በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከሱዳን አጎራባች አካባቢዎች ሠርገው የሚገቡ ታጣቂ ኃይሎች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ እና በሱዳን አጎራባች አካባቢዎች አልፎ አልፎ ሠርገው እየገቡ ጥቃት እየፈጸሙ ነው የተባሉት ታጣቂዎች፣ እስካሁን ጥቃት የፈጸሙት በአሶሳ ዞን ሸርቆሌ ወረዳ እና በመተከል ዞን ጉዳ ወረዳ ባሉ አካባቢዎች መሆኑን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እና በሱዳን አጎራባች ድንበሮችን ጥሰው የሚገቡ ሠርጎ ገብ ታጣቂ ኃይሎች የሚደርጉት ሙከራ እየተበራከተ ነው ተብሏል። ሠርጎ ገቦቹ የሚደርጉት ሙከራ ተደጋጋሚ ቢሆንም፣ በአካባቢው የተሠማራው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ሙከራቸውን እያከሸፈው መሆኑን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።
ሠርጎ ገቦች ወደ ክልሉ ለመግባት በሚሞክሩባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ክትትል እያደረገ መሆኑን የሚገልጹት የአካበቢው ነዋሪዎች፣ አልፎ አልፎ ድንገት ብቅ እያሉ ጥቃት እያደረሱ ነው ብለዋል። ሠርጎ ገብ ታጣቂቆቹ ጥቃት የሚያደርሱት “ተሹለክልከው እየገቡ ነው” የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ የጸጥታ አካላት በአካባቢው የሚያደርጉትን ክትትል እና የሚወስዱትን የማጥቃት ዕርምጃ አጠናክረው ከቀጠሉ አልፎ አልፎ የሚያደርሱትን ጥቃት ማስቆም እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ችግሩ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥጋት እየፈጠረ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረባቸው ሥጋት መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንደተስተጓጎለ ተናግረዋል። በዚህም ከስጋት ነፃ ሆነው ከቦታ ቦታ እንደማይንቀሳቀሱ ገልጸዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ በሱዳን እና በክልሉ አጎራባች አካባቢዎች ታጣቂዎች ሠርገው መግባት የጀመሩት አሁን አይደልም ይላሉ። አሁን ላይ ተጠናክሮ ቀጠለ እንጂ በክልሉ ታጣቂ ኃይሎች ጥቃት መፈጸም የጀመሩት ከዓመታት በፊት ነው ብለዋል።
በክልሉ፣ በተለይም በመተከል እና በካማሺ ዞኖች ለዓመታት በዘለቀው የታጣቂዎች ጥቃት እና እረብሻ ላይ የሚሳተፉ አካላት፣ አጎራባች አካባቢዎችን እንደ መውጫ እና መግቢያ እንደሚጠቀሙባቸው ይገለጽ ነበር።
ባሳለፍነው ሳምንት በክልሉ አጎራባች አካባቢዎች ሠርገው የገቡ የህወሓት ተላላኪዎች ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን እና መማረካቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን መግለጹ የሚታወስ ነው።
ሰሞኑን ዕርምጃ የተወሰደባቸውና በቁጥጥር ሥር የዋሉት የሽብር ቡድን አባላት፣ በክልሉ ጠረፋማ አካባቢ በሆነው አሶሳ ዞን ኩርሙክ፣ ሸርቆሌ እና መንጌ ወረዳዎች የገቡ መሆናቸውን ኢዜአ መዘገቡ የሚታወስ ነው። በጸጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር የዋሉት ታጣቂዎች የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ይዘው ተገኝተዋል።
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ታጣቂዎች ይዘው የተገኙት የጦር መሣሪያ፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች ከመሰል ተተኳሽ ጥይቶች፣ ፀረ-ሰው እና ተሸከርካሪ ፈንጂዎች፣ የእጅ ቦምቦች፣ መገናኛ ሬዲዮኖች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችና የጦር ሜዳ መነጽሮችም ይገኙበታል። ታጣቂዎቹ መነሻቸው ካደረጓት ሱዳን የሱዳን ፓውንድ፣ የሱዳን ጦር ዩኒፎርሞች ይዘው ተገኝተዋል መባሉ የሚታወስ ነው።
ሠርገው ከገቡት ታጣቂዎች መካከል በሱዳን ሥልጠና ወስደው ወደ ክልሉ የገቡና እራሱን “ቤህነን” ብሎ የሚጠራውን ቡድን ዓርማ የያዙ እንደሚገኙበትም የተገለጸ ሲሆን፣ የተደመሰሱ የጥፋት ተላላኪዎች ትኩረት ያደረጉት ንጹኃንን ማጥቃት ላይ ነው ተብሏል።
በክልሉ ሠርገው የሚገቡ ታጣቂዎችን ከአካባቢው ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ሕብረተሰቡ ተቀናጅተው እየሠሩ መሆናቸውም ተጠቁሟሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014



