ዳሰሳ ዘ ማለዳ (ጥር 22/2012)

Views: 386

ኬኒያ 200 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት 2020 ከኢትዮጵያ ልትገዛ መሆኑ ተገለጸ። የግዥው ዓላማም ለኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚወጣውን ወጪ ለመቀንስ ሲሆን፣ በቅርቡም ይህ ስምምነት ተግባራዊ ይደረጋል። ከዚህ ቀደም ኹለቱ አገራት 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመገበያየት ሥምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም፣ አገራቱን የሚያገናኛቸው የመሠረተ ልማት ግንባታ መዘግየት እንዳይተገበር እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። ከዓመታት መዘግየት በኋላ ግን ኹለቱን አገራት የሚያገናኛቸው የ1 ሺሕ 125 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ተጠናቋል። ይህንንም ተከትሎ አገራቱ ያስገነቡት የኃይል መስመር በያዝነው ዓመት በቀጣይ ወራት ውስጥ ወደ አገልግሎት እንደሚገባ የኬንያ የነዳጅ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል። (አዲሰ ማለዳ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………

ኢትዮጵያ እያካሄደች ላለው የበረሃ አንበጣ መከላከል ሥራ 800 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አንድ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት አስታወቀ። የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት (ፋኦ) በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ በተመለከተ ባዘጋጀው የውይይትና ድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ፣ ድርጅቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል። በውይይቱ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የበረሃ አንበጣ ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች ከ485 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት በአስቸኳይ ለመከላከል እቅድ ተነድፎ እየተሠራ እንደሆነ ተጠቁሟል። (ፋና)
…………………………………………………………………………………………………………………………………

ቁጥራቸው ከኹለት ሺሕ በላይ የሆኑ እና 40 ዓመት በስደት የቆዩ ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ ሊመለሱ ነው። ስደተኞቹ የሚመለሱት በፍቃዳቸው መሆኑንም በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያኑ በራሳቸው ፍላጎት ለበርካታ ዓመታት ከቆዩባቸው የዳዳብና የካኩማ ስደተኛ ካምፖች ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስችላቸው ድጋፍና ዝግጅት እየተደረገ ነውም ብለዋል። (ቢቢሲ አማርኛ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………

የእስራኤል መንግሥት ቁጥራቸው 400 የሚሆኑ ቤተ እስራኤላውያንን ለመቀበል መወሰኑን ቻናል 12 የተባለ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኀን አስታወቀ። የእነዚህ ቤተ እስራኤላውያን ቤተሰቦች በአሁን ወቅት ኑሯቸውን በአስራኤል ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ቤተ እስራኤላውያኑ ግንቦት ወር ላይ በእስራኤል ከሚደረገው ምርጫ በፊት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ቁጥራቸው 400 የሚሆኑት ቤተ እስራኤላውያኑን ከኢትዮጵያ ለማምጣት ውሳኔ የተወሰነው በፈረንጆ 2018 ዓመት ነበር። በአሁን ወቅት በእስራኤል 140 ሺሕ ቤተ እስራኤላውን እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመላክታሉ። (አዲስ ማለዳ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………

የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑን አወጀ። በዚህ ምክንያት አምስት የአፍሪካ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ አቋርጠዋል። የኬንያ፣ የሩዋንዳ፣ የማዳጋስካር፣ የሞሪሸስ እና የሞሮኮ አየር መንገዶች ወደ ቻይናና ከቻይና ያደርጓቸው የነበሩትን ሁሉንም ጉዞዎች ለጊዜው እንዳቋረጡም ተጠቁሟል። አየር መንገዶቹ ከዚህ ውሳኔያቸው በፊት ወደ ቻይና ወይም ከቻይና ለመጓዝ ትኬት ቆርጠው የነበሩ ደንበኞቻቸውን ገንዘብ ለመመለስ ወይም በሌላ መስመር እንዲመጡ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። በአፍሪካ ካሉ ጥቂት ግዙፍ አየር መንገዶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ትናንት ሐሙስ እንዳስታወቀው፣ ወደ ቻይና የሚያደርጋቸው ሁሉም በረራዎቹ እንደቀጠሉ ናቸው። (ቢቢሲ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት በመጪው አገር አቀፍ ምርጫ ዙሪያ መከሩ። ውይይቱም በምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ይዘትና አፈጻጸም፣ ወደ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ በሚችሉ ጉዳዮች ዓይነትና ባህሪያት፣ የምርጫና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችሎቶች ስለሚደራጁበት አግባብ እና የዳኞች ሥልጠና ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ተብሏል። እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ከምርጫ ጋር ተያይዞ ለሚቀርቡላቸው አቤቱታዎች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች የሕዝብ አመኔታ እንዲኖራቸው፤ በተለይም ከድምጽ ቆጠራና ውጤት ጋር ተያይዞ ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ አቤቱታዎች በአጭር ጊዜ ውሳኔ ስለሚያገኙበት ሁኔታ፣ የምርጫውን ሂደት ፍትሐዊነት የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ሊወሰድ ስለሚገባ ጥንቃቄም ተወያይተዋል። (የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
…………………………………………………………………………………………………………………………………

በአሶሳ ከተማ አስተዳደር በተለምዶ ጎንድል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጥር 21 /2012 ረፋድ ላይ አንድ ተጠርጣሪ ግለሰብ ዘጠኝ ሰዎችን በስለት በመውጋት ባደረሰው ጉዳት የአራት ሰዎች ሕይወት አለፈ። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው፣ በድርጊቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አምስት ተጎጂዎች በአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ። ግለሰቡ ጩቤ እና ጦር በመያዝ በዘጠኝ ሰዎች ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውሰጥ ኹለት ሕጻናትና ኹለት ወጣቶች ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል። ተጠርጣሪው ግለሰብም በቁጥጥር ሥር ውሏል። (ኢትዮ አፍ ኤም)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com