ህወሓት በአማራ ክልል ከ279 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ የሀብት ውድመት ማድረሱ ተነገረ

0
701

የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ እንደገለጸው፣ ህወሓት በአማራ ክልል ወረራ በፈጸመባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከ279 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ የሀብት ውድመት አድርሷል ብሏል።
አሸባሪው ህወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከ6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለችግር እንዲጋለጥ ያደረገ ሲሆን፣ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብን ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬው አፈናቅሏል።
የሽብር ቡድኑ ይሄን ያህል መጠን ያለው ጉዳት ማድረሱ የተረጋገጠው ወረራ በፈፀመባቸው የተለያዩ ዞኖች በሚገኙ 45 ወረዳዎች በተካሄደ ክልል አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ነው ተብሏል።
በጤናው ዘርፍ 1ሺህ 466 ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱም ተነግሯል።
አሸባሪው በ6 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች፣ እንዲሁም በ17 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ላይ ባደረሰው ጉዳትም 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት መውደሙ ነው የተገለጸው።
እንዲሁም፣ በመንገድ መሠረተ ልማትና በድልድዮች ላይ ባደረሰው ጉዳት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት አስከትሏል:: በመስኖ ተቋማትም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ሙሉ በመሉ ከጥቅም ውጭ መሆኑን ለአብነት ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ፣ በግርድፉ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከ279 ቢሊዮን 543 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት እንዲወድም ማድረጉን እና በቀጣይ አዳዲስ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች የጉዳት መጠን ያካተተ ጥናት ሲካሄድ የጉዳቱ ስፋት በእጅጉ የከፋ እንደሚሆንም ተመላክቷል።
በገንዘብ ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት እንደወደመ የተገለጸ ሲሆን፣ የደረሰው ውድመት ቢያንስ ከ10 እስክ 20 ዓመት ክልሉን በልማት ወደ ኋላ የሚጎትት ነው ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here