በቤኒሻንጉል ጉምዝ ካማሺ ዞን የጉምዝ ታጣቂዎችና ኦነግ ሸኔ ጥምረት በመፍጠር ጥቃት እየፈጸሙ ነው ተባለ

0
1040

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካሚሺ ዞን የሚንቀሳቀሰውና ራሱን “የጉሙዝ ነጻ አውጪ ግንባር” ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን፣ ከኦነግ ሸኔ ጋር ጥምረት በመፍጠር <ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት> እየፈጸመ መሆኑን ተገለጸ።
በካማሺ ዞን ቤሎ ጅጋንፎይ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች፣ የጉሙዝ ነጻ አውጪ ግንባር የተባለው ታጣቂ ቡድን በአካባቢው በስፋት እየተንቀሳቀሰ ስለሚገኝ፣ አዝመራቸውን መሰብሰብ እንዳልቻሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የታጣቂ ቡድኑ አባላት በተለይ ጅጋንፎይ ወረዳ ውሪንቃ ቀበሌ አካባቢ በስፋት ስለሚንቀሳቀሱ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለሕይወቱ ዋስትና በማጣቱ ቀበሌውን በሙሉ ለቆ ፏፏቴ ወደተባለች የገጠር ከተማ መሸሹ ተነግሯል። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ 13 የአካባቢው አርሶ አደሮች በታጣቂ ቡድኑ መገደላቸውን ተከትሎ ሌሎች አርሶ አደሮቹ ሥጋት ስላደረባቸው፣ የደረሰ ሰብላቸውን ትተው ለመሰደድ እንደተገደዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

“የተገደሉት አርሶ አደሮች ሬሳ በየዱሩ እና በየበረሃው ተጥሎ አውሬ እንዲበላው ተደርጓል” የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ እነሱም ላይ ተመሳሳይ ዕጣ ከመድረሱ በፊት ቤት ንብረታቸውን ትተው ቤተሰባቸውን ይዘው ለመሸሽ እንደተገደዱ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የወረዳው አስተዳዳሪ ነገሩ አያና፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ቅሬታ እና የደኅንነት ሥጋት እውነት መሆኑን ገልጸው፣ ለነዋሪው የደኅንነት ዋስትና መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል። የጉምዝ ታጣቂ ቡድን ከኦነግ ሽኔ ጋር ጥምረት በመፍጠር ነዋሪዎቹን እያሸበረ እንደሆነ አስተዳዳሪው ጨምረው ገልጸዋል። አስተዳዳሪው አያይዘውም፣የአካባቢው የደኅንነት ሥጋት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ጠቁመዋ፣ ጉዳዩን ለበላይ አካል በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም ሕዝቡን ሊታደግ የሚችል ድጋፍ እንዳለገኙ እና ጥቃቱም ብሔርን መሠረት ያደረገ እንደሆነ አስረድተዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የውሪንቃ ቀበሌ አርሶ አደር ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ “600 ኩንታል የሚገመት የሰሊጥ ምርት የደኅንነት ሥጋት ስላለብኝ ሳልሰበስበው ማሳ ላይ ቀርቷል። ሜዳ ላይ የቀረው የእኔ አዝመራ ብቻ ሳይሆን የመላው የውሪንቃ ቀበሌ አርሶ አደር ነው” ብለዋል።

በተያያዘም፣ በእንጂጋ ወረዳ ውስጥ የተለያዩ ቀበሌዎች አሁንም በሥጋት ቀጠና ላይ መሆናቸውን አርሶ አደሮቹ ይናገራሉ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ በኩል፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ካማሺ ዞን ጀጋንፎይ ወረዳ በመግባት፣ ከጉምዝ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር በማበር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አርሶ አደሮቹ ጠቁመዋል። ታጣቂዎቹ ከቦታ ቦታ በሚዘዋወሩበት ወቅትም የአርሶ አደሩን ቤትና ንብረት እየዘረፉ መሆኑንም ተናግረዋል።

የታጣቂዎቹ ጥቃት ማንነትን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ የወረዳው ነዋሪዎች ሕይወታቸውን ለማዳን ሀብትና ንብረታቸውን ትተው መፈናቀላቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ ችግራቸውን ለወረዳው አስተዳዳሪ በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም፣ የአስተዳደሪው ምላሽ ግን ጉዳዩ ከወረዳው አቅም በላይ ነው ከማለት የዘለለ ባለመሆኑ ተስፋ ቆርጠው እንደተቀመጡ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሺ ዞን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ኩታ ገጠም በመሆኑ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ወደ ካማሺ በመግባት ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንደሚፈጽሙና አሁን ላይ ደግሞ፣ ከጉምዝ ታጣቂ ቡድን ጋር ቅንጅት በመፍጠራቸው ለአካባቢው ሥጋት መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here