ባህር ዳር የተጠለሉ ተፈናቃዮች ከተማ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ መከልከላቸውን ተናገሩ

0
1551

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባለው ጦርነት ተፈናቅለው ባህር ዳር የተጠለሉ ተፈናቃዮች በከተማ አስተዳደሩ እንዳይንቀሳቀሱ መከልከላቸውን ተከትሎ ወደ መጡበት አካባቢ እየተመለሱ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በባህር ዳር ከተማ ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃዮች አቅም ያላቸው በከተማዋ በግላቸው ቤት ተከራይተው፣ አቅም የሌላቸው በከተማዋ በተዘጋጁ መጠለያዎች ተጠልለው ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በተለይ በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ የሚሆን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መታወጁን ተከትሎ፣ ተፈናቃዮቹ በከተማዋ በነፃነት መንቀሳቀስና ወጥቶ መግባት አለመቻላቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተለይ ከዋግ ኽምራ ሰቆጣ ዞን የመጡ ተፈናቃዮች በባህር ዳር ከተማ ከተጠለሉ ወራት ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ቀድሞ የነበረው ነፃነታቸው እና ይደረግላቸው የነበረው እንክብካቤ ወደ እንቅስቃሴ ገደብ መቀየሩ ያልጠበቁት ነገር እንደሆነባቸው አስተያታቸውን ሰጥተዋል።
“ከተማ አስተዳደሩ ያሠማራቸው ሕግ አስከባሪዎች የባህር ዳር መታወቂያ የሌላቸውን ተፈናቃዮች ከመስመር ላይ አያፈሱ ሲያስሩ ነበር” ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ወጣት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። ወጣቱ አያይዞም ቀደም ሲል ተከራይተው የሚኖሩ ተፈናቃዮችም ይሁኑ በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ በተለይ ወጣቶች፣ ሲንቀሳቀሱ ከተገኙ እንደሚታሠሩ ገልጿል።

በከተማዋ የሚገኙ ተፈናቃዮች የባህር ዳር መታወቂያ ስለሌላቸው በከተማዋ ለመንቀሳቀስ ከመቸገራቸው በተጨማሪ፣ ለእስር እና ለእንግልት እየተዳረጉ ነው ተብሏል። ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ተፈናቃይ ውጣት፣ “ባለፈው ሳምንት በከተማዋ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 30 ተፈናቃዮች የባህር ዳር መታወቂያ የላችሁም ተብለው ለእስር ተዳርገዋል። ከአንድ ቀን እስር በኋላ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተስጥቷቸው ወደ መጡበት አካባቢ እየተመለሱ ነው” ሲል ኹኔታውን ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ሕግ አስከባሪዎች ተፈናቃዮችን በከተማዋ እንዳይንቀሳቀሱ መከልከላቸውን ተከትሎ የተደናገጡት ተፈናቃዮች፣ በተለይ መጀመሪያ ወደ ባህር ዳር የገቡ ተፈናቃዮች ከባለፈው ሳምነት ጀምሮ መኪና መንቀሳቀስ እስከሚችልበት ቦታ ድረስ በመኪና በመሔድ ቀሪውን መንገድ በእግራቸው ተጉዘው ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

ባህር ዳር ከተማ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎችት በተዘጋጁ መጠለያዎች መጀመሪያ ከገቡት ተፈናቀዮች በተጨማሪ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጦርነቱ ከተስፋፋባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችም ጭምር ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ በመጠለያው እንደሚገኙ ተገልጿል። አዲስ ወደ ከተማዋ ከገቡት ተፈናቃዮች በተጨማሪ ቀድመው ከገቡ ተፈናቃዮች ውስጥ ሴቶች እና ሕፃናት በመጠለያ ጣቢያዎቹ እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

አዲስ ማለዳ ተፈናቃዮች ያቀረቡትን ቅሬታ መሰረት በማድረግ ከባህዳር ከተማ አስተዳደር ስለ ጉዳዩ መረጃ ለማግኘት ለተለያዩ አመራሮች ስልክ ብትደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም። አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ የከተማ አስተዳደሩን የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ማካተት ያልቻለችው “አሁን ምላሽ” መስጠት አንችልም በማለታቸው እና አንዳንዶቹ ስልካቸው ጥሪ ባለመቀበሉ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here