የጦርነት ፕሮፖጋንዳ እና ዲፕሎማሲ

0
1290

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከተጀመረ ባሳለፍነው ጥቅምት 24/2014 አንድ ዓመት አስቆጥሯል። ጦርነቱ መነሻውን በትግራይ ክልል ያድርግ እንጅ ከባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቷል። አንድ ዓመት የዘለቀው ጦርነት የኃይል ፍልሚያ ብቻ አለመሆኑን መንግሥትን ጨምሮ ብዙዎች ይስማማሉ።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለው ጦርነት ገና ከጅምሩ ከኃይል ፍልሚያ በላይ፣ በፕሮፖጋንዳ እና በዲፕሎማሲ የተስፋፋ እና የተራዘመ ጦርነት መሆኑን ከወታደራዊ እስከ ፖለቲካ ባለሙያዎች በተደገጋሚ ሲገልጹ ይሰማል።
ኢትዮጵያ አሁን የገጠማት ጦርነት “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የሚባለው አባባል በተግባር እያሳየ መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ። ለዚህም እንደማሳያ የሚያነሱት የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ፣ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የገባው ህወሓት ጦርነቱን ያስፋፋበት መንገድ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ሕዝብ እንዲሸበር እና አካባቢውን ለቆ እንዲሸሽ በማድረግ ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ጦርነቱ የኃይል ፍልሚያ ከመሆን አልፎ፣ በውጭም በውስጥም በተቀናጀ መንገድ የሚደረግ የፕሮፖጋንዳና የዲፕሎማሲ ጦርነት ሆኗል። ይሁን እንጅ መንግሥት ውጤታማ የጦርነት ፕሮፖጋነዳና ዲፕሎማሲ ስልት አለመጠቀሙን ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል የቀጠለው ጦርነት ፕሮፖጋንዳና ዲፕሎማሲዊ መልኩን በተመለከተ፣ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ወታደራዊ እና የፖለቲካና የውጭ ግንኙነት ባለሙያዎችን አነጋግሮ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

በኢትዮጵያ ከተጀመረ አንድ ዓመት ያሳለፈው ጦርነት መነሻውን በትግራይ ክልል ያድርግ እንጅ አሁን ላይ ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ወጥቶ በአማራ እና በአፋር ክልሎች እየተስፋፋ ነው። የጦርነቱ መስፋፋት እና የተራዘመ መሆን በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ ጫና ማሳደሩ አልቀረም።

መነሻውን በትግራይ ክልል ያደረገው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት የተጀመረው ጥቅምት 24/2013 ነው። በወቅቱ የትግራይ ክልል መንግሥት የነበረውና በአሁኑ ጊዜ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) መቀመጫውን በትግራይ ክልል ዋና ከተማ ባደረገው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ነበር ጦርነቱ የተነሳው።

ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን በወቅቱ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ወጥተው ያረዱት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ አቅንቶ ሕግ እንዲያስከብር ትዕዛዝ መሰጠቱን ተናግረው ነበር። መከላከያ በተሰጠው ትዕዛዝ ሕግ ለማስከበር ወደ ትግራይ ባቀናበት ወቅት፣ ከህወሓት ጋር አንድ ወር ያልፈጀ ውጊያ በማድረግ መቀሌን ተቆጣጥሮ ነበር። በወቅቱ የፌዴራል መንግሥት ትግራይን ለማስተዳደር “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር” መሥርቶ በክልሉ ለስምንት ወራት መቆየቱ የሚታወስ ነው።
የአገር መከላከያ ሠራዊት የተሰማራበትን “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ቢያጠናቅቅም፣ ትግራይን በጊዜያዊነት ለማስተዳደር ከተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በትግራይ ለስምንት ወራት ቆይቷል።

በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የውጭ ጫና መታየት የጀመረው በዚያን ወቅት ነበር። በወቅቱ የፌዴራል መንግሥት ያቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር እና የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በህወሓትና ደጋፊዎቹ በኩል ለውጭ አገራት እና ለውጭ ሚዲያዎች በሚሰጡ መረጃዎች በክልሉ የተሰማራው የታጠቀ ሠራዊት በአስገድዶ መድፈርና በንጹኃን ግድያ ክስ ይቀርብበት ነበር። በዚህም እንደ አሜሪካ ያሉ አገራት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በተለያየ መንገድ ጫና ማሳደራቸው አይዘነጋም።

በወቅቱ በፌዴራል መንግሥት ላይ የሚደርሱት የውጭ ጫናዎች በሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ ያጠነጠኑ፣ የኤርትራ ሠራዊት በጦርነቱ መሳተፉና የኢትዮጵያን ድንብር አልፎ በመግባቱ ላይ የሚያተኩሩ እና የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል በሚሉት ጉዳዮች ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። በተጠቀሱት እና በሌሎችም ምክንያቶች የፌዴራል መንግሥት በውጭ ሚዲያዎች ከመብጠልጠል ጀምሮ ኤርትራን ጨምሮ እስከ ማዕቀብ ያደረሰ ጫና አርፎበታል።

የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የቆየው ለስምንት ወራት ሲሆን፣ በቆየባቸው ወራት ከጊዜ ወደ ጊዜ የደረሰበት የውጭ ጫና የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ እንዲወጣ ካስገደዱት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው። መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል የወጣው ሰኔ 21/2013 ሲሆን፣ በወቅቱ የወጣበትን ምክንያት ሲገልጽ ወቅቱ የእርሻ ወቅት በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ የእርሻ ሥራውን እንዲከውን በማሰቡ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ደርሱ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት መስተጓጎል መንግሥት ከወጣ በኋላ ይሻሻሉ መእንደሆኑ ለማሳየት እንዲሁም፣ በእነዚህ ጉዳዮች መነሻነት ከውጭ የሚመጣውን ጫና ለመቀነስና የውጭው ማኅበረሰብ ሁኔታውን እንዲረዳው ለማድረግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ አብራርተው ነበር።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ባለው ጦርነት መነሻነት አሜሪካ በግንቦት 2013 በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ለትግራይ እና ሌሎች ክልሎች ቀውስ ተጠያቂ ናቸው ያለቻቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የህወሓት አባላትን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክል የቪዛ ገደብ ወይንም ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።

በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ዕድል ሥርዓት ተጠቃሚነቷን (አፍሪካ ዕድገት ከቀረጥ ነጻ ዕድል የንግድ ሥርዓት-አጎዋ) ማገዷን አሜሪካ አስታውቃለች። የቀረጥ ነጻ ንግድ ሥርዓት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሠማሩ አምራቾች ምርታቸውን ለአሜሪካ ገበያ ከቀረጥ ነጻ የሚያቀርቡበት ሲሆን፣ ውሳኔው በኢትዮጵያ ላይ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

አሜሪካ ውሳኔውን ያሳለፈችው በኢትዮጵያ ያለውን ችግር በውል ሳትረዳ መሆኑን በውሳኔው ላይ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹ የሚታወስ ነው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፣ እገዳው ከ200 ሺሕ በላይ አነስተኛ ገቢ ያላቸው እና ከጉዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው በተለይም ሴቶችን ተጎጂ እንደሚያደርግ ጠቅሷል።

ኢትዮጵያን ከአጎዋ ማገድ በኢትዮጵያ ያለውን ችግር በየትኛውም ሁኔታ ሊፈታው እንደማይችል የጠቀሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ፣ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔውን መልሶ እንዲያጤነው መጠየቁ የሚታወስ ነው። ውሳኔው በሽብርተኝነት የተፈረጀውን የህወሓትን ቡድን የሚያበረታታ እና ኢትዮጵያውያን ከድህነት ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረትና ፍላጎት የሚጎዳ መሆኑንም ጠቁሟል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከገጠማት የአገር ውስጥ ጦርነት ባሻገር እጅግ የበረታዉ የዉጭ አገራት ተጽዕኖ ሌላ የራስ ምታት ከሆነባት ሰነባብቷል። የአጎዋ እገዳም የዚሁ አካል ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሱ ያሉት የውጭ ጫናዎች በጦርነቱ ምክንያት የተከሰቱ ናቸው።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በቀጠለው ጦርነት ገና ከጅመሩ የነበረው የውጭ ጫና የበረታበት አንዱ ምክንያት በውጭ ሚዲያዎች ስለ ጦርነቱ የሚዘገብበት መንገድ ሲሆን፣ ጉዳዩን የታዛባ ዘገባው መሬት ላይ ያለውን እውነታ የማያሳይ ከመሆኑ ባለፈ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ችግር አጋኖ የሚያሳይ መሆኑ ነው። በዚህም የኢትዮጵያ ወዳጆች እና የቅርብ አጋር አገራት በጦርነቱ ላይ የተሳሳተ ግንዘቤ እንዲኖራቸዉ እስከማድረግ የደረሰ ተጽዕኖ ሚዲያዎቹ እያሳደሩ ነው።

የውጭ ሚዲያዎቸ በኢትዮጵያ አሁን ስላለው ጦርነት የሚያወጧቸው ዘገባዎች፣ ብሎም በኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ አገር ኢምባሲዎች በኢትዮጵያ ያለው ችግር የከፋ መሆኑን በመግለጽ ዜጎቻቸውን ከኢትዮጵያ በአስቸኳይ እንዲወጡ የሚያደርጉበት መንገድ በአገሪቱ ያለውን ችግር በተጋነነ ሁኔታ ለውጭው ዓለም የሚሳይ በመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሣድረው ጫና ቀላል እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የውጭ እና የውስጥ ጫናዎች እንዳሉባት መንግሥት እራሱ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይደመጣል። ብዙዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ችግር የኃይል ጦርነት ብቻ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት የውስጥ እና ውጭ የጦርነት ፕሮፖጋንዳ እና ዲፕሎማሲ ጫናዎችን ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ወቅቱን የጠበቀና በጦርነቱ ምክንያት የሚደርሱበትን ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችል የፕሮፖጋንዳ እና የዲፕሎማሲ ሥራ እንዳልሠራ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ይሰማል።

አሁን ላይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በቀጠለው ጦርነት በተለይ በአሜሪካ በኩል ያለው አረዳድ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ እና የኢትዮጵያን ችግር የሚያባብስ መሆኑ እየተገለጸ ነው። የውጭ ጫናዎቹ የሚበረቱት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ለመሆኑ በባለሙያዎች በኩል እንደ ምክንያት የሚቆጠረው፣ ህወሓት በፕሮፖጋንዳ እና በውጭ ዲፕሎማሲ ብልጫ በመውሰዱ እና ህወሓትን መደገፍ የሚፈልጉ ውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በመኖሩ ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠማት ጦርነት የፕሮፖጋንዳ እና የዲፕሎማሲ ጭምር መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ። የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ሻለቃ ታመነ አባተ “በጦርነት ወቅት ፕሮፖጋንዳ ከጦር መሣሪያ በላይ ጉዳት አለው” ይላሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት፣ አንድ ዓመት በዘለቀው ጦርነት በህወሓት በኩል የሚታየው “የውሸት ፕሮፖጋንዳ” ማኅበረሰቡን መረበሹን እና በውጭው ዓለም የተዛባ አመለካከት መፍጠሩን በመጥቀስ ነው።

የጦርነት ፕሮፖጋንዳ ከማኅበረሰብ እስከ ጦር ሠራዊት የሚዘልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል የሚገልጹት ሻለቃ ታመነ፣ ባለፈው አንድ ዓመት በነበረው ጦርነት በመንግሥት በኩል የፕሮፖጋንዳ እና የዲፕሎማሲ ሥራዎች ወቅቱ የሚፈልገውን ያክል አለመሠራቱን ይጠቅሳሉ። በአንጻሩ በህወሓት በኩል በውስጥም ይሁን በውጭ ቀላል የማይባል የፕሮፐጋንዳ ሥራ መሠራቱን ይጠቁማሉ።

የጦርነቱ የፕሮፖጋንዳና የዲፕሎማሲ አለመመጣጠን የተፈጠረው ህወሓት ኢትዮጵያን በበላይነት በመራባቸው 27 ዓመታት ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ የራሱን ሰዎች ስላሠማራ እና ስለተዘጋጀበት መሆኑን ተናገረዋል። በአንጻሩ በመንግሥት በኩል የታየው ድክመት፣ ያለው ዝግጅት ጊዜ አጭር በመሆኑ ነው ይላሉ።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙት መምህር የሆኑት ዳምጠው ተሰማ(ረ/ፕ) እንደሚሉት፣ ባለፈው አንድ ዓመት በነበረው ጦርነት በመንግሥት በኩል የታየው የዲፕሎማሲ ድክመት በሙያዊነት ላይ የተመሰረት የዲፕሎማሲ ሥራ የሚሰሩ ድፕሎማቶች ባለመኖራቸው የተፈጠረ ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁነታ አንጻር የመደበኛ ጊዜ የዲፕሎማሲ አካሄድ አዋጭ አለመሆኑን ይጠቁማሉ። በመንግሥት በኩል ጦርነት ላይ የታየው የዲፕሎማሲ ሥራ ወቅቱን የሚመጥን እና መሬት ላይ የወረደ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ አለመሆኑን ይገልጻሉ።
ዲፕሎማሲ ወቅቱን የጠበቀ እና በተጠና መንገድ ዝርዝርና ተጨባጭ ሥራዎች መሥራት የሚጠይቅ ነው የሚሉት መምህሩ፣ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅት ለውጭው ማኅበረሰብ ጥሩ ግንዘቤ በሚፈጥርና ሚዛን በሚደፋ መንገድ ያሉትን ነገሮች አጥንቶ የዲፕሎማሲ ሥራውን በአግባቡ ሠርቶ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ የዲፕሎማሲ ሥራ የምትፈልግበት ጊዜ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ጦርነት በኃይል ብቻ አይከወንም የሚሉት ሻለቃ ታመነ በበኩላቸው፣ ለውጭው ማኅበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ የሚነገሩትን የተዛቡ የፕሮፖጋንዳ መረጃዎችን በንቃት ተከታትሎ መመከት እና የተሰራጨውን ፕሮፖጋንዳ ለመመክት የሚያስችል ሥራ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ከዚህ አንጻር በመንግሥት በኩል ክፍተት እንደሚታይ የጠቆሙት ሻለቃ ታመነ፣ ቢቻል ቀድሞ ሥራዎችን መሥራት፣ ባይቻል ደግሞ የሚሰራጩ የውሸት ፕሮፖጋንዳዎችን ማስተባበልና የተሰራጨውን መረጃ ማርከስ የሚችል የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
መንግሥት የተዛባ የፕሮፖጋነዳ መረጃ የሚፈጠረውን የውስጥ እና የውጭ ጫና ለመቋቋም ያልተቋረጠና ንቁ የፕሮፖጋንዳና ዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንዳለበት ሻለቃ ታመነ ጠቁመዋል። በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በያሉበት ስለ ኢትዮጵያ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠትና ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራ በማከናወን የሚደርስውን ጫና መቀነስ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

የፖለቲካ ሳይንስና የውጭ ግንኙነት መምህሩ የሻለቃ ታመነን ሐሳብ በመደገፍ፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ወቀቱን የጠበቀ ትኩስ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በተለያዩ አካላት በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ የውጭ ጫናዎችን በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለያየ መንገድ እያስረዱ ሲሆን፣ የሕዝባዊ ዲፕሎማሲ ማጠናከርና ውጤት ሊያስገኝ በሚችልበት ሁኔታ መምራት እንደሚገባ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ በገጠማት ጦርነት ከውጭ ከሚደርስባት ጫና ባልተናነሰ በፕሮፖጋንዳ መስክ ባለፈው ዓመት ቀላል የማይባል የውስጥ ጫና እንዳጋጠማት ሻለቃ ታመነ ያስታውሳሉ። ህወሓት በሚያሰራጫቸው የፕሮፖጋንዳ መረጃዎች ሕዝብን በማሸበር ከአካባቢውን ለቆ እንዲሸሽ በማድረጉ ጦርነቱ እንዲስፋፋ ገፊ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ህወሓት ወደ አማራ እና ወደ አፋር ክልሎች በስፋት እንዲገባ ዕድል እንደተፈጠረለት የሚገልጹት ሸላቃ ታመነ፣ ህወሓት ጦርነቱን እየገፋ አሁን አለበት ቦታ ላይ የደረሰው የኃይል ብልጫ አግኝቶ አለመሆኑን ጠቁመዋል። ባለፈው አንድ ዓመት ያገጠመውን የፕሮፖጋንዳ ጥፋት አሁንም እንዳይቀጥል ማድረግ እንደሚገባ ባለሙዎቹ ጠቁመዋል።

የውስጥ ፕሮፖጋንዳ ጫናዎችን መቋቋም የሚቻለው በመንግሥት በኩል ያልተቋረጠ መረጃ በተገቢው ሥርዓት፣ ወጥ በሆኑ አሠራር ተደራሽ በማድረግ እና በፕሮፖጋንዳ የሚረበሸን የማኅበረሰብ ክፍል ሥነ ልቦና በማጠንከር መሆኑን ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል።
በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮች በተለይ ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች ማኅበረሰቡ በፕሮፖጋንዳ መረጃ ተረብሾ አካባቢውን ለቆ እንዳይሸሽ የማድረግ እና አስተባብሮ ችግሩን መጋፈጥ እንደሚገባቸው ተመላክቷል።

ጦርነቱ እንዲራዘም እንደ አንድ ምክንያት የሆነው የተዛባ ፕሮፖጋንዳ መሆኑን የሚገልጹት የፖለቲካ ሳይንስና የውጭ ግንኙነት መምህሩ፣ መንግሥት ፕሮፓጋንዳውን ከመመከት በተጨማሪ፣ ከውጭ አገራት የሚመጣውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንዳለበት ጠቁመዋል። በጦርነት ፕሮፖጋንዳና ዲፕሎማሲ በመንግሥት ላይ የሚደርሰው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ከመምጣት ውጭ መንግሥት በወሰዳቸው በጎ ዕርምጃዎች ጫናውን መቀልበስ ስላልተቻለ፣ አዋጪው መንገድ የሚመጣውን ጫና ተቋቁሞ ጦርነቱን ባልተራዘመ ጊዜ ማጠናቀቅ መሆኑን ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 159 ሕዳር 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here