የኮሚሽኖቹ አባላት ሹመት

0
788

‹‹በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው ቂም ካልፀዳ ጠንካራ ፖለቲካ መገንባት አይቻልም››

ይህ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን እንዲሁም የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ማክሰኞ፣ ጥር 28/2011 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከጸደቀ በኋላ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ ከተናገሩት የተወሰደ ነው።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ማንነትን፣ ወሰንን፣ ድንበርንና ሌሎች ምክንያቶችን መሰረት አድርገው በተደጋጋሚ የሚታዩትን ግጭቶች ለመፍታትና ባለፉት ዓመታት በሕዝቦች ልብ ውስጥ ያለውን የበዳይ ተበዳይ አስተሳሰብ በዕርቅ ለመዝጋት እነዚህ ኹለት ኮሚሽኖች፡ የአስተዳደርና ወሰን ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን እና ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት እንዲቋቋሙ ሆነ። እንደኮሚሽኖቹ ማፅደቂያ ሁሉ ኮሚሽኖቹን ተግባራዊ ለማድረግ ይመጥናሉ ተብለው ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተወጣጡትን አባላት ማፅደቁም ላይ ከምክር ቤቱ በኩል አልጋ በአልጋ አካሄድ አልነበረም። በርካታ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና ተቃውሞዎች ተስተናግደዋል።
የኹለት ዓመታት ዕድሜ እንደሚኖራቸው በሕግ የተወሰነባቸው እነዚህ ብሔራዊ ኮሚሽኖች ታላላቅ አገራዊ ችግሮችን ይፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአስተዳደርና ወሰን ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን
የቀድሞ የኢፌዴሪ ርዕሰ ብሔር ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ያካተተው እና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍልና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የተወጣጡ ግለሰቦችን በአባልነት የያዘው ይህ ኮሚሽን አርባ አንድ አባላትን ያቀፈ ነው ። የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተሰፋየ ዳባ ስለ ኮሚሽኑ አባላት ለምክር ቤቱ ሲናገሩ አባላት የተመረጡት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጉዳዩን አጥንተው ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርቡ ነው እንጂ የጉዳዩ ባለቤት በዋናነት ኅብረተሰቡ መሆኑን አስረድተዋል። የተስፋየ ዳባን ሐሳብ የሚጋሩት የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ‹‹ወሰንም ይሁን ማንነት›› ሲሉ ይጀምራሉ ባለቤትነቱ የሕዝቡ ነው ነገር ግን አባላት ወደ ሕዝቡ ሄደው ጥናት ሲያደርጉ ወገንተኛ እንዳይሆኑ አባላቱ የአገሪቱንና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ የሚያውቁ እንደሆኑ የአባላት የትምህርት ዝግጅታቸው ላይ በመመርኮዝ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አቅራቢነት እንዲሾሙ የቀረቡት አባላት አብዛኞቹ በሦስት ትውልድ ያለፉ እና ታሪክን በመመርኮዝ ችግርን ይፈታሉ ተብለው እንደሚታሰቡ በምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪው ጫላ ለሚ ይገልፃሉ። አያይዘውም ከወጣቱም ትውልድ እንዲሳተፍ መደረጉን አክለዋል።

የአስተዳደርና ወሰን ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላትን ሹመት በተመለከተ ከምክር ቤት ተቃውሞ ተሰምቷል። በኮሚሽኑ ውስጥ የተካተቱት አብዛኞቹ አባላት የመንግሥት ተቃዋሚዎች ናቸው፤ ስለዚህ የኢህአዴግ ተቃዋሚ በሆኑ ሰዎች ለውጥ ይመጣል ብዬ አላምንም ይላሉ የምክር ቤት አባሉ አጽበሃ አረጋዊ። የአባላት ስብጥሩ ትክክል አይደለም በሚል የተቃውሞ ድምፃቸውን የሚያሰሙት አባል ደግሞ ሱማሌ ክልል በአንድ ሰው መወከሉን ይነቅፋሉ። ብዙ ደም መፋሰስና ዕልቂት የነበረበትን ክልል በአንድ ሰው መወከል ለዛውም ስለ ነበረው ችግር እምብዛም መረጃው የሌለውን ሰው ማስቀመጥ ትክክል አይደለም በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተው በተጠቀሱት አባላት ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልፀዋል።

ለተነሱት ተቃውሞዎች ጫላ ለሚ ጠቅለል አድርገው ምላሽ ሲሰጡ ኮሚሽኑ እስከ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ ወርዶ እንደሚሠራና የፖለቲካ ሰዎች ኮሚሽኑ ውስጥ የገቡት የፖለቲካ ሐሳባቸውን ለማራመድ እንዳልሆነ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

በኮሚሽኑ ውስጥ በአባልነት የተካተቱት የአርበኞች ግንቦት 7 ፀሐፊ አንዳርጋቸው ፅጌ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሲገልፁ ‹‹ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል›› ሲሉ ጀምረው የተሰባሰበው ኃይል የተማረ ኃይል ነው ሲሉ ይቀጥላሉ ። ወሰንና ድንበር ላይ ብቻ ትኩረት የሚደረግ ከሆነ በእርግጥ ችግር ሊፈታ እንደማይችል እና ማለቂያ ወደ ሌለው የወሰንና የማንነት ጥያቄ እንደሚያመራ ይገልፃሉ። ለዚህ ደግሞ ከማንነት ጋር የተቆራኘ ፖለቲካ ሲቀረፍ ብቻ እንደሚገታ እንደ መፍትሔ ጠቁመዋል። የአንዳርጋቸውን ሐሳብ የሚጋሩትና በዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባልነት የተካተቱት የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀ መንበር ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በየክልሉ ያለው የወሰንና ማንነት ጥያቄ ሳይፈታ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እንደማይታሰብ ይናገራሉ።

በኮሚሽኑ አባላት ላይ በተነሳው ተቃውሞ ያላቸውን አስተያየት አንዳርጋቸው ጨምረው ሲገልፁ በመቃወም ደረጃ የሚቃወም ድርጅት ይኖራል፤ ነገር ግን የሚቃወም ሕዝብ እንደሌለ ያብራራሉ። በሁሉም የአገሪቱ ክልል ያለው ኅብረተሰብ በሰቀቀን እንደሚኖርና ይህም መቀጠል እንደሌለበት ገልፀው ባለፉት ዓመታት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ፀረ ሽብር አዋጅ እየተባለ ሰው ሲገረፍና ሲገደል በነበረበት አገር በዕርቅና ሰላም እንዝጋው ሲባል ተቃውሞ ማሰማት እጅግ አሳፋሪ ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል።

በመጨረሻም የአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ሹመት 22 ተቃውሞና አራት ታዕቅቦ አስተናግዶ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት
በኢትዮጵያ ውስጥ የወደፊት የሰላም፣ አብሮነትና የተግባቦት ኑሮን ለማረጋገጥ እና በሕዝቦች መካከል የነበረውን በጥርጣሬ የመተያየት፣ የቂም በቀል ስሜትንና የበዳይ ተበዳይ አስተሳሰብን ለማርገብ በማሰብ እንደተቋቋመ የተገለፀው ኮሚሽኑ የሐይማኖት መሪዎችንና ታዋቂ ግለሰቦችን ያካተተ አርባ አባላትን የያዘ ነው። የቀድሞ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማሪያም ደሳለኝን እና በአባልነት ያካተተው ኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጁን ለማጽደቅ የገጠመው የተቃውሞ ድምፆች እንዲሁ የኮሚሽኑ አባላት ሹመት የወቅትም ገጥሞታል።

‹‹የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝብ ተጣልቶ አያውቅም፤ ቢጣላም አስታራቂ አያስፈልገውም›› በሚል የተቃውሞ ድምፃቸውን በማሰማት የጀመሩት የምክር ቤት አባል ካሳ ጉግሳ ናቸው። ካሳ የኮሚሽኑ አባላት ማንን ከማን እንደሚያስታርቁ ግልፅ እንዳልሆነላቸው እና ዕርቁ ወደ ድርጅቶች ቢዞር ትርጉም እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ስለ ኮሚሽኑ አባላትም ሲናገሩ ስም ሳይጠቅሱ ‹‹አንዳንዶቹ ድንጋይ ተሸክመው ቢለምኑም አስታራቂ መሆን አይችሉም›› ሲሉ ተችተዋል።

በኮሚሽኑ የቀረቡት እጩዎች አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት የሕዝብ ኃላፊነትን በአግባቡ ያልተወጡ ናቸው። ገሚሶቹ ደግሞ ከዚህ በፊት ሕገ መንግሥቱን ለመናድ የተንቀሳቀሱ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በግልፅ ጠላታችን እከሌ ነው በሚል እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ናቸው የሚል ነቀፌታ የምክር ቤት አባል ሃዱሽ አዛናው አሰምተዋል። ስለዚህም ይላሉ ሃዱሽ ‹‹አባላት ነፃ ሆነው ያስታርቃሉ›› ብለው እንደማያምኑ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

 

ተጎድቻለሁ ለሚለው የኅብረተሰብ ክፍል መካስ እንኳን ባይቻል ችግርህን አይተንልሃል፤ እናውቅልሃለን ማለት ለኮሚሽኑ ትልቅ ኃላፊነት ለተጎጂው ደግሞ ከፍተኛ የመንፈስ ድጋፍ እንደሆነ ተጠቅሷል

 

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን በስም በመጥቀስ በተቀባይነታቸው ላይ ጥርጣሬ አለኝ ሲሉ ተቃውሞ ያሰሙት አባል ኮሚሽኑ ብቁ አባላትን አካቷል ለማለት እንደሚቸገሩም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አበበ ከፈኔ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ‹‹ዕርቅን የሚጠላ ሰይጣን ነው›› በማለት ለኮሚሽኑ ያላቸውን ድጋፍ ከማሰማተቸውም ባሻገር የኮሚሽኑ አባላትን በተመለከተ አብዛኛውን ኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ እንደሆነና ቶሎ ወደ ሥራ መገባት እንዳለበት ጠቁመዋል።

‹‹ድርጅቶች ግዑዝ አይደሉም የሰዎች ስብስብ ናቸው›› በማለት የምክር ቤት አባል ጌታቸው መለሰ ሐሳባቸውን ጀምረው የግለሰቦች መታረቅ ለድርጅቶችም መፍትሔ እንደሆነ ጠቁመው ድርጅቶች ወጥተው የሚያንፀባርቁት የኅብረተሰቡን ሐሳብ እንደሆነ አብራርተዋል።

የመንግሥት ተጠሪው ጫላ ለሚ በተለያዩ ምክንያቶች ኅብረተሰቡ ከቤት ንብረቱ እየተፈናቀለ ባለበት ሁኔታ ‘ሰላም አለ ችግር የለም’ ሊባል እንደማይችል ገልፀው፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጉዳይ በሚመለከትም አንድ ሰው የሠራው ጥፋት እንዳልሆነ እና እንደ መንግሥት ጥፋት መታየት ያለበት ጉዳይ እንደሆነና እሱም መንግሥት በይፋ ይቅርታ የጠየቀበት ሁኔታ እንደነበር በማስታወስ ምላሽ መሰጠቱን አስታውሰዋል።

ስለ ኮሚሽኑ ዓላማና ስለተነሱት ጥያቄዎች ብርሃኑ ነጋ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ‹‹የተሔደበት አካሄድ ትክክል ነው›› ይላሉ። የቆየ ችግር ያለበት አገር ነው ቀስ ተብሎ ከምርጫው በፊት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል። በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው ቂም ካልፀዳ ጠንካራ ፖለቲካ መገንባት እንደማይታሰብ የገለፁት ብርሃኑ፥ ከዚህ በፊት የነበሩትን ችግሮች በይቅርታ መፍታት ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉ ያክላሉ። ‹‹ሹመቱ ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነና በግሌ ትልቅ ሸክም ተሰምቶኛል ምክንያቱም ትልቅ ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል›› ብለዋል። ተጎድቻለሁ ለሚለው የኅብረተሰብ ክፍል መካስ እንኳን ባይቻል ችግርህን አይተንልሃል፤ እናውቅልሃለን ማለት ለኮሚሽኑ ትልቅ ኃላፊነት ለተጎጂው ደግሞ ከፍተኛ የመንፈስ ድጋፍ እንደሆነ ተጠቅሷል።

በኮሚሽኑ አባላት ሹመት ወቅት በተነሱት ተቃውሞዎች ላይ ብርሃኑ ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ኅብረተሰብ አልተጣላም ማለት የሕፃን ወሬ ነው፤ በደሎች፣ ግጭቶች ተሰርተው ነው እዚህ የተደረሰው›› በማለት ብርሃኑ አንዱ አንዱን በክፋት እንዲመለከት ተደርጎ የኖረ ኅብረተሰብ እንዳለ ተናግረዋል።

የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ሹመት በዐሥራ ስድስት ተቃውሞ እና በአራት ታዕቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here