የቤተ እስራኤላውያን ሰሞነኛው ጉዞ አንድምታ

0
1848

በእየሩሳሌም ነግሶ የነበረው ‹ጥጦስ›፣ ከክርስቶስ ልደት ከሰባ ዓመት በኋላ እየሩሳሌምን ሲያፈራርሳት የአይሁድ ሕዝቦች በዓለም እንደተበታተኑ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
በጊዜው ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ ቢኖሩም፣ የመጀመሪዎቹ ቤተ እስራኤላውያን ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት አንድ ሺሕ ዓመት በፊት፣ ከንግሥተ ሳባ ልጅ ምኒልክ ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ታሪክ ያሳያል።

እስከ 4ተኛው ክፍለ ዘመን ድረስም በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በኤርትራ እና በትግራይ አካባቢዎች እንደኖሩም ነው ታሪክ የሚዘግበው። በኋላም (በ4ኛው ክ/ዘ) በኢትዮጵያ፣ ክርስትና የአገሪቱ ኃይማኖት ሆኖ ሲታወጅ፣ ኃይማኖቱን አንቀበልም በማለታቸው ከአክሱም ተባረው በወገራ፣ ደምቢያ፣ ጭልጋ፣ ጣና ሐይቅ ዳር እና ሌሎች ቦታዎች ከሰፈሩ በኋላ፣ በሙሴ ሕግ የሚመራ የራሳቸውን ሥርወ-መንግሥት መሥርተው መኖራቸው ይጠቀሳል።

ይህ የቤተ-እስራኤላውያን ሥርወ-መንግሥት፣ ከአክሱም ሥርወ-መንግሥት እና በኋላም በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተመሠረተው ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ጋር ብዙ ጦርነትን ያሳለፈ ሲሆን፣ እስከ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም መሻገር ችሎ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን የቤተ-እስራኤላውያኑ ሥርወ-መንግስት እየተዳከመ ሔዶ ሲፈርስ፣ ቤተ-እስራኤላውያኑ በኢትዮጵያ ያላቸው ማኅበራዊም ይሁን ፖለቲካዊ ድርሻ እየተዳከመ፣ ቁጥራቸውም እንዲሁ እየቀነሰ መሄዱ ይነገራል።

ለረዥም ዘመናት በሌላው ዓለም ተበትነው የሚኖሩት አይሁዶችም እንዲሁ በሚኖሩበት አገር ኹሉ ጥቃት ሲበዛባቸው ከሌላው ዓለም በመምጣት በፍልስጤም ይኖሩ ከነበሩት ጥቂት አይሁዶች ጋር ተሰባስበው አገር ከመመሥረት ውጭ ሌላ የሚያድናቸው ነገር እንደሌለ በማሰብ፣ ከፍልስጤም ምድር የእርሻ መሬት በመግዛት ቀስ በቀስ እስራኤል የምትሰኝ አገራቸውን እንደመሠረቱ ታሪክ ምስክር ነው።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዓለም ተበታተነው የሚገኙ እስራኤላውያንን ከያሉበት የመሰብሰብ ዘመቻዎች ተካሂደዋል። ዘመቻዎቹም ግዙፍ የሚባሉና በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ናቸው። በኢትዮጵያ የሚኖሩ ቤተ-እስራኤላውያንም ከ1976 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ወደ እስራኤል አገር በመመለስ ላይ ይገኛሉ። በ1976 ‹‹ዘመቻ ሙሴ›› እና በ1983 ‹‹ዘመቻ ሰሎሞን›› በተባሉ ዘመቻዎች በርካታ ቤተ-እስራኤላውያን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ምድር እንደሄዱም ይታወቃል።
ሰሞኑንም ቤተሰቦቻቸው እስራኤል አገር ውስጥ የሚገኙ 3 ሺሕ ኢትዮጵያውያንን እስራኤል ወደ ምድሯ የመውሰድ ውሳኔ ማሳለፏ ተሰምቷል።

ወደ እስራኤል እንዲገቡ የተወሰነላቸው ቤተ-እስራኤላውያንም ወላጆቻቸው፣ ልጆቻቸው ወይም ቤተ-ዘመዶቻቸው እስራኤል ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፣ የመጀመሪያዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ቤተ-እስራኤላዊቷ ባለሥልጣን የስደተኞች ጉዳይ ሚኒስትር ፒኒና ታማኖ ሻታ ውሳኔው እስራኤል ውስጥ ለሚገኘው ማኅበረሰብ እና ለቤተሰቦቻቸው ጠቃሚ ነው ስትል፣ የአገሪቱ ምክር ቤትም ባስቸኳይ ይኽ እንዲፈጸም በሙሉ ድምጽ መወሰኑን መናገሯ በጉዳዩ ላይ የወጡ ዘገባዎች ያመላክታሉ።

ሆኖም፣ ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት በርከት ያሉ ቤተ-እስራኤላውያንን ማውጣት ለምን ፈለገች የሚለው ጉዳይ ለብዙዎች ጥያቄ አጭሯል። በ1983 እንዲሁ ‹‹ዘመቻ ሙሴ›› በሚል እስራኤል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን ለመውሰድ ባደረገችው ሒደት የደርግ መንግሥት ማብቂያው ደርሶ እንደነበርና በዚህም የተወሰኑ የደርግ ባለሥልጣናት በዚህ ዘመቻ አብረው እንደሄዱ ይነገራል።

መምህር ደረጀ ነጋሽ ይህን አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ሲገልጹ፣ በአንድ አገር ውስጥ ፈተናዎች ሲኖሩ እና የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ ሌሎች አገራት ዜጎቻቸውን ያስወጣሉ። አጋጣሚውን ተጠቅመው ዝርያቸውንም ሊያስወጡ ይችላሉ ነው ያሉት። አሁን ላይ እስራኤል የምታደርገው ነገር በሠላም ጊዜ ማድረግ ይቻል ነበር፤ ነገር ግን ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ሊሆንም ይችላል የሚሉት መምህሩ፣ ከዚህ ኹሉ በላይ ነው ያሉትን የኢትዮጵያን እና የእስራኤላውያንን የጠበቀ ግንኙነትም አስረድተዋል። በዚህም 12 ሺሕ የሚደርሱ የሌዊ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡና በአክሱም እንዲሁም በጣና ቂርቆስ አካባቢ ለበርካታ ዘመናት መኖራቸውን አንስተው፣ በዚህም ከሚቀያየረው ፖለቲካዊ ግንኙነት ውጭ ያለው የኹለቱ አገር ሕዝቦችን ትስስር የማይቋረጥ ነው ብለዋል።

እንዲሁም፣ የሙሴ አማች ኢትዮጵያዊው ዮቶር ለሙሴ ሕግን ያስተማረው ስለሆነ፣ ኢትዮጵያውያንና እስራኤላውያን በመማር ማስተመር ሒደት የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ነው የጠቆሙት። እየሩሳሌምን ለመሠረተው ኢትዮጵያዊው መልከጼዴቅ አስራት ያወጣው አብርሀም (እስራኤላዊ) እንደነበርም አንስተው፣ የኹለቱን ሕዝቦች ታሪካዊ አንድነት አመላክተዋል። ከዚህ አኳያ ከ3000 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የኹለቱን አገሮች ወዳጅነት የላላ ሲመስል እንኳን እንደማይቋረጥ አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ፣ እስራኤል ቀደም ብሎ ከዓመት በፊት በማይካድራ በተደረገ ጭፍጨፋ የተሳተፉ ግለሰቦች የተካተቱበትን የቤተ-እስራኤላውያንን የማስወጣት ድብቅ ዘመቻ ማድረጓ የሚታወስ ነው። ሆኖም በምስጢር ማስወጣት ለምን አስፈለገ? የኢትዮጵያ መንግሥት ቤተ እስራኤላውያን እንዳይሄዱ መከልከል ይችላል ወይ? ለሚለው መምህር ደረጀ ሲመልሱ፣ ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ እስከሆነ ድረስ የማስወጣት ሒደቱ በስምምነት ነው የሚደረገው። አኗኗራቸው፣ ባህላቸው፣ የሚጠቀሙት ገንዘብ እና ባንዲራ የኢትዮጵያ እስከሆነ ድረስ ከዚህ ኹሉ ወጥተው ዜግነታቸውን እስከሚለውጡ እስራኤል ብትፈልግም የኢትዮጵያ መንግሥት ካልፈቀደ አይወጡም። በድብቅ የሚያደርጉትም ለዚህ ሊሆን ይችላል ብለዋል። ምናልባትም ደግሞ ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠርና ሠላም የሌለባት አገር ናት በማለት ለሌላው ዓለም የኢትዮጵያን ገጽታ አጨልሞ ለማሳየት ሊሆን እንደሚችልም አመላክተዋል።

በማይካድራ የንጹኃን ጭፍጨፋ ካካሄዱትና የሳምሪ ቡድን ከሚባሉት ውስጥ በስመ ቤተ እስራኤላዊ ወደ እስራኤል ከሄዱት ጋር ተያይዞ፣ እስራኤል ይህን ማድረጓ ምናልባት ለህወሓት ድጋፍ ስለምታደረግ ሊሆን ይችላል የሚሉ መኖራቸውን ተክትሎ፣ መምህር ደረጀ ይህ እውነት ነው ብሎ መቀበል እንደሚከብድና ማረጋገጫ እንደሌለ ጠቁመዋል። በውጭ ፖሊሲ ላይ ቋሚ ጠላትም ይሁን ቋሚ ወዳጅ የለም፣ ህወሓትን የሚደግፉ ቢሆን እንኳን የአሁኑ ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ተመልሰው የወዳጅነት እንቅስቃሴ ሲፈጥሩ እናያለን ነው ያሉት። በአሜሪካ በኩልም፣ ከባይደን የውጭ ፖሊሲ ጋር እንጂ ከሕዝቡ ጋር ምንም ዓይነት ችግር የለም። ከእስራኤል ጋርም ሊሆን የሚችለው በውጭ ፖሊሲ ካልሆነ ሕዝብ ለሕዝብ ያለው ግንኙነት ሠላማዊ መሆኑን አንስተዋል።

ምናልባት ግን ኢትዮጵያ የሚኖሩ ቤተ-እስራኤላውያንን ለማስወጣት የተደረገው ድብቅ ዘመቻ ህወሓት ወንጀለኞቹን ለማሸሽ የተጠቀመበት መንገድ ሊሆን እንደሚችል ይነሳል። በአንድ ወቅት የህወሓት ሰዎች “በማንነታችን ምክንያት የሕልውና አደጋ ውስጥ ነን” በማለት፣ በማንነታቸው ለብዙ ዘመን መከራ ከተቀበሉት እና ከመጥፋት ድነው አገር ከመሠረቱት እስራኤላውያን ልብ እንዳገኙ ይነገራል። ይህም በወታደራዊ አቅም ከጎለበተችዋ እስራኤል ድጋፍ ለማገኘት ብቻ ሳይሆን፣ እነሱ ለሚታገሉት አካል የኃይል ድጋፍ እንዳትሰጥ ለማድረግ ነው ይባላል። መምህር ደረጀም ወንጀለኞች ይህን ተጠቅመው እንዳይወጡ መንግሥት በእጅጉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

መምህር ደረጀ የቤተ እስራኤላውያን መሄድ ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰው ምንም የለም። ወደፊት ተመልሰው እንደሚመጡ አልጠራጠርም ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የሄዱትም ወደ ቀደሞ አገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው ሲመጡ አይተናል ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም፣ እስራኤል ይህን ዘመቻውን በድብቅም ይሁን በግልጽ የምታደርገው ለቤተ- እስራኤላውያን ፍቅር ስላላት ነው ማለት አይቻልም ብለዋል። የመምህሩን ሐሳብ የሚያጠናክር በሚመስል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትኒያሁ፣ ከኢትዮጵያ ጭምር የሄዱ አፍሪካውያን ስደተኞችን አስመልክቶ በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የ7.8 ሚሊዮን አይሁዶች መኖሪያ የሆነችውን እስራኤል አይሁዳዊ ባህሪ ሊበርዙ የሚችሉ አደጋዎች ናቸው ሲሉ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ይህም አገሪቱ ለስደተኛ የማትመች የሚያስመስላት መሆኑንና ከኢትዮጵያ ለሚሄዱ ቤተ-እስራኤላውያንም እንዲሁ እዚህ ሆነው የሚያስቡትን ያህል የከንዓን ምድር ሆና ላያገኟት እንደሚችሉ ይነሳል። በቤተ-እስራኤላውያኑ ላይ የቆዳ ቀለምን መሠረት ባደረገ ዘር ተኮር መድሎ ሳቢያ በእስራኤል በተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ ሲካሄድም ነበር።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያና የእስራኤል ግንኙነት ጥንታዊና በብዙ መልኩ የተሳሰረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የሚኖሩ አይሁዶችን ከሕጋዊ መንገድ ውጭ በድብቅ ለማስወጣት መሞከሯ በኹለቱ አገሮች መካከል ለዘመናት የኖረውን መልካም ግንኙንት ሊያሻክረው እንደሚችል መምህር ደረጀ አመላክተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እስራኤል እያደገ ለመጣው የአፍሪካ ፍላጎቷ ከህወሓትም ጋር ይሁን የፍላጎቷ አስፈጻሚ ከሚሆን ከየትኛውም አካል ጋር ትብብር ልታደርግ እንደምትችል ነው የሚነገረው።
በተለይም የዐረብ አገራት በተወሰነ መልኩ ዓይናቸውን ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ አፍሪካ ቀንድ ማዞራቸው ይታመናልና እስራኤልም የዐረቡን አቅም ለመግታት በአፍሪካ ቀንድ ላይ ድርሻ እንዲኖራት መፈለጓ አይቀሬ ነው የሚሉ አሉ።
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማያልፈው የዓባይ ወንዝ መካከለኛው ምሥራቅ ድረስ ዘልቆ የጥቅም አጀንዳ የመሆኑ ጉዳይ ነው። በቅርቡ በሱዳን በተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ግብጽና እስራኤል እጃቸው እንዳለበት ሱዳን ማስታወቋ አይዘነጋም።

ይህም በመስከረም 1971 በ39ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር ሚና፣ በግብጹ ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት እና በእስራኤል መሪ ቤናቼም ቤጅን የተደረሰው፣ ‹‹ካምፕ ዴቪድ ሥምምነት›› በዋናነት በኹለቱ አገሮች መካከል ሠላም ለመፍጠር ቢሆንም፣ የዓባይ ወንዝ ጉዳይም የዚህ ሥምምነት አንድ አካል መሆኑ አይካድም። በዚህም ግብጽ የዓባይ ውኃ ሲና በረሃን አቋርጦ ወደ አይሁዶች መንደር እንዲዘልቅ ለማድረግ ሥምምነት መፈጸሟ ምናልባትም እስራኤል በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያላት ትኩረት እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችልና ልክ እንደ ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ሱዳንን መጠቀሚያ ልታደርጋት እንደምትችል ይነሳል።

በአውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 2019 መጨረሻ ድረስ፣ ከ155 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በእስራኤል እንደሚኖሩ በወቅቱ የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል። ወደፊትም ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለመሄድ የሚጠባበቁ በርካታ ቤተ-እስራኤላውያን መኖራቸው ይነገራል።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here