ነው? ብለን ለየብቻ ተወያይተንና ተከራክረን ስለነበር በኋላ ላይ የተነሱትን ሐሳቦች በሐሳብ ለመርታት በቅተናል የሚለው ገረመው፣ መድረኩ አያስፈልግም ይሉ የነበሩት ጭምር በኋላ ላይ ጥቅሙን እንደተረዱት መናገራቸውን ያወሳል። ትክክለኛ በጎ ሐሳቦች ተለይተው በሚቀጥለው የጋራ ውይይት መድረክ የቀረቡ ሲሆን፣ ተቀላቅለው ባደረጉት ውይይት የመጣ ጥሩ ውጤት መኖሩን የቡራዩው ወጣት ይናገራል።

ገና ከውይይቱ መነሻ ጀምሮ የአመለካከት ለውጥ ሲመጣ ይታይ ነበር የሚለው ገረመው፣ በተለይ እየተዋወቅን ስንሄድ የበለጠ እየተግባባን ለመቀራረብ በቅተናል ይላል። የሠላምና ልማት ማዕከል ዕድሉን በማመቻቸት እኛው አስተባባሪ መርጠን ራሳችን እየመራን ተወያይተናል የሚለው ይህ ወጣት፣ በቅድሚያ ከተዋወቅን በኋላ የሚያግባባን ጨዋታ የመሰለ አስተማሪ መርሃ-ግብር ነበር የተዘጋጀው ብሏል። ከተቀራረብን በኋላ እርስ በርስ ተወያይተን መቀራረብ ችለናል ሲል ሒደቱን ያብራራል።

ከተፈጥሮ አቀማመጥና ልዩነት ይልቅ ሰው በመሆን እንድናምን ውይይቱ አስችሎናል የሚለው ተሳታፊው፣ የወጣቶቹ መቀራረብ ስለሠላም፣ አብሮ ስለመኖርና ስለ ሰብዓዊነት ለማወቅ ውይይቶቹ ማገዛቸውን ተናግሯል። ሠላምና መረጋጋት ወጣቱ ውስጡ ከሌለ ወደ ሌላ ሊያስተላልፈው ስለማይቻለው፣ በመጀመሪያ የራስን አመለካከት መቀየር እንደሚያስፈልግ ተሳታፊው የተረዳበት ሒደት ነበር።

በውይይቶቹ ወቅት ወጣቶቹ በአብዛኛው የማይግባቡባቸው ጉዳዮች ላይ መስማማት ቢችሉም፣ በሐሳብ የተለያዩባቸው ጉዳዮች እንደነበሩ ገረመው አልሸሸገም። አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ ሆነን ነገሮችን እንድንመለከት ስለተደረገ፣ ልዩነቱ የተፈጠረው ነገሮችን ካለመረዳት፣ እንዲሁም ውስጣችን ከነበረ የአመለካካት ችግር መነሻነት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ሲል ያስተዋለውንም ይናገራል።

ሰው ሰው ነው በሚል አመለካከቱን ኹሉም እንዲያስተካክል ውይይቱ ስለረዳ መቀጠል አለበት የሚለው ገረመው፣ አሁን የሚሠራው ጥሩ ቢሆንም በቂ አይደለም ይላል። ከተሳታፊዎቹ ቁጥር አነስተኛነት አኳያ፣ እንዲሁም ከችግሩ ስፋት አንጻር የሠላምና ልማት ማዕከል ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀትል ጥሪውን ያቀርባል። በውይይቱ ያገኘውን ዕውቀት በየትኛውም አጋጣሚ ለሌሎች ዕድሉን ላላገኙ እንደሚያካፍል የሚናገረው ይህ ወጣት፣ ስለአዲስ አበባ ወጣቶችም ሆነ በአጠቃላይ ስለሰው ልጆች ያለው አመለካከት እንዲቀየር በመደረጉ፣ ሰው በሰውነቱ እንዲከበር እኔም የበኩሌን ኃላፊነት እንድወጣ አስችሎኛል ይላል።

ሰው በቀላሉ ሊቀየር ባይችልም ጥረቴን አላቋርጥም የሚለው ገረመው፣ በፖለቲካም ሆነ በትንሽ የመንደር አስተሳሰብ ሰው መለያየት እንደሌለበት መረዳቱን ይናገራል።

የሠላምና ልማት ማዕከል ወጣቱ ችግሩን በራሱ መፍታት አለበት ብሎ ይህን ያህል ጥረት ማድረጉ ሊያስመሰግነው ይገባል ያለን ሲሆን፣ ሥራው ከጥሩም በላይ ስለሆነ መበረታታትና መደገፍ አለበት ባይ ነው። አሁን የተሠራው እንደጅማሮ ነው የሚለው ገረመው፣ በአቅም ዕጥረት ምክንያት ተደራሽነቱ ሠፊ ባለመሆኑ በሌሎች እየታገዘ አድማሱን እንዲያሰፋ ቢደረግና ሥራውም ወደሌሎች ቢስፋፋ መልካም እንደሚሆን ይጠቁማል።

በሌላ በኩል፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ወክሎ በውይይቱ ላይ የተገኘው ሰባሃዲን ከድር ይባላል። ይህ የ26 ዓመት ወጣት ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ከተመረቀና ሥራ መፈለግ ከጀመረ 9 ወራት ሆነውታል። የተወለደው ወለጋ ነቀምት እንደሆነ የሚናገረው ይህ ወጣት በልጅነቱ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣው።

በአዲስ አበባና በቡራዩ ወጣቶች ዘንድ እርስ በርስ ጥላቻ ነበር የሚለው ይህ የውይይቱ ተሳታፊ፣ ወጣቶች እንዲቀራረቡ ቢፈልግም በግሉ የነበረውን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ ሳይችል ቆይቷል። አለመግባባቶች ቀጥለው ችግር እንዳያስከትሉ የነበረውን ሥጋት የሚቀርፍ ውይይት መዘጋጀቱን በአንድ ወዳጁ በኩል ሲሰማ ደስተኛ እንደነበር ይናገራል። እንደሌላው ጭፍን የሆነ ጥላቻ አልነበረኝም የሚለው ሰባሃዲን፣ በመካከል የነበረውን አለመግባባት የሚፈታ ሥልጠና እንጂ የወጣቶች የእርስ በርስ ውይይት አልመሰለኝም ነበር ይላል።

በመንግሥት የሚዘጋጁ የተለመዱ ወጣት ላይ ያተኮሩ የማንናገርባቸው ሥልጠናዎች መስለውኝ ነበር ያለው ይህ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወጣት፣ ውይይት መሆኑና እራሳችን የምንመራው የእርስ በርስ መቀራረቢያ መድረክ መሆኑን ሳውቅ በጣም ደስተኛ ነበርኩ ሲል አጀማመሩን ይገልጻል። የአዲስ አበባ ወጣቶች እንደቡራዩ ወጣቶች ሁሉ በመጀመሪያው ቀን ለብቻቸው ተገናኝተው ልዩነቱን የፈጠረው ችግር ምንድን ነው በሚል ተወያይተዋል።

በቀጣይ የኹለቱ አካባቢ ወጣቶች ተቀላቅለው የተካሄደው ውይይት በጣም ውጤታማ ነበር የሚለው ይህ ወጣት፣ ወንድማማች እንደሆንን እንድንረዳ ማዕከሉ ያዘጋጀው ውይይት አስፈላጊ ነበር ብሏል። የነበረው ጨዋታ እንድንቀራረብ በማድረጉ ልንናገር ያሰብነውንና ይዘን የመጣነውን ሐሳብ ጭምር እንድንረሳ ያደረገ ነበር ሲል ሒደቱን ያብራራል።

ጭፍን ጥላቻ ብዙዎች ላይ ነበር የሚለው ሳባሃዲን፣ አንዱ የሌላውን ወገን ሐሳብ ሲሰማ የነበረውን አመለካከት ያለ ችግር እንዲቀይር ለማድረግ ረድቷል ሲል ያስረዳል። ያለያየን የነበረው ፖለቲካው ወይም ሌላ ጉዳይ እንጂ እኛ እንዳልነበርን ለማመን ችለናል የሚለው ይህ የአዲስ አበባ ወጣት፣ ያለያዩን የነበሩ ሐሳቦች በሙሉ በእኛ አቅም ሊፈቱ የማይችሉ እንደሆኑ ተገንዝበን ሊያጣሉን እንደማይገባ መስማማት ችለናል ብሏል።

በመካከላችን ያለው ወሠን ሰው ሰራሽ እንደመሆኑ ሊለየን አይገባም የሚለው ይህ የውይይቱ ተሳታፊ፣ የሚያራርቀንን ጉዳይ ትተን የሚያቀራርበን ላይ እንድናተኩር በሠላምና ልማት ማዕከል የተሰናዳው ፕሮግራም ጠቅሞናል ሲል ይናገራል። ከብሔር በላይ ወንድማማችነት ይበልጣል የሚለው ሰባሃዲን፣ መወያየትና መነጋገር መፍትሔ እንደሚያመጣ የተረዳንበት ሒደት ነበር ብሏል።

ማዕከሉ የኹለቱን አካባቢ ወጣቶች ለማቀራረብ የተጠቀመበት መንገድ ጥሩ ነበር የተባለ ሲሆን፣ መቦዳደን ሰው ሰራሽ መሆኑን እንዲረዱ ከማድረጉ በላይ፣ ጊዜያዊ ክፍፍሎች ለፖለቲከኞች ጥቅም ሲባሉ የሚፈጠሩ በመሆናቸው ቅድሚያ ራሳቸው ያላቸውን አመለካከት መቀየር እንደሚገባ የተረዱበት እንደነበር ተሳታፊዎቹ ይናገራሉ። ውይይቱ ብዙዎችን በማሳተፍ ለወደፊትም በስፋት መቀጠል አለበት የተባለ ሲሆን፣ ዩኒቨርስቲዎችና ወጣቶች ላይ በይበልጥ ትኩረት ተደርጎ ቢሠራ መልካም ውጤት እንደሚገኝ ወጣቶቹ ይጠቁማሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here