ውለታ ቢስነታችን ቅጥ አጥቷልና ግርማዊነትዎ ይማሩን!

0
1483

የሰሞኑን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ እና የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልት ዘግይቶም ቢሆን መገንባት ተንተርሰው ሙሉጌታ ገዛኸኝ ኢትዮጵያ የንጉሠ ነገሥቱን ውለታ ዘንግታለች በማለት ይከራከራሉ።

 

 

ዐፄ ኃይለሥላሴ ከዲፕሎማሲያዊ ችሎታቸው ባሻገር በዓለማቀፋዊና አህጉራዊ መድረኮች ያስገኙት ስኬት እንዲሁም ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ማንነትና አንድነት የውርስ አሻራ ይታወሳሉ። ተራማጅ አስተሳሰብና የሞራል ልዕልናን የተላበሱ እንደነበሩም ጸሐፍት ይሥማማሉ። የጃንሆይ ግዙፍ ስብዕና በፓን አፍሪካኒዝም እውን እንዲሆንና የአህጉሩን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ከአፍሪካ አንድነት መሥራች አባቶች ቀድመው ተሰልፈው የመሠረት ድንጋይ ያኖሩ ዘንድ የትውልድ ኃላፊነትን ፍፃሜ ለማድረስ ችለዋል።

ንጉሠ ነገሥቱ ለአፍሪካ አህጉር ውሕደት ብሎም ለመላው ጥቁር ዘር ተምሣሌት በመሆን በተለይም በካሪቢያን እና በአሜሪካ ተቀስቅሶ የነበረው የኔግሮ ነጻነት ጠቅላላ ትግልና የኒውዮርክ ሐርለም መነቃቃት ንቅናቄ አራማጆች እነ ማርክስ ጋርቬይ፣ ዊልያም ዲቦይዝ፣ ሲልቪስተር ሲልቫ እና ሌሎችም የጥቁር ብሔርተኞች ልዩ አክብሮት መስጠታቸው አይዘነጋም። የራስ ተፈሪያን እምነት መፈጠርና የነጻነት መሪ ሆነው መቆጠር ዛሬም ድረስ በጥቁሮች መብት ትግል ረገድ ይንፀባረቃል። ይህንን የተገነዘበው ዕውቁ የሬጌ አቀንቃኝ ቦብ ማርሌ በአገረ ጃማይካ የራስ ተፈሪያንን ጎራ ተቀላቅሏል። ዕድሜ ልኩንም ኢትዮጵያን የጥቁሮች ተስፋይቱ ምድር፣ ዐፄ ኃይለሥላሴን ደግሞ የነጻነት ፈርጥ አድርጎ አወድሷል። የሬጌው ንጉሥ ቦብ ማርሌ አድናቂ ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው። በሙዚቃ ሥራው ተወዳጁ ቴዲ አፍሮ የግርማዊነታቸውን ፓንአፍሪካኒስት ዕሳቤ ግሩም በሆነ ጥዑመ ዜማ እንዲህ ሲል ገልፆታል፦

“እነ ጆሞ ኬንያታ፣
የኖራቸው ትልቅ ቦታ፣
ከተፈሪ መክረው ለካ፣
ተሞከረ ፓን አፍሪካ…”
(ከተፈሪ መክረው ለካ የሚለው ይሠመርበት።)

ለአፍሪካ ነጻነት ብሎም ለመላው ጥቁር ዘሮች ነጻ ሕዝብ ዕውቅና መረጋገጥ ፅኑ እምነትና አቋም የነበራቸው ዐፄ ኃይለሥላሴ በአንድ ወቅት በአሜሪካን አገር የጥቁሮች ሰብኣዊ መብቶች ዕውቅና በቅጡ ባላገኘበት ያ ዘመን ዋይት ሀውስ ቤተ መንግሥት ከወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆን.ኦፍ ኬነዲ ጋር የክብር ግብዣ የተደረገላቸው፣ ረቀቅ ባለው ዲፕሎማሲ ችሎታቸው የተደነቁ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ መሪ ነበሩ። ከአገራቸው ጥቅም አስቀድመው የጥቁሮች መብት አያያዝ ሁናቴ ልዩ ትኩረት እንዲስብ ተወያይተዋል፤ ለቀጣዩ የአፍሪካ አህጉራዊ ትስስር ጥንካሬ ዋጋ እንዲኖረው ለማስቻል ጭምር ፅኑ አቋማቸው ተግባራዊ ውጤት ማስገኘቱ ሊካድ የማይችል ሐቅ ነው።
የንጉሠ ነገሥቱ ዓለም ዐቀፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ምን ይመስል ነበር? ብለን ስንጠይቅ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ቴዎዶር ቬዝታል እንዲህ ገልጾታል። “…ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጄኔቭ ለመንግሥታቱ ማኅበር ‘ሊግ ኦፍ ኔሽንስ’ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር በወቅቱ አጋር አልባዋ ኢትዮጵያ በብቸኝነት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የተከራከሩት ለአገራቸው ነጻነት እውን መሆን ብቻም ሳይሆን የአፍሪካን ዕጣ ፈንታ ጭምር ነበ።” የተጫወቱትን አህጉር ዐቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት ከእርሳቸው ቀጥሎ አገሪቱን እያስተዳደሩ የመጡ መሪዎች የንጉሠ ነገሥቱን ጠንካራ ውርስ ዋጋ እንዲሰጡና በእርሳቸው የታሪክ ጎዳና ለመራመድ ሳይገዳደራቸው የሚቀር አይመስልም። የአሁኖቹ መሪዎች በአፍሪካም ሆነ በመላው ዓለም መድረክ ምን ይዘው? በምንስ መሠረት ይቅረቡ? የዐፄ ኃይለ ሥላሴን አርቆ አሳቢና ፈር ቀዳጅነት፣ አገር የገነቡበትን ብልሐት ጠንቅቀው ካልተገነዘቡ በስተቀር ልቃቂቱ እንደጠፋበት ድር በከንቱ ይባዝናሉ።

ሌላው ጉዳይ በአፍሪካ አህጉር በደቡብ አፍሪካ ተንሠራፍቶ የነበረው የአፓርታይድ ወይም የዘር መድልዖ አገዛዝና ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመላቀቅ የፀረ ኮሎኒያሊዝም ትግል ስኬት ብርታት ሆኗቸዋል። ቅኝ ግዛት እንዲያከትም ለፀረ አፓርታይድ ትግሉ ያበረከቱት ዓይነተኛ ድጋፍ ሲሆን በተለይም ከአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ (በምኅፃረ ቃል ኤ.ኤን.ሲ.) ቀንደኛ መሪዎች በተለይም ኔልሰን ማንዴላ በፖለቲካዊና ወታደራዊ ትጥቅ ትግል ሥልጠና እንዲያገኝ መርዳታቸው መላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት በሰባ ወይም ሰማንያ ዓመታት ብቻ እንዲቀጭ ያደረጉት ጥረት የአፍሪካ አባት እስከመባል የበቁ ስለመሆናቸው የምዕራቡ ዓለም ጸሐፍትም ይህንኑ ሀቅ አልሸሸጉም። በሚገባ ተመዝግቦም ይገኛል።

 

የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ የአህጉራዊው ድርጅት ዋና መቀመጫ በአዲስ አበባ ሆኖ መቀጠል አይችልም የሚል የሰላ ሙግት በቃጡ ጊዜ የያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነሸጥ አድርጓቸው ጋዳፊን የረቱበት ብቸኛ የመከራከሪያ ብልሐት የዐፄ ኃይለ ሥላሴን ጉልህ ሚና ታሪክ ያስከነዳ ማስረጃ አጣቅሶ ማቅረባቸው መሆኑን ልብ ይሏል።

 

እ.ኤ.አ በጥቅምት ወር 1954 በይፋዊ ጉብኝት ወደ እንግሊዟ ሎንዶን ከተማ ያቀኑት ንጉሠ ነገሥት በወቅቱ የእንግሊዝ ልዑላን ቤተሰቦች፣ ንግሥቲቱ እና የኤድንብራው መስፍን በቪክቶሪያ አየር ማረፊያ የእንኳን ደኅና መጡ ደማቅና ልዩ የክብር አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ጎዳናዎችም ባልተለመደ ሁናቴ ስፍር ቁጥር በሌለው ሰው ተጨናንቀው ተስተውለዋል። ንግሥቲቷ ዳግማዊት ኤልሳቤጥ ባደረጉት ንግግር እንዲህም ብለው ነበር። “ጃንሆይ ከጥንታዊና ሉዓላዊቷ…. መንግሥት ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጡ። ከኹለተኛው ዓለም አውዳሚ ጦርነት መገባደጃ የራሷን ነጻነትና ሉዓላዊነት ያስከበረች ብቸኛ አገር…” ሲሉ ንግግራቸውን ቀጠሉ። ዐፄ ኃይለሥላሴም በጉብኝታቸው የንግሥቲቱን እናት ሰላምታ ለመለዋወጥ ከሎንዶን ከተማ ዌስት ሚኒስትር ምክር ቤት ተነስተው ወደ ክላሬንስ እና ዲግናቶሪስ መኖሪያ ቤኪንግሐም ቤተ መንግሥት አመሩ። በዚያው ዘመን በአሜሪካ የሚታተመው ዝነኛው ታይም መጽሔት በፊት ለፊት ገጹ ዐፄ ኃይለ ሥላሴን የምዕተ ዓመቱ ታላቅ ሰው ብሏቸዋል።

አህጉራዊው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት በተሸጋገረ ማግስት መሥራች አባቶችን በተለይም የጋናው መሪ ክዋሚ ንክሩማህ ሐውልት እንዲቆምላቸውና እንዲዘከሩ ሲደረግ ዕፄ ኃይለሥላሴን ገሸሽ ማድረግ ከእኩይ ጥላቻ የመነጨ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ፍርዱን ለእውነተኛ የታሪክ ጸሐፍትና ለትውልድ ብንተወው ሳይሻል አይቀርም። ዘመን የማይሽረው ጠንካራ አፍሪካዊ አንድነትና መሠረት መጣል አስተዋፅዖዋቸው ክብር መንፈግ አይገባም።

በቶጎ ዋና ከተማ ሎሜ በተካሔደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አ.አ.ድ.) ጉባዔ ላይ የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ የአህጉራዊው ድርጅት ዋና መቀመጫ በአዲስ አበባ ሆኖ መቀጠል አይችልም የሚል የሰላ ሙግት በቃጡ ጊዜ የያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነሸጥ አድርጓቸው ጋዳፊን የረቱበት ብቸኛ የመከራከሪያ ብልሐት የዐፄ ኃይለ ሥላሴን ጉልህ ሚና ታሪክ ያስከነዳ ማስረጃ አጣቅሶ ማቅረባቸው መሆኑን ልብ ይሏል።

ለማጠቃለያ ይሆነን ዘንድ ዐፄ ኃይለሥላሴ የዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት ሲመረቅ ያደረጉት አስደማሚ ንግግር እንጥቀስ፡- “ከትልቅ ወይም ከትንሽ መወለድ ቁምነገር አይደለም፤ ራስን ለትልቅ ታሪክ መውለድ እንጅ” ነበር ያሉት።

ሙሉጌታ ገዛኸኝ የታሪክና ቅርስ ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው gezahegn.mulu@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here