የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለኛ ቅንጦት ወይስ የሀብት ብክነት?

0
874

የአዳማ እና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲዎች በከፍተኛ ወጪ የተቋቋሙ ነገር ግን የታለመላቸውን ግብ ያልመቱ ተቋማት ናቸው እየተባሉ ይታማሉ። ይህንን ከግንዛቤ ያስገቡት አንድነት በለጠ ዩንቨርስቲዎቹ የሀብት ብክነት ናቸው፣ በቅድሚያ በየዩኒቨርሲቲው ያሉትን የቴክኖሎጂ ዲፓርትመንቶች ማጠናከር ያስፈልጋል ይላሉ።

 

መንግሥት ለተፈጥሮ ሳይንስ የሰጠውን ከፍተኛ የፖሊሲ ትኩረት ተንተርሶ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራቸችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በመስፋፋት ላይ ይገኛሉ። ይኼን መነሻ በማድረግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የተቋቋሙ ሲሆን፥ የተፈጥሮ ሳይንስ ተቋማቱ ቁጥር ወደፊት ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለአንድ አገር ዕድገት የሚጫወተው ሚና ለማንም ሰው የተደበቀ እውነት አይደለም። እንደሚታወቀው በሰው ልጅ የሥልጣኔ ጉዞ ሒደት በአጠቃላይ በዓለም አገራት የዕድገት ታሪከ ያለ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር የተለወጠ ማኅበረሰብ እና ያደገ አገር የለም። በዚህ ረገድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር ተቋማት የጠፈር ምርምር (space science centers) ተቋማትን ጨምሮ መፈጠርና በሒደት መስፋፋት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ይህን መሠረት ባደረገ መልኩም በአገራችን ከዚህ በፊት በከፍተኛ ተቋማት አካዳሚያዊ አደረጀጀት ውስጥ ያልነበሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችን በመክፈት ተማሪዎችን ተቀብለው በተለያዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፎች በማስተማር ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ተቋማት በተቃዋሚ አደረጃጀታቸው ለተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርትና ሥልጠና ከፍተኝ ትኩረት በመስጠት የሳይንስና ቴክኖሎጂ የልኅቀት ማዕከል (center of excellence) ለመሆን ይሠራሉ ተብሎ ይታሰባል። ይህ ማለት ግን ለማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርትና ሥልጠና ዘርፎች ክፍት መሆን የለባቸውም ማለት አይደለም። ከዐሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በእንግሊዝ ከተጀመረውና በኋላም በሌሎች የምሥራቅ አውሮፖ አገራት በተስፋፋው የኢንዱስትርያል አብዮት ጀምሮ በሳይንስና ፈጠራ ረገድ ከፍተኛ እመርታና አስደናቂ ውጤት እያስመዘገቡ የመጡት አገራት፥ አሁን ላይ ለደረሱበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልኅቀት ማዕከላት የመሆን ደረጃ (center of excellence) ለመድረስ የተለያዩ ታሪካዊ ሒደቶችን አልፈዋል። በተጨማሪም የሳይንስ ተቋማቱ ምንም እንኳ በፖሊሲ ደረጃ ለተፈጥሮ ሳይንስ ትኩረት ቢሰጡም፣ የማኅበራዊና ሌሎች የጥናት ዘርፎችን ከተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች በተጓዳኝ ይሰጡ ነበር እንጂ፥ ለተፈጥሮ ሳይንስ ትኩረት እንሰጣለን በሚል ሌሎች የማኅበራዊ የጥናት መስኮች ላይ በራቸውን አልዘጉም ነበር።

ነባራዊው ሁኔታ
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለአገራችን የቴክኖሎጂ ሽግግርና ፈጠራ (‘innovation’) ምኞት ቅንጦትና ብክነት ከመሆን አልፎ ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ በጥልቀት መፈተሽ ያለባቸው በርካታ ፖሊሲ ነክና ተቋማዊ ጉዳዮች አሉ። በመሠረቱ ማኅበራዊ ሳይንስን በማዳከም የተፈጥሮ ሳይንስን ማሳደግ አይቻልም። ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ትኩረት ስንሰጥ በተጓዳኝ ሌሎች ዘርፎች (‘disciplines’) ላይ የጥፋት ፍርድ (‘academic suicide’) በመፈፀም ሊሆን አይገባም። ከጥንት ጀምሮ ተጣብቀው የተወለዱትንና ተያይዘው ያደጉትን ኹለቱን የሳይንስ ጥናት ዘውጎች የፖለቲካ ግብ ለማሳካት በሰርጀሪ ማለያየት ይቻል ይሆናል:: ይሁን እንጂ ዘላቂና እውነተኛ ለውጥና ዕድገት ማምጣት ግን አይታሰብም። የተፈጥሮና ማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት ዘርፍ በመሠረታዊ ባሕሪው አንዱ ለሌላው ደምን ለሕዋሰ (cell and blood) የሚያቀብል ተቃቃፊና ተመጋጋቢ ዘውግ እንጂ አንዱ ካንዱ ተነጣጥሎ በማደጎና በጉዲፈቻ ሊያድግ የሚችል ነገር አይደለም። ለሳይንስ ትኩረት መስጠት በሚል ብሒል የማኅበራዊ ጥናት ዘውግን ማቀጨጭ፣ የዜጎችን በምርጫቸው የመማር መብትና ማኅበራዊ ፍትሕን እንደመንፈግ ተደርጎ ይወሰዳል። የሒሳብ ዕውቀት ‘ለኮሚፕዩተር ፕሮግራመሩ’ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፥ ለአካውንታቱና ለኢኮኖሚስቱ እንደየደረጃው ያስፈልገዋል። አርኪዮሎጂ ሳይንቲስቱ በቁፋሮ ያገኘውን አፅመ ቅሪት ያለ ታሪክ ተመራማሪው ሙያዊ ሚናና ተሳትፎ ትክክለኛ ዕድሜውንና ታሪካዊ ዳራውን ለማወቅ አይቻልም።

እንደሚታወቀው የአካዳሚክ ጥናት ዲስፒሊን ማኅበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ በሚል የተከፈለው ለአጠናን እንዲያመች (‘for methodological purpose’) እንጂ በኹለቱ መካከል ፍቺ ለመፈፀም ወይም ደግሞ አንዱን የበላይ አንዱን የበታች በማድረግ በመሐላቸው የበርሊን ግንብ ለመገንባት አይደለም።

ከተለያዩ የአለማችን አገራት ልምድና ተሞክሮ እንደምንረዳው እንደ እኛ ባሉ እንኳንስ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ባዕድ ለሆኑ ዛሬም ድረስ በበሬ ሻኛ እራታቸውን ለሚጋግሩ ኋላ ቀር አገራት ይቅርና በቴክኖሎጂ ዕድገታቸው (‘mass production/mass consumption’) ደረጃ ላይ በደረሱ በርካታ የዓለማችን አገራት እንኳን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጥናትና ምርምር ተቋማት ከአካዳሚ፣ ኢንስቲትዩትና ኮሌጅነት የዘለለ ተቋማዊ አደረጃጀት የላቸውም። ለምሳሌ ለአሜሪካን የጠፈር ምርምር (‘NASA’) ከ21% በላይ የሰሠጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ የሚታወቀውና ታዋቂው ኢትዮጵያዊው የአርኪኦሎጂ ሳይንቲስት ዶክተር ዘረሰናይ የሚሠራበት የካሊፎርኒያ ሳይንስ አካዳሚ የተሰኘው የሳይንስና ‘ኢኖቬሽን’ ተቋም ተቋማዊ አደረጃጀቱ አካዳሚያዊ ሲሆን፣ በውስጡ ታሪክና ቅርሳ ቅርስ ጥናትን ጨምሮ በርካታ የማኅበራዊ ጥናት መስክ ማዕከላትን አካቶ የያዘና አንዱ ከሌላኛው እየተመጋገበ በጋራ የሚሠራ ተቋም ነው። በተጨማሪም በዓለም በግዙፍ የቴክኖሎጂ አዳዲስ ሐሳብ አመንጪነቱ የሚታወቀው የአሜሪካን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን የዓለማችን ግዙፍ የቴክኖሎጁ ተቋም ተመሳሳይ ቅርፅና ይዘት ያለው ሥመ ጥር የሳይንስ የፈጠራ ማዕከል ነው። እንደ ጀርመንና ፈረንሳይ ባሉ ሌሎች የአውሮፖ አገራት ያለው ተሞክሮም ቢሆን ባመዛኙ ተመሳሳይ ነው። በተመሳሳይ የአውሮፖ ‘ኢኖቬሽን’ ልኅቀት ማዕከል ተደርጎ የሚወሰደውንና አውሮፖን በቴክኖሎጂ ይመግባል የሚባለውን የጀርመኑን ሔድበርግ ሳይንስ ኢንስቲትዩትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

 

በበሬ ሻኛ እራታቸውን ለሚጋግሩ ኋላ ቀር አገራት ይቅርና በቴክኖሎጂ ዕድገታቸው ደረጃ ላይ በደረሱ በርካታ የዓለማችን አገራት እንኳን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጥናትና ምርምር ተቋማት ከአካዳሚ፣ ኢንስቲትዩትና ኮሌጅነት የዘለለ ተቋማዊ አደረጃጀት የላቸውም

 

ስለሆነም እንደኛ ላሉ ገና በዳዴ የሚሔድ ቴክኖሎጂ ላይ ላሉ አገራት የተሻለው አማራጭ አካዳሚያዊ ተቋማዊ አደረጃጀቱን በአካዳሚ ወይንም ደግሞ በኢንስቲትዩት ደረጃ ዝቅ በማድረግና ለተቋማቱ ሙሉ አካዳሚያዊ፣ የሥራ ነጻነትና ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሌሎች የጥናት መስኮች ጋር በመተሳሰር እጅና ጓንት ሆነው የሚሔዱበትን ሁኔታ አጥንቶ ማመቻቸት ነው። ለዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና የመቀሌ ኢንስቲትዩት ኦቭ ቴክኖሎጂ ዓይነቱን ተሞክሮ በመውሰድ መሰል ተቋማትን በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች መፍጠር፣ ያሉትን ማጠናከርና በሒደት ወደ ሳይንስ ኮሌጅና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚያድጉበትን መንገድ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናት መተግበር እንጂ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥም የማኅበራዊ ሳይንስና ሌሎች ፕሮግራሞችን በማጠፍ፣ በመቀነስና በመበተን የሀብት ብክነትን ከማስፋፋት፣ ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን፣ ማኅበራዊ ፍትሕንና የትምህርት ተደራሽነትን ከመጉዳት ባለፈ መንትዮቹን የተፈጥሮና ማኅበራዊ ሳይንስ የጥናት መስኮች በማለያየት ምንም ዓይነት አገራዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here