ህወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ግብር እየሰበሰበ መሆኑ ተሰማ

0
782

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት በተቆጣጠራቸው አንዳንድ አካባቢዎች ግብር እየሰበሰበ መሆኑን የሰሜን ወሎ አካባቢ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ባሳለፍነው የኅዳር ሦስተኛ ሳምንት 2014 ወደ ሎጊያ ከተማ ያቀኑ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ህወሓት በተቆጣጠራቸው የተወሰኑ ቦታዎች፣ ለተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ከማኅበረሰቡ ግብር እየሰበሰበ መሆኑን ነው አዲስ ማለዳ መረዳት የቻለችው።
የህወሓት ሥራ አስፈጻሚዎች ከማኅበረሰቡ ግብር እየሰበሰቡ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ግብር እየጠየቀ ያለው ለመብራትና ውኃ አገልግሎት መሆኑን አመላክተዋል።

ሰሞኑን ከቆቦ ከተማ ወደ ሎጊያ ከተማ ያቀኑ አየነ አራጋው የተባሉ ግለሰብ በዋጃ፣ በጥሙጋና በቆቦ ከተማ የመብራት አገልግሎት መዘርጋቱን ጠቅሰው፣ ለዚህም በጊዜያዊነት የተሾሙት የህወሓት ሥራ አስፈጻሚዎች የመብራት ግብር እየሰበሰቡ መሆኑን ጠቁሟል።
አየነ፣ በእያንዳንዱ ቤት 50 ብር የአገልግሎት ክፍያ ህወሓት እንደሚሰበስብ ገልጸው፣ የመብራት አገልግሎት ዝርጋታው ከመቀሌ እንደመጣና አካባቢው ይህን አገልግሎት ማግኘት ከጀመረ ከኹለት ወር በላይ እንዳስቆጥረ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መንገሻ በላይ የተባሉ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ፣ የህወሓት አባላት ግብር መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን፣ የኤሌክትሪክ ገመዶችን ሆን ብለው በመቁረጥና “መብራት እንድንቀጥልላችሁ ብር አዋጡ” በማለት ገንዘብ እንደሚሰበስቡም ነው የተናገሩት።
ለአብነትም፣ በቆቦ ከተማ 03 ቀበሌ ያለውን መብራት መስመር በመቁረጥና “እንቀጥልላችሁ” በማለት፣ በእያንዳንዱ ቤት መቶ ብር አዋጡ ብለው ከ50ሺሕ ብር በላይ አሰባስበዋል ሲሉ ነው መንገሻ የተናገሩት።

ከነዋሪው ከላይ የተጠቀሰውን ገንዘብ ቢሰበስቡም፣ የመብራት ጥገናውን ያከናወኑት ግን ምንም ዓይነት ወጭ ሳያወጡ ተቆርጦ የነበረውን ገመድ በመቀጠል ብቻ መሆኑን በቦታው ተገኝቸ አይቻለሁ ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
ሌላኛው የገቢ ማሰባሰቢያ ምንጫቸው ወፍጮና ውኃ ነው የሚሉት መንገሻ ጮቢ፣ አባርጎ፣ ቆቦ፣ አራዶም በተባሉት ቦታዎች ወፍጮ እንዳለ ጠቁመው፣ 50 ኪሎ ጤፍ ለማስፈጨት ክፍያው 500 ብር መሆኑን ነው ያመላከቱት።
መንገሻ አያይዘውም፣ የውኃ አገልግሎት ዝርጋታ የተጀመረው ከአንድ ወር በፊት መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ ለዚህም ከእያንዳንዱ ቤት 50 ብር ግብር እየተከፈለ ነው ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ህወሓት ቋሚ ግብር የሚሰበስበው ከመብራትና ከውኃ ቢሆንም፣ ከወፍጮ፣ ከትራንስፖርት፣ ከገበያ “በፈለጉት መጠን” ተጨማሪ ብር እንደሚያሰባስቡ ነው መረዳት የተቻለው።
ጌታሁን ጫኔ የተባሉት የአካባቢው ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት፣ የትራንስፖርት አገልግሎትም እንደተጀመረና ታሪፉ ከዕጥፍ በላይ መሆኑን ነው።

ከትራንስፖርትም ግብር እየተሰበሰበ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ታሪፉ ከዕጥፍ በላይ ነው የሚሉት ጌታቸው፣ ከደሴ መርሳ 1ሺሕ 200 ብር፣ ከደሴ ወልደያ 1ሺሕ 500 ብር፣ እንዲሁም ከደሴ ቆቦ 2ሺሕ ብር መሆኑን ነው የገለጹት።
ከዚህ በፊት በነበረው ታሪፍ ከደሴ መርሳ 50 ብር፣ ከደሴ ወልደያ 75 ብር፣ ከደሴ ቆቦ 100 ብር፣ እንዲሁም ከወልደያ ቆቦ 25 ብር እንደነበረ ነው ጌታቸው የተናገሩት።

ጌታቸው አያይዘውም፣ የህወሓት ታጣቂዎች የነዳጅ ማደያዎችን በመቆጣጠር ነዳጅ በውድ ዋጋ እየሸጡና ገቢ እያሰባሰበ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ አሁን ላይም 20 ሊትር ነዳጅ 7ሺሕ ብር፣ አንድ ሊትር ቤንዚን 300 ብር፣ አንድ ሊትር ጋዝ 250 ብር፣ አንድ የእጅ ባትሪ ዲንጋይ 83 ብር፣ አንድ ደርዘን ክብሪት 6 ብር፣ እንዲሁም አንድ ሻማ 25 ብር እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች ከጦርነቱ በተጨማሪ፣ የኢኮኖሚ ውድመት እየደረሰባቸው መሆኑን እና ብር የሚያወጡትም ወደ ሎጊያ ከተማ እየሄዱ መሆኑን ነው ጌታቸው የገለጹት።

ከዚህም በተጨማሪ የአካባበው አርሶ አደር 70 በመቶ የሚሆነውን ሰብል እንደሰበሰበና ከኹለት ሳምንት በፊት የህውሓት ታጣቂዎች “አዲስ ቅኝ” እና “መንደፈራ” ከተባሉ አካባቢዎች ሰብሉን ጭነው ለመውሰድ በመጡበት ወቅት በፋኖ እንደተማረኩ ተመላክቷል።
ሰሞኑን ወደ ሎጊያ 14 የህወሓት ምርኮኞችን ይዘው ያቀኑ ተመስገን አህመድ የተባሉ የፋኖ አባል፣ ህወሓት ግብር እየሰበሰበ ከመሆኑም በተጨማሪ “አዲስ ቅኝ” እና “መንደፈራ” በተባሉት ቦታዎች ከኹለት ሳምንት በፊት የተሰበሰበውን ሰብል ለመዝረፍ ሙከራ አድርጎ ነበር ብለዋል።

ቢሆንም ግን፣ ይህን የሰሙት ፋኖዎች በቁጥር ያልታወቁ በርካታ የህወሓት ታጣቂዎችን እንደገደሉና 14 የሚሆኑትን ከአንድ ኤፍ ኤስ አር መኪና ጋር እንደማረኩ ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here