አስገዳጅ የኮቪድ-19 ክትባት ሕጎችና ውጤታቸው

0
811

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ባለሥልጣናት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አሁንም በጣም አስጊ ነው ሲሉ ወቅታዊ መረጃን ይፋ አድርገዋል። በተለያዩ አገራት ክልከላዎችና ቁጥጥሮች እየላሉ መምጣታቸውን ተከትሎ ተቋሙ ያፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፣ በመላው ዓለም ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር፣ በቫይረሱ የሚያዙትም ሆኑ የሚሞቱት ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም፣ አስጊነቱ ግን ቀንሷል ማለት አይቻልም። በዐስር አገራት ከባለፈው ሳምንት ይልቅ አሁን ሥርጭቱ እያሻቀበ ነው የሚለው ድርጅቱ፣ አገራት ከመዘናጋት ይልቅ ጥንቃቄውን ቢያጠናክሩ መልካም እንደሚሆን ተናግሯል።

እንደተቋሙ ባለሥልጣናት ከሆነ፣ የተለያዩ አገራት አውጀውት የነበረን ሕግ በማላላታቸው፣ እንዲሁም ሕብረተሰቡ አስፈላጊ የተባለን ጥንቃቄ ለመውሰድ በመሠላቸቱ የሥርጭት መጠኑ አሁንም አሳሳቢ እንደሆነ ነው። በመንግሥት ባላሥልጣናት የሚታዩ መዘናጋቶችም እንዳሉ የጠቆመው ድርጅቱ፣ ሕብረተሰቡ አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን እንዳያደርግ የሚያግዱ የመመሪያ መላላቶች ተጨማሪ ዕክል እየፈጠሩ ነው ብሏል። በተለይ ክትባትን በተመለከተ አገራት የተለያየ ሕግ ስላላቸው መከላከያው ውጤታማ ሊሆን እንዳልቻለ ተጠቁሟል።

አስገዳጅ ሕጎች እየላሉ በመጡባቸው የአውሮፓና የመካከለኛው እስያ አገሮች ወረርሽኙ በመቀነስ ፈንታ እንደአዲስ እያገረሸ መሆኑ ተነግሯል። ይህ በተወሰኑ አገራት ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም እንደአጠቃላይ በተወሰደ መረጃ የተረጋገጠ እንደሆነ ተገልጿል። ለዚህ መንስዔ የሆነው ከጅማሮው አንስቶ ተደንግገው የነበሩ ሕጎችን ሕብረተሰቡ ተግባራዊ ማድረግ በማቆሙ ነው ተብሏል።

በ22 አገሮች መረጃ ላይ ተመርኩዞ በተደረገ ጥናት፣ በአገራቱ ለናሙና ጥናቱ ጥያቄ ከቀረበላቸው ግለሰቦች 66 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ማስክን በመደበኛነት ይጠቀማሉ። እጅ መታጠብን በተመለከተ፣ 78 በመቶ የሕብረተሰቡ ክፍል ብቻ ነው እጁን በአግባቡ የሚታጠበው። ኹለት ሜትር ርቀታችሁን ጠብቁ የሚለውን ትዕዛዝ ደግሞ ግማሽ በግማሹ ይዘነጉታል። ይህን ዓይነት የጥንቃቄ መመሪያ ከሚተላለፉ ግለሰቦች አብዛኞቹ ረስተውት ሳይሆን ሆን ብለው ጥንቃቄውን እንደማያደርጉ ተናግረዋል። በዚህ መንገድ ወረርሽኙን ማስቆም አይቻልም እያለ የሚወተውተው የዓለም ጤና ድርጅት፣ ክትባቱ ላይ ያለ ጥርጣሬም ተወግዶ ሕብረተሰቡ መከተብ እንዲኖርበት መንግሥታት ጥረት እንዲያደርጉ ይጠይቃል።

ከዓለም አጠቃላይ ሕዝብ 40 በመቶው በኹለት ወር ውስጥ መከተብ አለበት ብሎ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ተቋሙ፣ ጥቂት አገሮች ብቻ የተቀመጠውን ትልም ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ ነው ብሏል። የተቀሩት በጣም አነስተኛ ዜጎቻቸውን ብቻ የከተቡ አገራት የበለጠ ስኬታማ እንዲሆኑ እንደሚያግዝም አሳውቋል።

የኮቪድ ክትባት በተፈለገው መጠን እንዳይሰጥ እንቅፋት ከሆኑ ምክንያቶች የተወሰኑት ተጠቅሰዋል። አቅም ማነስ፣ ግጭት፣ ሰላም አለመኖር፣ የጤናው መስክ አለመዳበሩ፣ ለክትባቱ ያለ የተዛባ አመለካከት የተወሰኑት ሲሆኑ፣ መንግሥታት ሕብረተሰቡ ዘንድ ያለውን አመኔታ ከፍ ለማድረግ የበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቁሟል። ስለክትባቶቹ የሚነገሩ ማናቸውንም አደናጋሪ መረጃዎች በመመርመር ሕብረተሰቡ ትክክለኛው መረጃ እንዲኖረው በማድረግ፣ እንዲሁም በቀጥታ በማስተማር ከባለሥልጣናት ጋርም አብሮ በመሥራት ያለውን ተቀባይነት ለመጨመር መታሰቡን አሳውቋል።

የኮቪድ ክትባትን እያገኙ ካሉ ሕዝቦች አፍሪካውያን ዝቅተኛውን ቁጥር ይይዛሉ። አውሮፓውያንን በመሳሰሉ ሀብታም አገሮች እስከ 80 በመቶ የሚደርሱ ዜጎቻቸውን የከተቡ አገራት አሉ። በተቃራኒው ከሠሀራ በታች ያሉ አገራች ግፋ ቢል አምስት በመቶ ዜጎቻቸውን ብቻ ነው ማስከተብ የቻሉት። ‹ሜል ኤንድ ጋርዲያን› ላይ በወጣ መረጃ መሠረት፣ በአቅም ማነስ ምክንያት መከተብ እየፈለጉ ያልቻሉ አፍሪካውን በርካታ ናቸው። ወረርሽኑ ከመከሰቱ በፊት ከነበሩበት ድህነት እጅግ በጣም ወደታች የወረዱ አዲስ 70 ሚሊዮን ድሀ አፍሪካውያንን ወደነበሩበት ለመመለስ እንኳን ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ወረርሽኙ ባስከተለው መዘዝ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ወደ አቋረጡት የትምህርት ገበታቸው አይመለሱም። ከ550 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል ጥቂት የማይባሉ ኑሯቸውን ለመደጎም ወደማይመለሱበት የጉልበት ሥራም ሆነ ወደትዳር ዓለም ገብተዋል።

ወረርሽኙ ያስከተለውን የኢኮኖሚ መናጋት ለማረጋጋት፣ ዓለምም ወደነበረችበት ሒደት በቶሎ እንድትመለስ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF) ከዚህ ቀደም አድርጎት የማያውቀውን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ (650 ቢሊዮን ዶላር) መመደቡ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ከገንዘቡ ተጠቃሚ የሆኑት ድሀ አገሮች ሳይሆኑ ሀብታሞቹ ናቸው። አፍሪካ ከተመደበው 4 በመቶው ብቻ የደረሳት ሲሆን፣ ከሕዝብ ቁጥሯ አንጻር በጣም ዝቅተኛ ነው። አንድ አፍሪካዊ ከሚደርሰው 21 ዶላር መጠን ሲነጻጸር፣ የሀብታም አገር ዜጋ በ17 ዕጥፍ የበለጠ 364 ዶላር ድጎማን ያገኛል። ይህን የመሳሰለ ልዩነት አሁንም በመቀጠሉ ክትባትን የመሳሰሉ ወረርሽኑን ለመቀነስ የሚያግዙ ቁሳቁሶችን ለማዳረስ አዳጋች እንደሆነ ይነገራል። በየዓመቱ አንድ ነጥብ 2 ትሪሊዮን ገንዘብ እያስወጣ ያለውን የኮቪድ ወረርሽኝ በጋራ ርብርብ ማስቀረት ካልተቻለ የተወሰኑ ቦታዎች ብቻ ማተኮሩ ውጤታማ እንደማያደርግ ይታወቃል። በዘመቻ መልክ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልና፣ ዜጎቻቸውን አስከትበው የጨረሱ አገራት ወደ ድሀ አገሮች ትኩረታቸው እንዲያዞሩ ቢደረግ ይመከራል።

ሀብታም አገሮች ዜጎቻቸው እንዲከተቡ ከማሳመን አልፈው ለማስገደድም እየሞከሩ እንደሆነ ይሰማል። አውሮፕላን አትሳፈሩም፤ አገልግሎት መስጫ ተቋሞች ውስጥ አትስተናገዱም፤ ከሥራም ትባረራላችሁ፤ በሚል የተለያዩ ሕጎችን ቢያወጡም ያን ያህል ውጤታማ እንዳልሆኑ ይሰማል። አንዳንድ አገሮች ሕዝባቸው ሐሳቡን ተቀብሎ ብዙኃኑን መከተብ ቢችሉም፣ በአንዳንድ አገሮች ደግሞ የተገላቢጦሽ ሆኖ ተቸግረዋል። ሠራተኞች፣ “መብታችን ተጣሰ፣ የማንፈልገውንም እንድንከተብ ተገደናል” እያሉ አሜሪካና ካናዳ ያሉ ዜጎች በሠራተኛ ማኅበራቸው በኩልም ክስ መስርተዋል። ኒውዚላንዳውያንን የመሳሰሉ የተማረሩ ደግሞ አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ‹‹መብታችንን አትጋፉ፣ እምቢ ካልን እምቢ ነው›› የሚል ይዘት ያለው መፈክር በመያዝ የግዴታ ክትባቱን ተቃውመውታል።

የሌላውን ጤና አደጋ ላይ ስለምትጥሉ መብቴ ይከበር ማለት አትችሉም በማለት መንግሥታት ቢሟገቱም፣ ጥቂቶችን ሥራ እንዳንባረር ብለው ከሰጉት ውጪ ማስከተብ አለመቻላቸው ይነገራል። ሙያ እየተለየ አገልግሎት የሚሰጡ ግዴታ እንዲሆንባቸው ቢወሰንም ጉዳዩ ብዙ መነጋገሪ ሆኗል። የአገራችን መምህራንም ግድ ካልተከተባችሁ ማስተማርና ትምህርት ቤት መግባት አትችሉም መባላቸውን ተከትሎ ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል። በተለይ እናቶች አጥቢ ስለሆንን መገደድ የለብንም ሲሉ ተሰምተዋል። ብዙዎች ከክትባቱ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የጎንዮሽ ጉዳትን በመፍራት እምቢኝ ሲሉ ይደመጣሉ። አንዳንዶች ደግሞ የምዕራባውያን ሴራ ውጤት ነው በሚልም ሲፈሩ ይታያል። የተወሰኑ ደግሞ ኃይማኖታዊ ምክንያትን በማስቀመጥ እንደማይከተቡና ዕምነታቸውን እንደሚሸረሽር በመናገር የግዴታ ትዕዛዙን ሲቃወሙት ይሰማል።

የዜጎቻቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል የተለያዩ አስገዳጅ መመሪያና ሕጎችን የሚያወጡ አገራት ቢኖሩም፣ መሥሪያ ቤቶችም በተናጥል በማስገደድ ላይ እንደሚገኙ ይሰማል። በአገራችን የውጭ አገራት ግብረ ሰናይ ተቋማት፣ “ካልተከተባችሁ መሥራት አትችሉም” እያሉ ሠራተኞቻቸውን ያስገድዳሉ። አንዳንዶች ሥራ ለመልቀቅ እንደሚገደዱ ቢገልጹም፣ ተቃውሟቸው ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል።

ሕንድን በመሳሰሉ ወረርሽኙ አሁንም በከፍተኛ ፍጥነት የሚስፋፋባቸው አገራት የሚገኙ ኩባንያዎች፣ “ያልተከተበ ደሞዝ አይከፈለውም” እያሉ አሠርተው ክፍያ መከልከላቸውም ተነግሯል። የሲንጋፖር ባለሥልጣናት በበኩላቸው፣ ያልተከተቡ ሰዎች ቢታመሙ ወጪያቸውን ራሳቸው ይችላሉ የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ትዕዛዝ አውጥተዋል። እነዚህን የመሳሰለ ማስፈራሪያና ቅጣት አገራም ሆኑ ኩባንያዎች ቢያደርጉም፣ አንከተብም ብለው ቆርጠው የቀሩትን ሐሳባቸውን ማስለወጥ አልቻሉም። “ያልተከተበ ይታሰራል” የሚል ሕግ እስካሁን ተግባራዊ ባይደረግም፣ ይህን መሰል አስገዳጅ ሕግ ለሕገ ወጥነት በር ስለሚከፍት ውጤታማ አያደርግም በሚል የማይቀበሉት በርካቶች ናቸው።

የክትባቱን ውጤታማነት በተመለከተ የተለያዩ ጥናቶች እየተካሄዱ ግኝቶች ይፋ መደረግ ከጀመሩ ከራርመዋል። ክትባቶች የሚያስገኙት ጥቅም ከፍተኛ ነው እየተባለ፣ ሊያስከትሉ የሚችሉትም ጉዳት ዝቅተኛ መሆኑ እየተነገረ ነበር። የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች ከሠሞኑ ይፋ እንዳደረጉት፣ ያልተከተቡ ሰዎች ከተከተቡት ይልቅ በ16 ዕጥፍ በበሽታው ሊሞቱ ወይም አስጊ ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ነው።

የአገሪቱ ተመራማሪዎች ባለፉት አራት ወራት ባካሄዱት ጥናት፣ በተባለው ጊዜ ሕይወታቸው ካለፈ ግለሰቦች ሦስት በመቶ ብቻ የሚሆኑት ናቸው ተከትበው የሞቱት። አማካይ ዕድሜያቸው 82 ስለሆነ ለሞት ተዳርገዋል የሚለው የጥናቱ ውጤት፣ ሆስፒታል ከተኙ 63 በመቶ የሚሆኑት ምንም ዓይነት ክትባት ያላገኙ ናቸው ብሏል። የአሜሪካ ተመራማሪዎች ከዚህ ጥናት ውጤት ጥቂት ጊዜ ቀደም ብለው፣ ያልተከተቡ ሰዎች ከተከተቡት የመሞት ዕድላቸው በ11 ዕጥፍ ይጨምራል ብለው እንደነበር ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here