በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ወረ ጃርሶ ወረዳ በ“ኦነግ ሸኔ 256 ቤት ተቃጠለብን ያሉ” ከ8 ሺሕ በላይ ዜጎች ምንም አይነት ድጋፍ ባለማግኘታቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ ማረጋገጥ እንደቻለችው እነዚህ “ቤታችው የተቃጠለባቸው” ከ8 ሺሕ በላይ ዜጎች አካባቢውን ለቀው ከወጡ ከጥቅምት 17/2014 ጀምሮ፣ ከመንግሥትም ሆነ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች ምንም ዓይነት የመጠለያና የምግብ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ችግር ላይ ናቸው።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ተስፋዬ ንጉሴ የተባሉት ግለሰብ፣ ቤታቸው እንደተቃጠለባቸውና ሰባት ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ የመጠለያ ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል። መንግሥት ምንም አይነት ድጋፍ አላደረገልንም የሚሉት ተስፋዬ፣ ቤታቸው ሲቃጠልባቸው ንብረታቸውም አብሮ መቃጠሉን ተከትሎ ካጋጠማቸው የምግብ ዕጥረት በተጨማሪ፣ መጠለያም ማግኘት እንዳልቻሉ ነው ያብራሩት።
ግለሰቡ አያይዘውም፣ ቤተሰቦቻቸው እየተመገቡ ያሉት “በዱር የሚገኙ እህሎችን አየሸመጠጡ ነው” ያሉ ሲሆን፣ በመጠለያ ዕጥረት ምክንያት ኑሯቸውን በጫካ ውስጥ ካደረጉ ከሦስት ሳምንት በላይ ማስቆጠራቸውን ነው ለአዲስ ማለዳ ያመላከቱት።
ሌላኛው ተመሳሳይ ችግር እንዳለባቸው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት ዳኘ በላይ የተባሉት ግለሰብ ናቸው። እንደ ዳኘ ገለጻ ከሆነ፣ በወረዳው ሥር በምትገኘው “ቢፊኔ ኤራ” ቀበሌ የሚገኙ የ256 አባውራ ቤቶች ሲቃጠሉ፣ “ኹለት ፖሊሶች ብቅ ብለው ተመለሱ እንጂ፣ ከዚያ ወዲህ እንዴት ሆናችሁ ብሎ የጠየቀን አካል የለም” ነው ያሉት።
ዳኘ በላይ አክለውም፣ እስካሁን በተቃጠሉት ቤቶች ምትክ ቤት መሥራት እንዳልተቻለ ጠቁመው፣ አቅም የሌላቸው ሽማግሌዎች “ምንም ማድረግ አንችልም እዚሁ ይግደሉን ብለው አመዱን ጠርገው ነው የሚኖሩት” ሲሉ ነው የተመለከቱትን የገለጹት።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ ቤቶቹን በእሳት ባቃጠለበት ወቅት በአንዲት ዐይነ ሥውር ሴት፣ በአንድ ሽማግሌ እና በአንድ ሕፃን ልጅ ላይ የአካል ጉዳት አደርሷል። በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች አሁንም ተመሳሳይ ችግር ይደርሳል የሚል ሥጋት እንዳደረባቸውም ነው የተመላከተው።
አስተያየት ሰጭዎቹ አክለውም፣ ወደ ቦታቸው ተመልሰው መጠለያ እንዳይሠሩ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ የሚያደርሰው ጥቃት አለመቆሙን እንደምክንያት ያነሱ ሲሆን፣ “ታጣቂ ቡድኑ በሐሮ ጨለንቆ መቃ ወንዝና ደረቅ ወንዝ” ተብሎ በሚጠራ ቦታ መሽጎ እንደሚገኝና ጥቃት እየሠነዘረባቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።
የአካባቢው ታጣቂዎች በየኬላው ተመድበው ከለላ ለማድረግ እየሞከሩ ነው የሚሉት ዳኘ በላይ፣ ሴቶችና ሕፃናት ጥይት በተተኮሰ ቁጥር ስለሚሠጉ፣ እነሱን ማረጋጋት እንደከበዳቸውም ነው ያመላከቱት።
ዳኘ በላይ አያይዘውም፣ ሽብርተኛ የተባለውን ኃይል ለመመከት እየሞከሩ ቢሆንም የመሣሪያ ዕጥረት እንዳለባቸው ገልጸው፣ ይህንኑ ችግራቸውን ለወረዳው አስተዳደር ቢያሳውቁም እስካሁን በቂ መሣሪያ እንዳላገኙ ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች አክለውም፣ በኦነግ ሸኔ ቤቶቹ በተቃጠሉበት ወቅት ከ800 በላይ የሚሆኑ የቤት እንስሳትም በቤቶቹ ውስጥ እንዳሉ መሞታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የሚመለከተው አካል የመጠለያና የምግብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው፣ ብሎም በታጣቂ ቡድኑ የሚደርስባቸውን ጥቃት እንዲያስቆምላቸው ነዋሪዎቹ አሳስበዋል።
ጥቃቱ ተከሰተበት የተባለው የቢፊኔ ኤራ ቀበሌ ሊቀ መንበር ወርቅዬ መኮነን በበኩላቸው፣ ከ8ሺሕ በላይ ዜጎች እንደተፈናቀሉ ያመላከቱ ሲሆን፣ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለወረዳው አስተዳደር ቢያሳስቡም ምላሽ እንዳላገኙ ነው የገለጹት።
ወርቅዬ አክለውም፣ “ጠላት በአንድ ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ነው ያለው፤ መንግሥት እንኳን መሣሪያ ቀርቶ ጥይትም 10 ፍሬ ብቻ ነው የሰጠን፤ የአካባቢውን ሰብልም መሰብሰብ አልተቻለም” ብለዋል።
አዲስ ማለዳ የነዋሪዎቹን ችግር በማስመልከት ወደ ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ አስተዳደር አየለ መንግስቱ ስልክ ብትደውልም ስልክ ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።
ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014



