ቦይንግ በኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ አደጋ ከሞቱት 157 መንገደኞችና የበረራ ሠራተኞች ቤተሰቦች ጋር ሥምምነት ላይ መድረሱ ተነገረ

0
494

የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድና ተጠያቂነቱንም እንደሚቀበል በቺካጎ ከሚገኘው የፍርድ ቤት ሠነዶች የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የቦይንግ አክሲዮኖች ድርሻ 1 በመቶ፣ ወደ 218.50 ዶላር መውረዱና ሥምምነቱ ከአሜሪካ ውጪ ያሉ እንደ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ባሉ አገራት ያሉ የተጎጂ ቤተሰቦች በአገራቸው ሳይሆን በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ካሳ እንዲከፈላቸው መንገድ መክፈቱ ነው የተገለጸው።
ካሳው የሚፈጸመው በየአገራቸው ቢሆን የበለጠ ሁኔታውን ፈታኝ እንደሚያደርገውና ክፍያውም ዝቅተኛ እንደሚሆን ይታመናል። በአደጋው ሳም የተባለ ልጃቸውን ያጡ እንግሊዛዊው ማርክ ፔግራም፣ “ለእኛ ዋናው አዎንታዊ ሁኔታ ቦይንግ ተጠያቂነቱን አምኖ ጥፋተኝነቱን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ፓይለቶች ላይ አለማሳበቡ ነው። ስህተታቸውን እንዲያምኑ እንፈልግ ነበር” ማለታቸው ነው የተነገረው።
በተቀራራቢ ጊዜ በ737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሱ ኹለት አደጋዎችን ተከትሎ ቦይንግ የአብራሪዎቹን አቅም ጥያቄ በማስገባትና ጥፋቱን ወደ ሌሎች አካላት በማዛወር ትችት ሲቀርብበት ነበር።
በመጋቢት ወር 2011 የደረሰው አደጋ ከ35 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ የ157 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here