በኢትዮጵያ የሚነሱ ግጭቶችን በየሦስት ወሩ መተንተን ሊጀመር ነው

Views: 308

የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ተቋም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን በየሦሰት ወሩ የሚመዘግብ፣ የሚተነትን እና ይፋዊ ሪፖርት የሚያወጣ አዲስ ቡድን አደራጅቶ ወደ ሥራ ሊያስገባ መሆኑን ገለጸ።

የመንግሥት ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የተለያዩ የግል ድርጅቶች እንዲሁም የሚዲያ ተወካዮች በዚህ ሥራ የሚሳተፉ ሲሆን፣ በተለያዩ ዘዴዎች የሚሰበሰቡ መረጃዎችን በማረጋገጥ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ግጭቶቹ የተከሰቱበት ቦታ ድረስ በመሄድ የሚያረጋግጡበት አንደሆነ ታውቋል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሃሌሉያ ሉሌ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ የግጭት ትንተናው ዋና ዓላማ መረጃ በቀላሉ እንዲገኝ ለማድረግ እና ስለ ግጭቶች በሚሰጡ የተሳሳቱ መረጃዎች ለከፋ ግጭት እየዳረጉ በመሆኑ ነው። ለዚህም ወቅታዊ እና ትክክለኛውን ሪፖርት ይፋ በማድረግ ግጭቶችን ለፖለቲካ ፍጆታ የማዋል ተግባሮችን ለመከላከል መታሰቡን ገልፀዋል።

‹‹በኹለት ግለሰቦች መካከል የተነሳ ግጭት ምንጩ ባለመጣራቱ ምክንያት ለፖለቲክ ፍጆታ እየዋለ ከመሆኑም በላይ ኅብረተሰቡ በተዛባ መረጃ ምክንያት ቀውስ ውስጥ እየገባ ነው›› ያሉት ሃሌሉያ፣ አክለው ‹‹ሆኖም የግጭት ትንተናው ይህን ከማጣራት ባሻገር ኢትዮጵያ እየደረሰባት ካለው ኪሳራ ይታደጋል ብለን እናስባለን›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የግጭት ትንተናው አስፈላጊነት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ችግሮች መካከል አብዛኞቹ የግጭቱ ምክንያት ሳይታወቅ የሚጀምሩ መሆናቸውን ተጠቁሟል። ነገር ግን ብሔርን መሰረት ያደረጉ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የማንነት ጥያቄዎች ዋና ዋና የግጭት መንስዔዎች በመሆናቸው መንስኤውን የማጥራት ሥራ ይሠራል ተብሏል።

ሃሌሉያ አያይዘውም ተቋሙ በቅድሚያ የግጭቶቹን መንስኤ መለየት ላይ እንደሚያተኩር እና በመቀጠል የግጭቶቹን ደረጃ ማወቅ ሌላው ሥራ ይሆናል ብለዋል። ‹ግጭቶች ከግለሰብ ፀብ ወደ ብሔር እና የእምነት ግጭት እንዴት ይሄዳሉ› የሚለውን የመለየት ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል። በተጨማሪም ከግጭት በኋላ ስለሚመጡ ውጤቶች ማለትም ሕይወታቸው ስለሚያልፉ ሰዎች፣ ተፈናቃዮች እና በአጠቃላይ ስለደረሱ ጉዳቶች ተአማኒነት ያለው መረጃን ሰብስቦ ይፋ ማድረግ አንዱ ተግባሩ እንደሚሆን ተናግረዋል። ግጭቶች የሚደጋገሙባቸውን አካባቢዎች በመለየትም መፍትሄ ለሚሰጡ አካላት ጠቃሚ መረጃዎችን የሚያቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰላም እና የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ ሜጀር ጀነራል አበበ ተክለ ሃይማኖት እንደሚሉት፣ ተግባራዊ የማይደረጉ ጥናቶችን ማካሄድ እየተለመደ መጥቷል። በደቡብ ክልል የተነሱ የክልልነት ጥያቄዎችን ለመፍታት ተቋቁሞ የነበረው እና በኋላ ላይ ግን ምንም ውጤት ሳያመጣ የቀረውን ቡድን ያስታውሳሉ።

‹‹እንዲህ ዓይነት ሥራዎች ሲሠሩ ለዘላቂነታቸው ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል›› ያሉት የቀድሞ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ አበበ ‹‹ምክንያቱም ከተጀመረ በኋላ ተአማኒነታቸው ታይቶ ኅብረተሰቡ ሊቀበላቸውም ሊነቅፋቸውም ይችላል›› ይላሉ።

ይህንን ጥናት እና ትንተና የሚያካሂዱ ሰዎችም የአእምሮ ዝግጁነታቸው ብቁ መሆን እና የኋላ ታሪካቸው ምን እንደሚመስል መለየት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ። አክለውም የትምህርት እና የሙያ ብቃት ያላቸው ሰዎችን መመልመል ለታሰበው ሥራ ወሳኝነት አለው ይላሉ፣ የሰላም እና የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኙ። በቂ እቅድ ወጥቶለት እና ምሁራን በበቂ ሁኔታ የሚሳተፉበት መሆን አለበት የሚሉት አበበ፣ ትንተናው በምን መልኩ ለሕዝብ ቢቀርብ ነው ጠቃሚ የሚሆነው የሚለው ላይም መሠራት አለበት ብለዋል።

‹‹ዋናው ጉዳይ ግን በዚህ ወቅት ከወገንተኝነት የራቀ እንዲሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል›› ያሉት አበበ ‹‹የግጭቶቹ ይዘት ላይ በማተኮር መያዝ ወይም ለሕዘብ መለቀቅ ያለባቸውን መረጃዎች መለየት በጣም አስፈላጊ ነው›› ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ከተፈጠሩት ግጭቶች ትንታኔ በተጨማሪ የነበሩትን የኅብረተሰቡን እሴቶች አብሮ ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ አብሮ መሥራት አስፈላጊ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com