በኢትዮጵያ የውዛዋዜ ወይም የዳንስ ጥበብ ውስጥ ሥማቸው ጎልቶ የሚነሳ ባለሙያዎች ጥቂት ናቸው። ከነዛ መካከል ደግሞ በጣት ቁጥር የማይሞሉት ጥበቡን በጥልቅ ተመራምረውታል። ከእነዚህ ጥቂት ሰዎች መካከል ነው፤ ሽፈራው ታሪኩ ቢረጋ። ከአንድ ወር ገደማ በፊት ነበር ‹ያልታደለው ጥበብ› የተሰኘ የዳንስ ጥበብን የተመለከተ የመጀመሪያ መጽሐፉን ለአንባብያን ያደረሰው።
ሽፈራው ‹እንቅስቃሴዎች ኹሉ ዳንስ ናቸው› የሚለው ነጥብ አይዋጥለትም። ‹‹ጥበብ በባህሪው ያመራምራል፤ ያዝናናል፤ ያስተምራል፣ ጥያቄ ፈጥሮ ተገቢ መልስ እንድንሰጥና አስፍተን እንድናይ ያደርጋል። ኹሉም እንቅስቃሴ ዳንስ ከሆነ ጥበብ አይሆንም። እንቅስቃሴዎችን ኹሉ ግን ዳንስ ማድረግ ይቻላል። ለዛም የራሱ የሆነ ቀመር አለው። ቅርጽ፣ ሥልተ-ምት እና ስሜት የሚባል ነገር አለ›› ሲል ያስረዳል።
ሆኖም አብዛኛው የአገራችን ማኅበረሰብ፣ አልፎም ባለሙያ ነኝ የሚለው ይህን ጉዳይ አልተረዳውም ባይ ነው። ብዙዎችም ጋር የዳንስ ጥበብን በተመለከተ በደመነ ነፍስ መጓዝ እንደሚታይ ያመላክታል። በተረፈ የዳንስ ጥበብ ከሺሕ ቃላት በላይ በተወሰኑ እንቅስቃሴዎች ብዙ መግለጽ የሚያስችል አቅምን እንደሚፈጥር ሽፈራው በልበ ሙሉነት ይናገራል። ከዚህ በተቃራኒ ሙያው እንደ ተራ ጉዳይ ሲታይ ግን እንደባለሙያ ቅር እንደሚሰኝ ነው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ያነሳው።
ማለዳ የተጀመረ ትግልና ጥበብ
ሽፈራው በልጅነቱ ነው ወላጆቹን ያጣው። በዚህ የተነሳ ከእንጀራ እናቱ ጋር እንዲያድግ ሆኗል። ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩት እንጀራ እናቱ ኑሮን ለማሸነፍ የሚሸጡት ጠላ ብቻውን አላገዛቸውም። ስለዚህም ሽፈራው በልጅነት ዕድሜው የኪስ ወረቀት እየሠራ በመሸጥ ቢያንስ የራሱን የምግብ፣ የልብስ እና የትምህርት ቤት ወጪ ለመሸፈን ጥረት ያደርግ ነበር።
‹‹በሕይወት የሚመጡ ውጣ ውረዶችን በልጅነቴ ነው መጋፈጥ የጀመርኩት። በስምንት ዓመቴ ጦር ኃይሎች ጀርባ ሰው ቤት ተቀጥሬ ከብቶችም እየጠበቅኩ ለአራት ዓመት ሠርቻለሁ›› ይላል። በሰው ቤት ተቀጥሮ መሥራት ከባድ እንደመሆኑ 12 ዓመት ሲሆነው ወደ ኪስ ወረቀት ሥራው ተመልሷል።
‹‹ያኔ ሰፈር ውስጥ መማር የምትፈልጉ ተመዝገቡ ተባለ። በጣም በደስታ ተመዘገብኩ። መምህራኑ ነጮች ነበሩ ተባልን። በኋላ ሲነገረን ትምህርቱ የዳንስ ጥበብ ትምህርት ነበር። ምን እንደሆነ ሳናውቅ ገባን፤ አድርጉ የሚሉንን እናደርጋለን›› ይላል፣ መለስ ብሎ ከዳንስ ጥበብ ጋር የተዋወቀበትን የልጅነት ዕድሜ ሲያስታውስ።
በዚህ መሠረት በተጀመረ ሥልጠና የተሳተፈው ትንሹ ሽፈራው ሳያቋርጥ ቀጠለ። የውጪ ዜጎች የነበሩት አሠልጣኞችም ወደየመጡበት ሔደው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ፣ ሽፈራውና ጓደኞቹ ሳይበተኑ ጠበቋቸው። በኋላም ካሉት ልጆች መካከል 18፣ ቀጥሎም ስድስት ልጆች ተመርጠው በእንግሊዝ አገር ከሚገኝ ‹ዳንስ ዩናይትድ› ከተሰኘ ድርጅት ጋር በትብብር ለአምስት ዓመት የዘለቀ ጠንካራ ሥልጠና አግኝተው ተመረቁ።
እነዚህ አጋጣሚዎች ሽፈራው ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ እንዲገኝ መነሻ የሆኑ ናቸው። ከዚህም በኋላ ሽፈራው ባገኘው ልምድና ዕውቀት ገፍቶ ለ11 ዓመት ‹አዱኛ ማኅበረሰባዊ የዳንስና የቴአትር ድርጅት› ጋር በአሠልጣኝነትና መምህርነት አብሮ ሠርቷል። ቀጥሎም ከዘጠኝ ዓመት ገደማ በፊት ራሱን ችሎ መሥራት ጀመረ።
የዳንስ ጥበብ የሚማሩበት ነው ወይስ በተፈጥሮ የሚታደሉት ስንል ጠይቀነዋል። እርሱም በኹለቱም ነው ይላል። ‹‹እኔ በእርግጥ ተምሬው ነው። ግን ለዳንስ ነው የተወለድከውና የተፈጠርከው የሚሉኝ አሉ። በአጭር ጊዜ ሠልጥኜና ተዋህደውኝ የሠራኋቸው ሥራዎች አሉ›› ይላል።
የዳንስ ጥበብ በኢትዮጵያ?
‹‹የዳንስ ጥበብ ተገቢውን ክብር አላገኘም፤ ባለሙያውም ሆነ ማኅበረሰቡ አልተረዳውም›› የሚለው ሽፈራው፣ ዕድገቱም በዚህ ላይ የሚወሰን እንደሆነ ያስረዳል። ታድያ ባለብዙ ባህል ባለቤት በሆነችው በኢትዮጵያ፣ የዳንስ ጥበብ ተገቢውን ክብር እንዳያገኝ ያደረገው ዘመናዊው ሲመጣ ነው ወይስ የቀድሞውም ባህላዊ ውዝዋዜ በዚህ መልክ ይዳኛል?
በዳንስ ጥበብ ሥራ ውስጥ ለ24 ዓመት የቆየው ሽፈራው፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንዳላየ ይናገራል። ‹‹ይህን ያህል እንዴት ለውጥ አልመጣበትም ሲባል፣ የሚገባው አካል ተገቢ ትኩረት ስላልሰጠው ነው›› ይላል።
በግሉ ይህን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አሰናድቶ ለሚመለከታቸው ላላቸው ኹሉ ጠቁሟል። ቢሆንም እንዳሰበው ብዙው የተሳካ አልነበረም። እንደውም ባለፈው ዓመት 2013 አገር ፍቅር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ያስገባቸው የዕቅድ ሥራዎች ጥሩ ግብረ መልስ ማግኘታቸውን አስታውቋል።
‹‹ሙያው እንዲህ የሚጻፍ አይመስለኝም ነበር ያለኝ ሰው አለ። በሙያው ያሉ ሰዎች ያልተማሩ እንደሆኑ ያስባሉና ቅቡልነቱ አናሳ ነው። እንዲህ ፕሮጀክት ሲሰጥ ትጽፋላችሁ እንዴ የሚሉን ሰዎች ትክክል ናቸው። እኛው ነን ሙያውን ማስከበር ያለብንና›› ይላል ሽፈራው። እናም የኢትዮጵያ የባህል ውዝዋዜዎች ክትትል የሚፈልጉ ሆነው ክትትል ያላገኙ በመሆኑ፣ እንኳንና ‹ዘመናዊ› የተባለው የዳንስ ጥበብ ከውጪ አገር መጥቶ፣ አስቀድሞም በራሳቸው እንዲያድጉ ዕድል እንዳላገኙ ነው ያነሳው።
አሁን ላይ የተለያዩ የሙዚቃ ቪድዮዎች ላይ የሚታዩ ውዝዋዜዎች ከውጪ በቀጥታ የተቀዱ ናቸው። ሽፈራው ይህን ከዳንስ ጥበብ ዕድገት ጋር አያይዞ ሲያነሳ፣ ፈጠራ ያለንን ነገር መጣል ማለት አይደለም አለ። ‹ይህን ዳንስ ከየት አመጣችሁ?› ቢባል የማያውቁት ብዙ አሉ። የዳንስ ጥበብ አንድ አይነት ትርጉም ብቻ ይዞ መሄድ የለበትም፤ ዕይታን የሚያሰፋና የሚጠቁም መሆን አለበትም ብሏል።
አክሎም አለ፤ ‹‹የዳንስ ጥበብ የአንቺነት መገለጫ ነው። ከአፍሪካ በተለይ ሴኔጋል ደጋግሜ ሔጃለሁ። በዛም ከሕጻን እስከ አዋቂ ይደንሳሉ። ሕጻናት ላይገባቸው ይችላል ግን እንዲገባቸው ሲታገሉና ሲደንሱ ዐይቻለሁ። እዚህ እንደዛ የለም። እኛ አገር ከከተማ እንደውም ገጠር ላይ በተለያየ ማኅበራዊ ክስተት የተነሳ ውዝዋዜ ይቀርባል። ግን ለምን እንደ አንድ ክዋኔ ወቅት እየጠበቅን የምናደረገው አይሆንም ብዬ አስባለሁ።››
‹ያልታደለው ጥበብ› ምን ይዟል?
‹ያልታደለው ጥበብ› የሽፈራው አዲስ መጽሐፍ ነው። በዚህ መጽሐፍ መንገዱን ነው ያሳየሁት ይላል ሽፈራው። የመጽሐፉ ጽንሰት በመምህርነት ዘመኑ የጀመረ ነው። ከልጅነት ጀምሮ ባገኘው ሥልጠና ውስጥ የዳንስ ጥበብን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ጥበቡን እንዴት ማስተማር እንደሚቻል መማሩን ያወሳል።
ታድያ በልምድ የሚሰጠው ትምህርት ቀርቶ መስመር እንዲይዝ ለማስቻል በተለያየ ጊዜ ለመማር ማስተማር የሚረዱ ነጥቦችን እየጻፈ ይጠቀም ነበር። በዛ መሠረት መሄድ የሚከብደው ተማሪ ሲገጥመው ደግሞ የተማሪውን አቅምና ፍላጎት መሠረት አድርጎ አዲስ ስልት ያዘጋጃል። በዚህ መሠረት በወጣት ማዕከላት፣ ከተለያዩ መንግሥታዊ እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዳንስ እና ‹ኮንቴምፖረሪ› አስተምሯል።
ታድያ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዳንስ ጥበብን ለማስተማር ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ፣ ሐሳቡን በጽሑፍ እንዲያቀርብ ይጠየቃል። ለማስተማሪያነት ያሰበውን መንገድም በጽሑፍ መልክ ያቀርባል። ይህም ነው በየዩኒቨርስቲው ጎራ ሲል፣ ሲሻሻልና ሲዳብር ቆይቶ ‹ያልታደለው ጥበብ› መጽሐፍን የወለደው። ሽፈራው አሁን ላይ የቴአትር ጥበብን በሚያስተምሩ ዩኒቨርስቲዎች ‹የዳንስ መሠረታውያን› (Basics of Dance) የተሰኘ የትምህርት ዓይነት ይሰጣል። ከአገር ውጪም በተጋባዥነት ያሠለጥናል፤ ያስተምራል።
‹‹ያልታደለ ጥበብ መጽሐፍ እንደ ማስተማሪያ ሊያገለግል ይችላል። በተረዳሁት ብቻ ላለማፍሰስ አንኳሩን ነው ያስቀመጥኩት። መጽሐፉ ከዚህ በላይ ሊጻፍበትና መነሻ ሊሆን የሚችል ነው። ማስተማሪያም ይሆናል፤ መረጃም አለው›› እንደ ሽፈራው ገለጻ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ መጽሐፉ አሁን ላይ በጃፋር፣ ሀሁ፣ ሰአዳ እና ኮሜርስ መጽሐፍት መደብር ለአንባብያን ቀርቦ ይገኛል። መጽሐፉ ለአንባብያን እንዲደርስ የኅትመቱን ሙሉ ወጪ የሸፈነለትን አርቲስት አበበ ባልቻን፣ የምርቃቱን ወጪ የሸፈነለትንም ደመላሽ ብርሃኑ አብዝቶ አመሥግኗል። ይህ ለዳንስ ጥበብ ከሙያው ውጪ የሆኑ ሰዎች ያደረጉት አስተዋጽኦ አረአያ ሊሆን እንደሚችልም አንስቷል።
ምን ይደረግ?
የዳንስ ጥበብ ላይ በጉልህ የሚታዩ ልዩነቶች አሉ። በአንድ ወገን ተመልካቹ ጥበቡን የሚረዳበት መንገድ ሲሆን ሌላው ‹ባለሙያው› ጥበቡን የሚያቀርብበት መንገድ ነው። ከውጪ አገራት ተቀድተው በግልባጭ መጥተው በየሙዚቃ ቪድዮው የሚታዩ ዳንሶች ብዙዎች ለዳንስ የሚሰጡትን ግምት እንዲያወርዱ አድርጓል። በአንጻሩ በጥንቃቄ ተጠብበው የሚሠሩ የዳንስ እንቅስቃሴዎች ተመልካቹ ግራ በመጋባት ሊመለከታቸው ይችላል።
ይህ ተጣጥሞ እንዲሄድ የተመልካችና የዳንሰኛው ግንዛቤ ሊያድግ እንደሚገባ ሽፈራው ያሳስባል። ‹ሳትሰጪ አምጡ የለም። ስለጥበቡ ሳትናገሪ ተመልከቱልን ማለት አይቻልም›› ያለው ሽፈራው፣ ለዚህም በጉዳዩ ላይ መጻሕፍት መዘጋጀታቸው ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ይጠቅሳል። ወደፊትም በመንግሥት ባለድርሻዎች በኩል ፈቃድና ይሁንታ አግኝቶ አንድ ተቋም ቢመሠረት ምኞቱ ነው።
ያም ብቻ ሳይሆን ጥበቡን እየበደሉ መጠቀሚያ ያደረጉት ባለሙያዎች ነቅተው፣ ከራሳቸው ይልቅ ለጥበቡ መከበርና ዕድገት እንዲተጉ ይመኛል። በተጓዳኝ የጥበቡ ባለሙያ ነን የሚሉ ሰዎችም ተገቢውን ስፍራ የሰጡ እንዳይደሉ ያነሳል። ‹ከውጪ አገር የሙዚቃ ቪድዮ ቀድቶ የሚሠራን ሰው ጥበበኛ ብዬ ለመጥራት አልደፍርም›› ይላል።
አክሎም እንዲህ አለ፤ ‹‹ብዙ የሥራ ባልደረቦቼ ታዋቂ ናቸው፤ ሽፈራው ለምን ታዋቂ መሆን አልቻልክም ይሉኛል። በአገራችን ታዋቂ መሆን በጣም ቀላል ነው። ሚድያውም እየፈለፈለ እያገኘ ያመጣቸዋል። ለእኔ ኹለት ነገር አለ። ታዋቂ መሆን ሌላ ነው፣ ታዋቂ ባደረገኝ ጥበብ ላይ አዋቂ መሆን ሌላ ነው። ብዙ ታዋቂ አለ፤ አዋቂው ጥቂት ነው። መጽሐፍ ስለሰጠሁ አዋቂ ነኝ እያልኩኝ አይደለም። ግን ሁላችን ብንመራመርና አዋቂ ለመሆን ብንጥር አብዝተን በጥልቀት ብዙ ልናመጣና ለማኅበረሰቡም ይሁን ለአገራችንና ለዓለም ልናበረክት የምንችለው ብዙ አለ።››
የሕይወት መመሪያ
የሽፈራው በሕይወቱ ማንኛውም ነገር ሲከሰት ለምን መጣ አይልም፣ መፍትሄ ወደመፈለጉ አዘነብባለሁ ይላል። ጊዜውን ለሚያጠፋበት ነገርም ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ማንኛውምን ጊዜ የሰጠሁትን ሥራ በቁምነገርና ሙሉ ትኩረቴን ሰጥቼ ነው የምሠራው ሲል ይናገራል።
‹‹በልጅነቴ ክፉና ደጉን ማየቴና ራሴን ለማሸነፍ የሄድኩባቸው መንገዶች በሕይወት አጠንክረውኛል። ሽፈራው ጠንካራ መሆን ካለበት በራሱና በራሱ ብቻ ነው። እዚህ ስደርስ የሚደግፉኝ ቤተሰቦችና ዘመዶች አልነበሩም። ጥንካሬን ከልጅነት ነው ያገኘሁት›› ሽፈራው እንዳለው ነው።
‹ኔቨር ጎ ባክ› የሚል አንድ ሥራ አለው። ይህን የሠራው ሴት ልጁ ገና ዓለምን እንደተቀላቀለች ለሥራ ጉዳይ ወደ ውጪ መሄድ ግድ በሆነበት ሰዓት የተሰማውን ስሜት ለመግለጽ ነው። ይህ ሥራው በተደጋጋሚ የሠራውና የሚወደው ሥራ መሆኑን ይጠቅሳል። ልጁ 13 ዓመቷን የካቲት ላይ ስትደፍን ይህ ሥራውም አብሮ 13 ዓመቱን ይይዛል።
ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014