“እኛ መርዶ ነጋሪ ፖለቲከኞች አይደለንም”

0
965

ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር ናቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክና በኢኮኖሚክስ በተናጠል የያዙ ሲሆን፣ በተቀናጀ የውሃ ተፋሰስ ልማት የኹለተኛ ዲግሪያቸውን በውሃ ማኔጅመንት በተለይ የጥናታቸው ትኩረት ‘ሃይድሮሎጂ’ እና ‘ኢሮዥን’ ላይ በማድረግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሠርተዋል። በሥራው ዓለም በአጠቃላይ የዐሥር ዓመታት ልምድ ያላቸው ደሳለኝ፥ በአደጋና መከላከልና ጥናት ተቋም በምክትል ዳይሬክትርነት ያገለገሉ ሲሆን፥ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተመራማሪነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

የቀጥታ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ ያልነበራቸው ደሳለኝ፤ አብን ከመመሥረቱ በፊት አማራ ሕዝብ ላይ የነበረው በደል ቁጭት ከሌሎች የአማራ የመብት ተሟጋቾች ጋር ያደርጉት የነበረውና ለአንድ ዓመት የዘለቀ የማኅበራዊ ትሥሥር ውይይት፥ ‘ምን ማድረግ ይሻላል?’ ወደሚል ጥያቄ ከፍ ማለቱ ለአብን መወለድ ሰበብ መሆኑን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ዋና መሥሪያ ቤቱን አዲስ አበባ ያደረገው አብን በአማራ፣ በቤኔሻንጉ ጉሙዝ፣ በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች በአጠቃላይ 125 ቢሮዎች ከፍቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፤ በቅርቡም በድሬዳዋ እና በሐረር ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ለመክፍት በዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አሉን የሚሉት ሊቀ መንበሩ፥ 300 ሺሕ የተመዘገቡ አባለት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።

የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከደሳለኝ ጋር በአብን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፦ ባለፈው ቅዳሜ፣ ጥር 25 ‘ዳያሎግ ኦን ኢትዮጵያ’ በሚል ርዕስ በዩኤን፣ ኢሲኤ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ያላችሁ ቅሬታ ምንድን ነው?
ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፦ አንደኛው ቅሬታችን በመድረኩ ላይ በአቅራቢነትና በሐሳብ አመንጪነት የተሳተፉት ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብዙዎቹ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩና የችግሩ አካል የነበሩ ሰዎች ናቸው። ሃምሳ ዓመት ፖለቲካ ውስጥ የኖረ አንድ ሰው ስኬታማ ካልሆነ ‘ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መፍትሔ ላምጣ፣ የመፍትሔው አካል ልሁን’ የሚለውን እኔ በግሌ አልቀበለውም። ቅሬታችን የወጣቱ ትውልድና እሳቤ በዚህ መድረክ ላይ በትክክል አልተወከለም በሚል ነው።

ኹለተኛው ከአቅራቢዎቹ ውስጥ በሚገርም ሁኔታ አንድም አማራ አልነበረም። አሁን ባለው ሁኔታ አማራነትና እና በአማራነት መደራጀት አለብን ብሎ አዲስ ሐሳብ ይዘው የመጡ እንደ አብን ዓይነት ድርጅቶች አሉ። ይሁንና በአቅራቢነት የተሳተፉት የፖለቲካ ኃይሎች ብዙዎቹ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ባለፉት ዓመታት ሕገ መንግሥቱን በመቅረፅ፣ በማፅደቅና የአማራ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጠላት ነው ብለው የፈረጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አባልና አመራር የሆኑ ሰዎች ናቸው። እነ ዶ/ር አረጋዊ በርሔን ብትወስድ በግልጽ በሕወሓት ማኒፌስቶ ‘አማራ ማለት ጠላት ነው፤ አከርካሪው መሰበር አለበት’ ብለው የተናገሩ ሰዎች ናቸው።

ስለዚህ በዚህ ዓይነት ሁኔታ እነዚህ ሰዎች በተሳተፉበት መድረክ ላይ ቢያንስ የተለያየ ትረካ፣ የታሪክ ንባብና አረዳድ ሊያቀርብ የሚችል የአማራ ድምፅ መኖር መቻል አለበት። ልክ ባለፉት ዓመታት ሲደረግ እንደነበረው ሁሉ የአማራን ሕዝብ የመግፋትና የማግለል ዓይነት ሒደት አሁንም ሊደገም ይችላል የሚል ስጋት አለን።

በርግጥ ይሔ የሐሳብ ሙግት የሚቀርብበት ‘ወርክሾፕ’ ነው፤ በሐሳብ ሙግትም ውስጥ ግን ሁሉም ሐሳቦችና አመለካከቶች መንፀበረቅ አለባቸው ብለን ስለምናምን ይህን ቅሬታ አንስተናል።

 

አዴፓ አማራን ጨቋኝ ብሎ ከተነሱ ሕዝቦች ጋር የፖለቲካ ሥራ እየሠራ፣ ግንባር ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ ያለ ድርጅት ነው

 

አንዳንዶች አብን በብሔርተኝነት ላይ የተደራጀው የተለየ ሊያሽንፍበት የሚችልበት ርዕዮተ ዓለም ስለሌው ነው ይላሉ። ለምንድን ነው በርዕዮተ ዓለም ያልተደራጃችሁት?
አንደኛ ጥያቄው በመሠረቱ ስህተት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የእነ ዶ/ር ዐቢይ ፓርቲ የብሔር ድርጅት ነው፤ ግን ርዕዮተ ዓለም የለውም ማለት አይደለም። የእነ ዶ/ር መረራ ፓርቲ የብሔር ድርጅት ነው። ኢትዮጵያን ላለፉት 27 ዓመታት ሲመሩ የነበሩ ሁሉም የብሔር ድርጅቶች ናቸው። የብሔር ድርጅት አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል ፀረ አማራ ርዕዮት ነበራቸው። ስለዚህ የብሔር ድርጅቶች ርዕዮት የላቸውም የሚለው ስህተት ነው።

እኛም በፕሮግራማችን ላይ ያስቀመጥነው ብዙ ሙግት ያደረግንበት ለዘብተኛ ሊበራሊዝም የሚባለውን ርዕዮተ ዓለም ነው። አንድ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የማየው ችግር ሁሉም በብሔሩ ተደራጅቷል፤ አማራ ልደራጅ ሲል የሚኮነንበትና ለሌሎቹ ፅድቅ የሚሆኑበት ሁኔታ ከየት እንደሚመነጭ አይገባኝም።

ስለዚህ የአማራ ሕዝብ ሌሎች በብሔር ስለተደራጁ ብቻ ሳይሆን፥ አማራ ስለሆነ ብቻ በገጠመው የኅልውና ፈተናዎች አሉ። እነሱን ለማስመለስ ደግሞ በዜግነት ድርጅቶች ውስጥ ተሳተፈን ባለፉት ብዙ ዓመታት ዋጋ ከፍለን አይተነዋል። እንኳን ጥያቄዎቻችንን ማስመለስ፣ ጥያቄዎቻችንን የሚያዳምጡበት ዕድል ስላላገኘን ያንን መቀልበስ የምንችለውና አዋጪ ወይም አሸናፊ ሊያደርገን የሚችል የፖለቲካ አሰላለፍ በአማራነታችን መደራጀት መሆኑን ስላመንን፥ ሰፊ ትንታኔ ተሠርቶበት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መርምርን የደረስንበት ነው እንጂ እንዲሁ በሩጫ ወይም ደግሞ ምንም ርዕዮተ ዓለም ስለሌለን ወይም የምንታገልለት ሐሳብ ስለሌለን አይደለም። አንድ ሺሕ የአማራ ጥያቄዎች አሉ፣ አብን ቀርቶ ሌሎች ድርጅቶችንም ሊያታግሉ የሚችሉ ማለት ነው።

አብን ሕወሓትን በማውገዝ፣ በደሎችን በማጦዝ፣ ብሶትን በማጎን ቆዛሚ ትውልድ ከመፍጠር ይልቅ ሕዝብን በማንቃት የችግር መውጫ መፍትሔ ላይ ትኩረት ቢያደርግ የተሻለ ነው ብለው ለሚተቿችሁ ምላሻችሁ ምንድን ነው?
አንደኛ እንደዚህ ብለው የሚተቹ ሰዎች የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ለማቃለል የሚፈልጉ ዓይነት ሰዎች ይመስሉኛል። እኛ የመርዶ ነጋሪ ወይም የዋይታ ፖለቲከኞች አይደለንም። ለሕዝባችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮቹን በደንብ ነቅሰን ለእነሱ ደግሞ መፍትሔዎቹን በፕሮግራማችን ላይ አስቀምጠናል፤ ዲዛይን እያደረግናቸው ያሉ ፖሊሲዎቻችንም ላይ በግልጽ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መፍትሔ ይዞ የመጣ ድርጅት ነው።

ይህን ያስባለን ደግሞ ባለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የተተከለውን አማራ ጠል ፖለቲካ ማንሳት የለብንም፣ መተቸት የለብንም እና በሕዝባችንም ላይ የደረሰውን ማሳየት የለብንም በማለት አይደለም። ስለዚህ እነዚህን ችግሮችና በሕዝባችን ላይ ጥፋት ያደረሱ ቡድኖች የሠሩትን ሥራ በግልጽ ሕዝባችን ማወቅ አለበት። ይህንን አውቆ ደግሞ የመረረ ትግል እንዲያደርግ ማስተማርና መቀስቀስ መቻል አለብን። እንኳን በተጨባጭ በሕዝባችን ላይ ደርሶ በፈጠራ ትርክት ሕዝባቸውን ‘እንዲህ ተደርገሃል፣ እንዲህ ተበድለሃል፣ እንዲህ ሞተሃል’ እያሉ የፖለቲካ ማደራጃ አድርገውት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶች ነበሩ፤ ዛሬም አሉ።

እኛ ግን የሕዝባችንን ብሶት፣ ችግር፣ ቁስል ከማከክ የዘለለ የአማራ ሕዝብ ባለፉት ዓመታት ፍትሓዊ የልማት ተጠቃሚነት ችግር አለበት፤ በግልጽ ተራ አማራነት እና አማራ ጠልነት ኢትዮጵያ ውስጥ አለ። እነዚህን ተራ አማራነትና እና አማራ ጠልነትን ታግለን በመቀየር የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ አንደኛ ደረጃ ዜግነት [አግኝቶ]፥ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር እኩል ተወዳድሮ የሚኖርባት አገር ለመፍጠር እሱን መሥራት አለብን ብለን ፖለቲካ እየሠራን ያለን ድርጅት ነን።

ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ጋር ግልጽ የሆነ ልዩነታችሁ ምንድን ነው? ሥልጣን ብትይዙስ ለአማራ ሕዝብ ከአዴፓ በተለየ ልትሰጡት የምትፈልጉት ነገር ምንድን ነው?
አንደኛ አዴፓ ከሚባለው ጋር ያለንን የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ብቻ ላንሳ፤ አዴፓ የሚከተለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል አማራን በጨቋኝነቱ የሚፈርጅ የፖለቲካ ትርክት የያዘ ርዕዮተ ዓለም ነው። አዴፓ አማራን ጨቋኝ ብሎ ከተነሱ ሕዝቦች ጋር የፖለቲካ ሥራ እየሠራ፣ ግንባር ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ ያለ ድርጅት ነው። ስለዚህ ሕዝባችንን ጠላት ብሎ የቆመ የፖለቲካ ቡድንና የሕዝባችንን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት የተነሳ ቡድን ከአነሳሱ፣ ከፅንሰ ሐሳቡ ጀምሮ በብዙ ነገር እንለያያለን።
ሌላው አዴፓ ላለፉት 27 ዓመታት በተግባር ተፈትኖ የወደቀ የሕዝባችንን መሠረታዊ የሚባሉ የኅልውና፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደማይችል የተረጋገጠ ስለሆነ በብዙ ነገር ከአዴፓ የተሻልን አማራጭ ነን ብለን እናስባለን።

የአብን ደጋፊዎች የአንድነት የፖለቲካ ኃይሉ የሐሳብ ገበያው ላይ ተሠማርቶ እንዳይሠራ ጫና ይፈጥራሉ፤ ኃይል ተጠቅመው እንዲቋረጥ ያደርጋሉ ይባላል። በነጻነት ሕዝቡ የሐሳብ ገበያ ያለውን አማራጭ አይቶ እንዲወስን ማድረግ አይሻልም?
ስህትት ነው! ኃይል ተጠቀመ ተብሎ በማስረጃ የተደገፈና ሕጋዊ መረጃ ስለሌለ በዚህ ላይ ምንም አስተያየት መስጠት አያስፈልግም። ዝም ብሎ ባለፉት ሰባት እና ስምንት ወራት አብን ፈጣን የፖለቲካ ሥራ ሲሠራና ሕዝቡን ማነቃቃት ሲጀምር አማራ ሕዝብ ላይ ድጋፍ እናገኛለን ብለው አስበው የነበሩ ድርጅቶች ምንም የፖለቲካ ሥራ ሳይሠሩ ቁጭ ብለው አብንን የመወንጀል ተግባር ውስጥ ለመሠማራት ያደረጉት ነገር እንጂ እኛ ሕዝባችን ከመረጠው ምንም ሐሳብ ሊሆን ይችላል፣ ማንም የፖለቲካ ቡድን ሊሆን ይችላል፣ ምንም ዓይነት አመለካከት ያለው ድርጅት ሊሆን ይችላል በክልላችን ውሎ ማደር፣ የፖለቲካ ሥራ መሥራትና ሰሚ ካገኘም መንቀሳቀስና ማደራጀት ይችላል። ክሱ በጣም አስቂኝ ክስ ነው።

ከሌሎች ብሔርን ከሚያቀነቅኑ ድርጅቶች ጋር ግንባር ፈጥሮ የመሥራት ሁኔታችሁ እንዴት ነው? ፖለቲካ በአብዛኛው በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ ስለሆነ አብን ምን ይሰጣል? ምን ይቀበላል?
ከብሔር ድርጅቶች ጋር ብቻ ሳይሆን አገራዊ የዜግነት ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የጀመርናቸው ንግግሮች አሉ።

ምሳሌ ቢጠቅሱልኝ?
እነሱን በሒደት ውጤታቸው ሲያልቅ ለሕዝባችን ይፋ የምናደርጋቸው ይሆናል።
የአማራ ሕዝብ ጥቅምና የኢትዮጵያን አንድነት መሠረት አድርገን ከሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች እና ኃይሎች ጋር ፖለቲካ እንሠራልን፤ የምንሠራውም የፖለቲካ ዕድገቱ ወዴት ያመራል የሚለው ነገር በሒደት የሚታይ ይሆናል። ግንባር መፍጠር፣ በጋራ መሥራት እስከ ውሕደት የሚያደርስ ሁኔታ ካለና የሕዝባችንን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሆኖ ካገኘነው ምንም ችግር የለውም።

በሰጥቶ መቀበል ሒደትም ስርዓት ባለው መንገድ ተደራድሮ፥ የሕዝባችንን ጥቅም ማስከበር ይቻላል ብለን የምናስበው ሒደት ካለ በሰጥቶ መቀበል ፖለቲካ መሥራት የምንቸገር አይደለንም። ለዚያም ሁሌም ክፍት ነን።

የምታወጧቸው መግለጫዎች ጠንካራ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ከክልሉ ውጪ ተቻችሎ የሚኖረውን አማራ ሕዝብ ከፍተኛ ጫና ውስጥ እየከተታችሁት ነው ይባላል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ልክ ነው! ለሕዝባችን ድምፅ ለመሆን በምናደርገው ሒደት ውስጥ መሠረታዊ የሚባሉ ጥያቄዎችን ጠንከር አድርገን በድፍረት ነው የምናወጣው። በዚህ ሒደት ውስጥም ያገኘናቸው ለውጦች አሉ። በተለይ በክልሉ መንግሥት ላይ የፖለቲካ ጫና በመፍጠር ዛሬ የደረሰበት አቋም ላይ እንዲደርሱ፣ ፀረ አማራ የሆኑ አመራሮቹን እንዲያስወግድ ብዙ የፖለቲካ ሥራ ሠርተናል። በእኛ በኩል ጠንካራ መግለጫዎችን ማውጣት፣ የፖለቲካ ጫና ለማሳደር መሞከርና ለሕዝባችንን ትክክለኛ ድምፅ ለመሆን የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።

አብን ራሱን የሚከላከልበት ነጥቦች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ናቸው ይባላል። በአንድ በኩል ኢትዮጵያን የፈጠርን ነን የሚል ዋጋ የመውሰድ ዓይነት ዝንባሌ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች የተበተነውን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ነው የተቋቋምነው ትላላችሁ። ይሄን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያን እኛ ነን የፈጠርናት የሚለው አረዳዱ ስህተት ነው። የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያን በመፍጠር ሒደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው ሕዝብ ነው። ይህ ማለት ግን አማራ ብቻ ኢትዮጵያን ፈጠራት የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርስ አይደለም። እንዲህ ብሎ የሚደመድም ካለ ስህተቱ ያለው ደምዳሚው ላይ ነው። በሒደት ውስጥ የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር ሰፊ የሆነ ግንኙነት አለው፤ ሰፊ የሆነ መስተጋብር ፈጥሯል፤ ተጋብቷል፣ ተዋልዷል፣ በደም ተሳስሯል፣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ባሕል፣ የጋራ ማንነቶችን አዳብሮ ቆይቷል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የአማራ ሕዝብ አገር በመመሥረት ሒደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሰፊው ተሠራጫቶ የሚኖር ስለሆነ ነው አገራዊ አድርገን ድርጅታችንን የመሠረትነው።

 

የአማራና የቅማንትን ሕዝብ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባሕል፣ ተመሳሳይ ሃይማኖቶች፣ ተመሳሳይ አኗኗር ያለው በምንም የማትለየው ሕዝብ ነው

 

በክልላችሁ አልፎ አልፎ ለተፈጠሩ ወይም ለሚፈጠሩ ግጭቶች ተጠያቂው ማነው ብላችሁ ታምናላችሁ?
ባለፉት ዓመታት በተለይም ባለፈው ሁለት እና ሦስት ዓመት ውስጥ ክልላችንና ሕዝባችን የጦርነት ቀጠና እንዲሆን የሚፈልጉ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች እና ኃይሎች አሉ።

በዋነኛነት የአማራን ሕዝብ ውስጣዊ አንድነት በመከፋፈል እና እርስ በርሱ ጦትነት ውስጥ እንዲጠመድና እንዲባላ ማድረግ ከሚፈልጉት ኃይሎች ውስጥ ትሕነግ (የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር [ሕወሓት]) እና የትሕነግ ተላላኪዎች ናቸው።

እንደ ምሳሌ በአማራና በቅማንት መካከል ያለውን ችግር ብንወስድ፤ የአማራና የቅማንትን ሕዝብ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባሕል፣ ተመሳሳይ ሃይማኖቶች፣ ተመሳሳይ አኗኗር ያለው በምንም የማትለየው ሕዝብ ነው። የተጋባ፣ የተሳሰሰረ፣ ረጅም መስተጋብር ያለው ሕዝብ ነው።

ነገር ግን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የሚባለው ፀረ አማራ ቡድን የቅማንት ኮሚቴ የሚባሉትን ተቀጣሪዎች በመክፈል የአማራን ሕዝብ የመነጣጠል፣ እርስ በርሱ የማጣላት፣ ቅራኔዎች እንዲፈጥሩ የማድረግና ጦርነት ውስጥ እንዲገባ የማድረግ ሥራ ሠርቷል፤ መሣሪያ እያስታጠቀ ሕዝባችንን ሲያስወጋ ነበር። ፀረ አማራ የሆነው የትሕነግ አስተሳሰብና የትሕነግ አመራሮች ጉዳይ ነው ማለት ነው። ይህንን ስንል ብዙ ጊዜ በስህተት የሚደመደመው ትሕነግ ሲነካ የትግራይ ሕዝብ ተነካ ብለው አካኪ ዘራፍ የሚሉ የተለያዩ ቡድኖች አሉ።

የትግራይ ሕዝብ ወንድም ሕዝባችን ነው። የትግራይ ሕዝብ እና የአማራ ሕዝብ ማንም ሊለያየው የማይችል ለረጅም ጊዜ ትስስር ያለው ሕዝብ ነው። ትሕነግ ግን በግልጽ የአማራ ሕዝብ ጠላት የሆነና አማራ ጠላቴ ነው ብሎ የተነሳ ቡድን ነው።

እሱ አማራን ለመጉዳት መቼም ሊቆጠብ እንደማይችል አይተናል። ባለፉት 27 ዓመታት ሲሠራው የነበረው ያንኑ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ግን የክልላችን መስተዳድር የሆነው አዴፓ ተገቢውን የፖለቲካ ሥራ ባለመሥራቱና የእርስ በርስ የሕዝባችንን ግንኙነት እንዲጎለብት ባለማድረጉና ደካማ በመሆኑ ሕወሓት ሲሠራ የነበረውን ሥራ የሚከላከል የፖለቲካ ሥራ ባለመሥራቱ ዛሬ ሕዝባችንን ላለበት ውጥንቅጥ ተዳርጓል። ትልቅ የፖለቲካ መፍትሔ ይፈልጋል። ብዙ ሥራ መሠራት አለበት። አሁንም ቢሆን ከዚህ ግጭት በኋላ ሕዝባችንን የሚለያይ አይደለም፤ ቅማንት አማራ ብለህ የምትለየው ሕዝብ አይደለም።

በክልላችሁ ውስጥ ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች የንቅናቄያችሁ አቋም ምንድን ነው?
ባለፉት ዓመታት በተለይ በሽግግር ወቅቱ ክልሎች ሲካለሉ የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ግዛቶችና የአማራን ሕዝብ ለማዳከም በታቀደ መንገድ ወደ ተለያየ ክፍሎች ሲካለሉ ነበር። ከዛም ጋር በተያያዘ ወደ ሌሎች ክልሎች የተካለለው ሕዝባችን በግልጽ የማንነት ጥያቄ አለ፤ ‘ማንነታችን አማራ ነው፣ ወደ አማራ ክልል ልንከለል ይገባናል’ የሚል ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ አንስተዋል። እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ስለሆኑ ግዛቶቹም የአማራ ታሪካዊ ርስቶች ስለሆኑ ወደ አማራ ሕዝብ ሊካተቱ ይገባል።

የአማራ ሕዝብ ከታሪካዊ ርስቱ የተነጠለ ማንነት የለውምና ርስቶቻችንም ሕዝባችንም ወደ ዋናው አማራ ሕዝብ ሊካተቱ ይገባዋል የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው። ይህን ደግሞ አብን መቶ በመቶ የተቀበለው ነው። አብን ባደረገው ትግልም አዴፓ ባለፈው ባደረገው ጉባዔ እነዚህን ጥያቄዎች ተቀብያለሁ፤ የኔም ጥያቄዎች ናቸው ብሏል። ይህም የአብን አንዱና ግንባር ቀደሙ ድል አድርገን ነው የምንወስደው።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኑኙት “ተገርስሷል” በሚል እንደምታምኑ ይታወቃል። ይህንን ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው?
ተገርስሷል የሚለውን አባባል አልሰማሁትም። በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ባለፉት ዓመታት በነበረው የተበላሸ ሥራ መጠራጠር ተፈጥሯል። ይህንን ማንም የሚክደው አይደለም። ለምሳሌ በትግራይ እና በአማራ ሕዝብ መካከል ባለፉት ዓመታት ሲሠራ የነበረው በተለይ የአማራ ሕዝብ በወንድሙ የትግራይ ሕዝብ ላይ ልቡ እንዲሻክርና እንዲያዝን አድርጎታል። ምክንያቱም ከትግራይ የወጡ ወንበዴዎችና ገዳዮች የአማራን ሕዝብ ባለፉት ዓመታት ሲገድሉ፣ የትግራይ ሕዝብ አንድም ቀን አላወገዘም፤ አንድም ቀን እንባ አላፈሰሰም። ስለዚህም እንደዚህ ዓይነት መሻከሮች ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ነገሮች አሉ። ያ ማለት ግን ሕዝቡ ተለያይቷል ወይም [ግንኙነታቸው] ተገርስሷል፣ ግንኙነቱ ተቋርጧል የሚባል ነገር አይደለም። መሻከሮች አሉ፤ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም መሻሻል ያስገልገዋል። ያን ለማለት ካልሆነ እንደዚህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ የደረሰ አመራር አለ ብዬ አላስብም።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here