ከምኒልክ ሆስፒታል ተገቢውን አገልግሎት እያገኘን አይደለም ሲሉ ሕሙማን አስታወቁ

0
692

ከምኒልክ ሆስፒታል ተገቢውን አገልግሎት እያገኘን አይደለም ሲሉ ሕሙማን አስታወቁ

ወደ ምኒልክ ሆስፒታል የሚያቀኑ ሕሙማን ተገቢውን የአልጋና የካርድ አገልግሎት እያገኙ ባለመሆናቸው ቅሬታቸውን ገለጹ።
ቅሬታ አቅራቢ ሕሙማኑ እንደሚሉት ከሆነ፣ ‹ሪፈር› ተጽፎላቸው ሕክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ በሚያቀኑበት ወቅት ካርድ ለማውጣት እንኳ ሦስት ቀን እንደሚፈጅባቸው ገልጸው፣ በዚህም ከሕመማቸው በላይ “መጉላላቱ” ሌላ ችግር እንደሆነባቸው ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ካቀረቡት መካከል ካርድ ከማውጣት ጋር ተያይዞ መጉላላት እንደገጠማቸው የተናገሩት ትዕግስት ቀንዓ ናቸው። እንደ ትዕግስት ገለጻ ከሆነ፣ በሆስፒታሉ ካርድ ለማውጣት ሦስት ቀን መጠበቃቸውን ተናገረዋል።
ካርድን በተመለከተ በሆስፒታሉ መጉላላት ይስተዋላል የሚሉት ትዕግስት ቀንዓ፣ ምንም እንኳ በወቅቱ ካርድ አለማግኘቱ ተጽዕኖ እንዳለው ቢገልጹም፣ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚያገለግሉ ሐኪሞችና ነርሶች የሚሰጡት አገልግሎት መልካም መሆኑን ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ ካነጋገረቻቸው ሰዎች መካከል ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ አቤል ጥላሁን ናቸው። አቤል የሐሞት ጠጠር ታማሚ የሆኑት ታላቅ እህታቸውን ወደ ሆስፒታሉ ይዘው መመላለስ ከጀመሩ አንድ ዓመት እንዳስቆጠሩ ያመላከቱ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ አልጋ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የጠቆሙት።

በ2013 ጥቅምት ወር እህታቸው ከኮተቤ ጤና ጣቢያ ‹ሪፈር› ተጽፎላቸው ወደ ምኒልክ ሆስፒታል መጥተው ከተመረመሩ በኋላ ሌላ ቀን ተቀጥረው እንደተመለሱና በቀጠሯቸው ቀን ቢመጡም ድጋሚ እንደተቀጠሩ ነው አቤል ያመላከቱት።
ግለሰቡ እንደተናገሩት ከሆነ በቀጠሮው መሠረት እህታቸውን ይዘው ወደ ሆስፒታሉ ቢያቀኑም፣ “በኮሮና ምክንያትና ካርድ ጠፍቷል” ተብለው ለኹለተኛ ጊዜ እንደተመለሱና ባለፈው ሳምንት አልጋ ለመያዝ ወደ ሆስፒታሉ ቢያቀኑም አሁንም በድጋሚ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ነው የገለጹት።

እንደ አቤል አስተያየት ከሆነ፣ እህታቸው አልጋ እንዲይዙ ቢጻፍላቸውም አልጋ ባለማግኘታቸው ለሦስተኛ ጊዜ በድጋሚ ሊመለሱ መሆኑን ገልጸው፣ በወቅቱም ስልክ ሊደወልላቸው እንደማይችል ከእስካሁኑ ድርጊት ተነስተው መረዳት እንደማይከብዳቸው ነው የጠቆሙት።
ቀጠሮ ቢሰጠንም የምንመጣበትን ቀን እንኳን አልተነገርንም የሚሉት አቤል፣ የእስካሁኑ የቀጠሮ ጊዜ እንኳን በመርዘሙ እህታቸው ሕመሙ እየተባባሰባቸው እንደሆነ ነው ያመላከቱት። አቤል አክለውም የታመመ ለዛውም ሪፈር የተጻፈለት ሰው በፍጥነት መፍትሔ ሊሰጠው ሲገባ፣ በእያንዳንዱ ቀጠሮ ቀን ሲመጣ ኹሌም ምርመራ ስለሚደረግ ሕሙማኑ ከሚደርስባቸው የኢኮኖሚ ችግር በተጨማሪ፣ በሕመሙ መባባስ ምክንያት ለሕልፈተ ሕይወት የማይዳረጉበት ምክንያት እንደማይኖር ነው የተናገሩት።

በሆስፒታሉ የሚገኙ ሕሙማን ከዚህም በተጨማሪ፣ በተለይም የቀዶ ጥገና ሕክምና ተደርጎላቸው በሆስፒታሉ አራተኛ ፎቅ በአልጋ ላይ የሚገኙ ሰዎች ሌሊቱን ጭምር በጩኸት እንደሚረበሹና ለመተኛት እንደሚቸገሩ ተመላክቷል።
የታመመ ሰው እንቅልፍ በቶሎ ሊይዘው አይችልም፤ ከያዘው በኋላ የሚረበሽ ከሆነ ደግሞ ሌላ ችግር ነው፤ በጩኸት ምክንያት መተኛት አልቻልንም የሚሉት ኤልያስ ኃይሉ ናቸው።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት የምኒልክ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ታደሰ ኃብተዮሃንስ ጋር ቆይታ አድርጋለች። ሥራ አስኪያጁም “የአልጋ ችግር አይኖርም ብዬ አላስብም፣ በቀዶ ጥገና 91 በመቶ አልጋ የተያዘ ክፍል ነው” ብለዋል። አያይዘውም በሆስፒታሉ ትልቅ ተብሎ በሚጠራው ሥራ (የእንቅርትና የካንሰር) ቀዶ ጥገና ለማድረግ የሚጠብቁ 436 ተራ ያያዙ ሕሙማን እንዳሉ አመላክተዋል።

እነዚህ ቀጠሮ የተሰጣቸው ሰዎች ስልክ ሲደወልላቸው ወረፋቸውን ጠብቀው እንደሚመጡ ዋና ሥራ አስኪያጁ የገለጹ ሲሆን፣ በሐሞት ጠጠር ሕመም ቀጠሮ ተራዘመብን ላሉት ቅሬታ አቅራቢዎች በተመለከተ፣ “ወረፋ የሚጠብቁ አሉ፤ ምክንያቱም አልጋ የለንም፤ አልጋችን መያዝ ከሚችለው አቅም በላይ ነው ሊሆን የሚችለው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ቀጠሮ ተራዘመብን በሚል የቀረቡ ቅሬታዎችን ያለውን ሁኔታ ዐይተው ለመፍታት እንደሚሞከርና ወደ ሆሰፒታሉ የሚያቀኑ ሕሙማንን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here