ማስቆሚያ የታጣለት ያለ ዕድሜ ጋብቻና መዘዙ

0
979

ያለ ዕድሜ ጋብቻ ለአትዮጵያ አዲስ ባይሆንም በቅርቡ የብዙኃን የተከሰተው ከወትሮው ለየት ያለ ነበር። የተፈፀመው ትግራይ ክልል፤ ቦታው ደግሞ ተንቤን ወረዳ ሙዜ ደበት የሚባል አካባቢ ነበር። ዕድሜው በግምት ወደ 20ዎቹ አጋማሽ የሚጠጋው ክብሮም ግደይ የተባለ ወጣት ዘንግቶት ኖሮ ይሁን ረስቶት፤ ለብዙዎች ያስገረመ ምስል በፌስቡክ ገፁ ይለጥፋል። ምስሉም ክብሮም አንዲት ዕድሜዋ ከ13 ያልበለጠ ልጃገረድ ጋር ጋብቻ ሊፈፅም እንደሆነ ያሳይ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ፤ በማኅበራዊ ሚዲያ ጉዳዩ የብዙዎች ትኩረት ከመሳብ አልፎ አስቆጥቶም ነበር። በርግጥ ለክልሉ መስተዳደር ኃላፊዎችና ለበጎ ፈቃደኞች ምስጋና ይግባቸውና፤ ጋብቻው እንዲቀር እንዲሁም የሙሽራውና የሙሽሪት ቤተሰቦች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ቢደረግም፤ ጉዳዩ ግርምት ፈጥሮ አልፏል። በርግጥ፤ አንድ በኩል የጉዳዩ በማኅበራዊ ሚዲያ በሥፋት መወራት የችግሩ ገፈት ቀማሽ ልትሆን የነበረችው ታዳጊ እንደትተርፍ ትልቅ ሚና ቢጫወትም፤ ያለ ዕድሜ ጋብቻ አሁንም በኢትዮጵያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያሳይ ነው።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች፥ አፍሪካንም ጨምሮ በስፋት ከሚፈፀሙ ሰብኣዊ መብት ጥሰቶች መካከል አንዱ የሆነው ያለ ዕድሜ ጋብቻ፤ ብዙ ሴቶቹን ላይ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። በዓለም ካሉ ሴቶች ከ680 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት 18 ዓመት ሳይሞላቸው እንዳገቡ የወርልድ ቪዥን እ.ኤ.አ 2018 መረጃ ያሳያል። ለአብነትም፤ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ደግሞ ይህ ዓይነቱ ችግር ጎልቶ የሚታይ ሲሆን፤; በየዓመቱ ወደ ሦስት ሚሊየን ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው ሦስት ጉልቻ እንደሚመሰረቱ ባለፈው ዓመት የወጣ የዓለም ባንክ ሪፖርት ያሳያል።

ኢትዮጵያም፤ ይህ ዓይነቱ ችግር ከተነሰራፋባቸው አገራት መካከል ናት። በአገሪቷ ከተደነገገ ከ 60 ዓመታት በላይ የሆነው የቤተሰብ ሕግ፤ ለጋብቻ ብቁ የሆነ ሰው ቢያነስ 18 ዓመት መሙላት እንዳለበት ቢያትትም፤ ተፈጻሚነቱ አናሳ ነው። የችግሩ ግዝፈት እንደ ክልሉ ሁኔታ ይለያያል። ከፍተኛው ቁጥር ያላቸው ያለ ዕድሜያቸው የተዳሩ ሴቶች በማስመዝገብ አማራ ክልል ሲሆን፤ 45 በመቶ የሚሆኑ የክልሉ ልጃገረዶች 18 ዓመት ሳይሞላቸው ይዳራሉ። በክልሉ፤ ዕድሜያቸው ለትዳር ያልደረሱ በርካታ ሕፃናት ሲዳሩ ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች መካከል ቀዳሚዎቹ ምሥራቅ ጎጃም፣ ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ያሉ ቦታዎች ሲሆኑ በቅርቡ መሻሻል ቢታይም ችግሩ አሁን በሥፋት እንደሚተገበር የአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናት እና ወጣቶች ቢሮ መረጃ ያሳያል።

በ2009 እና 2010 በክልሉ 5685 የጋብቻ ጥያቄዎች በዕድሜ ምክንያት ውድቅ መደረጉ በኅብረተሰቡ በኩል ያለው አመለካከት ብዙም ለውጥ እንዳላሳየ እንደሚጠቁም ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ይህንን የተረዳው ክልሉ፥ በእያንዳንዱ የታችኛው የሥልጣን ተዋረድ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አስወጋጅ ጥምረት አስቀምጧል። ጥምረቱም፤ በየአካባቢው የሚዳሩት ልጆች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ነው ወይስ በታች የሚለውን ጥናት ካደረጉ በኃላ፤ ማንኛውም ከ18 ዓመት በታች የሆነች ሕፃን ወዲያው ትዳሩ እንዲቋረጥ ያደርጋል። ይህንንም ድርጊት ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሊያስከትለው የሚችለውን አስከፊ የጤና ችግር፣ ለተለያዩ በሽታዎች የሚዳርግ መሆኑንና የሴቶችን የትምርህት ዕድል የሚያደናቅፍ እንዲሁም ሁሉም ሴት ሕፃናት የዝቅተኛነት ስሜት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ በመግለፅ፤ በክልል ለሚገኙ ነዋሪዎች ትምህርት እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናት እና ወጣቶች ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ የተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር የሆኑት ስማቸው ዳኛዬ ይገልጻሉ።

በተጨማሪም ያለ ዕድሜ ጋብቻ በልጅነት ዕድሜያቸው የሚዳሩ ሕፃናት በሚያረግዙበት ወቅት ተያይዘው የሚመጡትን የጤና ጠንቆችን በመግለጽ በክልሉ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚስጥር ሳጥን እንዲኖር እና ማንኛውም ተማሪ ያለምንም ፍራቻ ይህንን እንዲጠቀሙበትና አለበለዚያም በአካል መተው እንዲያሳውቁ ሰፊ ርብርብ እያደረግን ነው ሲሉ ስማቸው ያስረዳሉ።

እንደነዚህ ዓይነት እርምጃዎች በክልሉ ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቀነስ ትልቅ ሚና ቢጫወትም ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት አለመቻሉን ስማቸው ይገልጻሉ። በጤና ምርመራ ወይም የዕድሜ ምርመራ ለማድረግ የሚያስፈልጉንን መሣሪያዎች አለሟሟላታቸው፤ በአማራ ክልል የሚፈፀመውን ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሙሉ ለሙሉ እንዳይቆም አድርጎታል በማለት ስማቸው አክለዋል። የተመሳሳይ ችግር ተጠቂ ለሆነችውም ትግራይም ቢሆን ያለ ዕድሜ ጋብቻ ትልቅ ራስ ምታት ነው።

እ.አ.አ 2018 በዩኒሴፍ የወጣ መረጃ እንደሚያሳያው፤ በትግራይ ክልል 43 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 24 የሆናቸው ሴቶች 18 ሳይሞላቸው ተድረዋል። በዋነኝነት ድርጊቱ የሚፈፀምባቸው ቦታዎች ቆላ ተምቤ የሚባለው ወረዳ አንዱ ሲሆን ይህም በውስጡ 28 ቀበሌዎች አሉት። ከነዚህም ውስጥ 8 ቀበሌዎች ጭራሽ የማይፈፀም ሲሆን የተቀሩት 20 ቀበሌዎች አብዛኛውን ጊዜ እንደሚፈፀምባቸው የክልሉ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ክልሉ፤ በየአካባቢው ጠቋሚዎችን አስቀምጦ እያንዳንዱ ሰው ሲዳር በቅርቡ ያሉት ቀበሌዎች እንዲያሳውቁ በመንገር ከ18 ዓመት በታች የሆኑትን በመለየት ድርጊቱን የማስቆም ሥራ እየሠራን ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት በክልሉ የሚፈፀመው ያለዕድሜ ጋብቻ ሙሉ ለሙሉ እየቀረ ነው ሲሉ የቢሮ ኃላፊ ገልፀዋል። ከትግራይና አማራ ክልል ባሻገር፤ በኦሮሚያ፣ አፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በከፍተኛ ደረጃ የሚፈፀመው ያለ ዕድሜ ጋብቻ በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ለማስቆም ዕቅድ ቢያዝም እስካሁን በተከሄደበት ፍጥነት ‘ኢትዮጵያ ታሳካ ይሆን?’ ለሚለው ጥያቄ መልሱን አጨቃጫቂ እንዲሆነረ አድርጎታል።

እንደ ዩኒሴፍ ያሉ ተቋማት ይሳካል የሚል ተስፋ ቢኖራቸውም፤ ውጤቱ የሚያሳየው አገሪቷ ለማሳካት ረጅም መንገድ መጓዝ እንደሚጠብቃት ነው። በያለዕድሜ ጋብቻ ምክንያት በሚያጋጥም የወሊድ ችግር የፌስቱላ ታካሚዎች መጨመር ለዚህም አንደ አብነት ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ፤ በየዓመቱ ዘጠኝ ሺሕ ሴቶች የፌስቱላ ችግር የሚያጋጥማቸው ሲሆን ወደ ሕክምና ተቋማት በመሄድ ለችግራቸው መፍትሔ ማግኘት የቻሉት ግን 1200 የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here