ሴቶችና ወሲብ

Views: 1000

ብዙዎች በግልጽ ከማይነጋገሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል በጾታዊ ግንኙነት ውስጥ ያለው ወሲብ ወይም ግብረ ሥጋ ግንኙነት አንዱ ነው። ነገሩ ደግሞ በሴቶች ሲሆን የበለጠ ይወሳሰባል። ሕሊና ብርሃኑ ይህን ሐሳብ በግልጽ አንስተዋል። የወንዶች የበላይነት አቀንቃኝ በሆነ ዓለምና ስርዓት፣ አባታዊ ስርዓት (Patriarchy) ወሲብን ጨምሮ በአብዛኛው ማኅበራዊ እሳቤ፣ ጸባይ እና ድርጊቶች ላይ ይስተዋላል ይላሉ። ይልቁንም ከወሲብ ጋር በተገናኘ ይህ የበላይነት በሴቶች ላይ ያሳደረውን ጫና እና የፈጠረውን ተጽእኖ ጠቅሰዋል።

ወሲብ በሰዎች መካከል ግልፅ ሥምምነትን ተከትሎ የሚደረግ የአካላዊና ስሜታዊ ቅርበት ጥግ ድርጊት ነው። ይህም በተለምዶ ፍቅርን፣ ትዳርን፣ የወዳጅነት ትስስርን ተከትሎ አልያም ጊዜያዊ ደስታን ከመሻት ከዚህ ቀድሞ ምንም ግንኙነት ሳይኖር በመጀመሪያ ትውውቅ የሚፈፀም ሊሆን ይችላል።

በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ ከልካይ አልያም ባሕላዊና ሃይማኖታዊ አንድምታ ካላቸው ወሲብን የሚመለከቱ አስተያየቶች በቀር ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ ስለ ወሲብ የሚደረጉ ውይይቶች በድብቅ እና ከዝግ በሮች ጀርባ የሚደረጉ ናቸው። በወሲብ ነክ ርዕሶች ዙሪያ መወያየት ነውርነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የሔደ ቢመሥልም፣ አሁንም የሴቶችን የወሲብ ፍላጎትና ተፈጥሮአዊ ባህርያትን የሚመለከት ሲሆን ግን እንደነውር መቆጠሩ አልቀረም።

በጣም አስቸጋሪው ማኅረሰባዊ ፍረጃ ደግሞ በእነዚህ ውይይቶች ሴት ለወሲብ ግድ የሌላት፣ በወንዶች ጥያቄና ስሜት ተመሪ ፍጡር ሆና መሳሏ ነው። ይህን ተከትሎ ወሲብን የሚመለከቱ ውይይቶች በሴቶችና በወንዶች መካከል ሲደረጉ ይዘታቸው እጅጉን ይለያያል።

የሴቶች ወሲባዊ ድርጊትና ፍላጎትን ከድንግልና አልያም ከመውለድ ድርሻ ጋር ብቻ፣ የወንዶችን ደግሞ ደስታን ከመሻት ጋር የማያያዝ ሁናቴ ኹለቱም ፆታዎች ጋር ይታያል። ይህ ጅምላ ፍረጃ የወንድ የበላይነትን ከሚያሰርፀው ፆተኝነት ማዕቀፍ የሚመነጭ ሲሆን፣ ወንዶችን አቅራቢ ወይም ሰጪ፣ ሴቶችን ተቀባይ ወይም ጠባቂ አድርጎ የሚያይ የተዛባ ማኅበረሰባዊ ዕይታ አንደኛው መገለጫ ነው።
ይህ የወንድ የበላይነትን አቀንቃኝ ስርዓት በሳይንሳዊ አጠራር አባታዊ ስርዓት (Patriarchy) የምንለው ሲሆን፥ ለማኅበራዊ ልምዶቻችን ምግብ ነው፤ ባሕርያችን፣ ስለ ትክክል እና ስህተት ሚዛን ያለንን እምነት መገንቢያም ጭምር ነው። ስለዚህ አብዛኛው ማኅበራዊ ዕሳቤ፣ ባሕሪይ እና ድርጊታችን ወሲብን ጨምሮ በእነዚህ ስርዓትና እሴቶች የሚገነባ ነው።

ይህ ለወንድ የሚያደላ ስርዓት በወሲብ አመላካከትና አፈፃፀም ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት የተለያዩ መንገዶች አሉ፦
አንደኛው ስለ ወሲባዊ ጥቃት የምንነጋገርበት መንገድ ነው። የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን የምንጠይቅበት፣ ታሪካቸውን የምናብጠለጥልበት፣ ተጠያቂነትን የምናዛባበት የተዛነፈ ዕይታንም ይጨምራል። የሴቶች ፍላጎትና እሺታ ፈቃድን በተመለከተ የሚሰነዘሩ አስታያየቶችና ቀልዶች፣ የሕግና የሕክምና ባለሙያዎች ጋር የሚስተዋሉ ፆተኛ አመለካከቶች ሁሉ እዚህ ውስጥ ይካተታሉ።
እዚህ ጋር ደግሞ በተለይ የመደፈር ወንጀልን ጨምሮ የተለያዩ ወሲባዊ ጥቃቶች ሲደርሱ ከሰብዓዊ መብት ገፈፋ ሳይሆን ከ’ድንግልና’ ማጣት ጋር የሚያያዙ አመለካከቶችና የሕግ ማዕቀፎችን ልብ ማለት ይገባል። ለምሳሌ ያህል የመደፈር ወንጀል እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ላይ ባለው በሕግና ደንብ መረጃ ስር “ክብረ ንፅህናን መድፈር” በሚል ዘርፍ ሲቀመጥ፣ የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ ላይም ቢሆን “መልካም ጠባይ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ምዕራፍ ስር “ንፅህና ላይ የሚፈፀሙ፣ የክብረ ንፅህና ድፍረት በደል” በሚሉ ተደጋጋሚ ቃላቶች ሲገለፅ እናያለን።

በነገራችን ላይ ሴትን ብቻ ከጋብቻዋ በፊት ‘በንጽህና’ እንድትኖር የሚያስገድዱ መስፈርቶች እንዲሁም ‘ድንግልና’ን የሴትን ልጅ ሥነ ምግባራዊ መልካምነት የሚያሳይ ‹የጠባይ ምስክር ወረቀት› አድርገው የሚያስቀምጡ ፆተኛ አመለካከቶች ጥቃት የደረሰባትን ሴት እንደተበላሸች፣ እንደጎደለች ማሳያ እንጂ ፍላጎቷ እንደተገፋና ሰብአዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባት ግለሰብ ለማሰብ አይሞክሩም/ፍላጎቱም የላቸውም።

በዚህ ዕይታና በሌሎች የተሳሳቱ አመለካከቶች ምክንያት ጋብቻ ውስጥ ያለ አስገድዶ መድፈር ወይም ያለ ኹለቱም ግልፅ ፈቃድ የሚፈፀም ወሲብ በኢትዮጵያ ሕግ እንደ ወንጀል አይቆጠርም፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ወሲብ የፈፀመችና በትዳርና በወንድ ጥበቃ ስር ያለች ሴት “እንዴት ክብሯን ልታጣ፣ ምንስ ቆርጧት ላትፈቅድ ትችላለች?” የሚል አመለካከት ስላለ ጭምር ነው።
የወንድ የበላይነት ስርዓት ኹለተኛው ተጽእኖው የሚያርፈው በፈቃድ ላይ የተመሰረተ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም ላይ ያሉ አመለካከቶችን በሚመለከት ነው። ወሲብ ምንድን ነው? በወሲብ ላይ ያለን አመለካከትስ? የወሲብ ግንኙነት ውስጥ የማን ፍላጎቶች እንደሚሟሉና እንደሚደመጡ፣ የመደሰት መብት የሚገባት/ው ማን እንደሆች/ነ በዚህ ስርዓት ምልከታ ይወሰናል። ሴቶች ላይ ሲመጣ እዚህ ጋር በድጋሚ በድንግልና ላይ፣ መጸጸት እና አለመጸጸት፣ መስጠትና አለመስጠት የሚሉ ትርክቶች ላይ ያተኩራል።
“ድንግልናሽን የወሰደን ወንድ ዕድሜ ልክ ትከተይዋለሽ”
“ወንዶች አንዴ ወሲብ ካደረጉ በኋላ ታስጠያቸዋለሽ፤ በቃ የነሱ ተፈጥሮ ነው። ምን ታደርጊዋለሽ?”
“የፈለገውን ካገኘ ዞር ብሎም አያይሽም”
“ኧረ አትስጭው!”
“ሲፈልግ ስጪው፣ ያለበለዚያ ሌላ ጋር ይሄዳል… ወንድ መሆኑን ረሳሽው እንዴ?”
የምናነባቸው መጽሐፍትም ቢሆኑ ወይ “አንሶላ ውስጥ ገብተው ወደ ሌላ ዓለም ተጓዙ” አልያም ደግሞ አጀብ በሞላበት አገላለጽ “የአንሶላው ጨርቅ በደም መላወሱን ሲያይ ወንድነቱ ሞላለት” ዓይነት ገለጻ ይበዛቸዋል።

ፊልሙም ቢሆን በተመሳሳይ “ድንግልናዬን ይዞት እብስ አለ” ብላ ከምትነፋረቅ ሴት አልያም በሴት ጓደኞቿ ታጅባ “ሴቶች እኮ ጊዜ ይወስድብናል…ወንዶች ናቸው በወሲባዊ ግንኙነት ለመደሰት የታደሉት” የሚል ምክር ከምትቀበል ሴት ያለፈ አይደለም።

እኚህ ሁሉ ማኅበራዊ ተጽዕኖዎች የሴቶችን ሚና ገድበው ያስቀምጣሉና ሰዎች አዩኝ አላዩኝ በሚል ድብብቆሽ የታጀበ በቦታው መገኘት፣ መድማት/አለመድማት (“ድንግልና” ጋር የተያያዙ አፈታሪኮች) ውጪ ብዙ ሴቶች ወሲብ ላይ ያላቸውንና የሚገባቸውን ቦታ እንዳያውቁ ያደርጓቸዋል።

በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለ የወንዶች የበላይነት ሦስተኛው ተጽዕኖ ሴቶችን ንቁ የወሲብ ተሳታፊዎች ሊያደርጋቸው የሚያስችል በቋንቋና በባሕል ያለ የመግባቢያ መሣርያ አለመኖርም ጭምር ነው። ይህም በመሆኑ ሴቶች ሙሉ ለሙሉ ምቾትና ፈቃድ የመስጠት ሁኔታዎች ሳይሟሉላቸው፣ አንዴ ከተጀመረ አይቀር በሚል ማኅበራዊ ይሉኝታ ተይዘው ሊጨርሱ የማይፈልጉት ወሲብ ውስጥ እራሳቸውን ሲያገኙ እንሰማለን።

“አልተመቸኝም፣ ደስታ አልተሰማኝም፣ ይህ ቢስተካከልልኝ” የሚሉ አስተያየቶችን ማቅረብና የሚፈልጉትን መጠየቅ የሴቷን የቀድሞ ልምድ ያሳያል አልያም የወንዱን ስሜት ይነካል በሚል ስጋት ደስታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ የሚመከሩ ሴቶችም አይጠፉም።

ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወሲባዊ ደስታ እና እርካታ በሰዎች አካላዊ እና አእምሯዊ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ይህ እንደ ሰው የጤንነታችን፣ የዕድገታችን እና የደስታችን ተፈጥሯዊ እና ወሳኝ ክፍል ነው። ስለዚህ ሴቶች ደስታን ማግኘታቸው እንዲሁም የድርጊቱ እኩል ባለቤት መሆናቸው አስፈላጊ ነው።

ወሲባዊ ግንኙነት ለሴቶችም ቢሆን ለወንዶች ደስታን የሚፈጥር ድርጊት እንደሆነ ሊታወቅ፣ ግልጽ ውይይት ሊደረግበት፣ የተሳታፊ ወገኖችን እኩል ስሜትና ፍላጎት በጠበቀ መልኩ ሊደረግ ይገባል እላለሁ።

ሕሊና ብርሃኑ
የሥርዓተ-ፆታና የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በዚህ አድራሻ ይገኛሉ bhilina.degefa@gmail.com

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com