ሠለሞን ዓሊ መሐመድ(ዶ/ር) ይባላሉ። በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሰብዓዊ ዲፕሎማሲና የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ናቸው። ማኅበሩ ውስጥ ማገልገል ከጀመሩ 10 ዓመት ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ከዛ በፊት በባህል ስፖርትና ቱሪዝም፣ እንዲሁም በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ለ16 ዓመት ያህል አገልግለዋል። ዶክትሬታቸውን እንደያዙ የፖለቲካና ፍልስፍና መምህር በመሆን በአስተማሪነት ሙያ ማገልገል የጀመሩት እኚህ ባለሙያ፣ ቀይ መስቀል ማኅበር ውስጥ ከገቡ በኋላ ለተቋሙ ሀብትን በከፍተኛ መጠን በማሰባሰብ ይታወቃሉ። ስለወቅታዊው የቀይ መስቀል ተግባራት እንዲሁም ተቋሙ ስለሚቀርብበት ስሞታ ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በመተዳደሪያ ደንቡ ተጠቅሰው ከሚያከናውናቸው ተግባራቱ ውስጥ አሁን ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራቸው የትኞቹን ነው?
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት የሚከሰቱትን ሰብዓዊ ቀውሶች ለመታደግ ይሠራል። ከውጭ አገራት የሚመጡ ስደተኞችን ጨምሮ ሕይወትና ኑሯቸው የተጎዱ ወገኖችን አቅሙ እንደፈቀደ ያግዛል። ጉዳት ለደረሰባቸው ልዩልዩ ድጋፎችን ይሰጣል። አገልግሎቶቹን በኹለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። መደበኛና ኢ-መደበኛ በመባል ይታወቃሉ። ኢ-መደበኛ የምንላቸው አስቸኳይ የሆኑ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲመጡ በዋናነት የምንሠራቸው ናቸው። መደበኛው ደግሞ ኹልጊዜ የምንሠራው ነው።
የ24 ሰዓት የአምቡላንስ አገልግሎት እንሰጣለን። በ10 ክልሎችና ኹለት ከተማ አስተዳደሮች ወደ 580 የሚሆኑ አምቡላንሶች አሉ። በ25 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ነጻ አገልግሎት ይሰጣሉ። የተጎዱ ወገኖችንም የመጀመሪያ ሕክምና ዕርዳታ ይሰጣሉ። ከአቅም በላይ ሲሆንም ወደአቅራቢያው የሕክምና ማዕከል በመውሰድ ሕይወትን የመታደግ ሥራ እንሠራለን።
ሌላው መሠረታዊ የመድኃኒት አቅርቦት ሥራ ነው። በ1980ዎቹ የተቋቋመ ሲሆን፣ 58 የሚሆኑ መድኃኒት ቤቶችን በመክፈት በተመጣጠነ ዋጋ ሕብረተሰቡ እንዲገለገልባቸው እያደረግን እንገኛለን። በዚህም ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ሰዎች በዓመት ውስጥ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ወደ 600 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎችም በየዓመቱ በእኛ የአምቡላንስና የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ዕርዳታ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ከተቋቋምን 86 ዓመታችን እንደመሆኑ እሳት አደጋ፣ ጎርፍና የመሬት መንሸራተትን የመሰሉ አደጋዎች ሲኖሩ፣ እንዲሁም ጦርነቶች ሲኖሩ ልዩልዩ ዕርዳታዎችን እንሰጣለን። ከአምቡላንስና የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ፣ ለተፈናቃዮች አስፈላጊ የሆኑ የምግብና የመጠለያ ድጋፎችን እናደርጋለን። በተለያዩ አጋጣሚዎች የተጠፋፉ ቤተሰቦችንም ማገናኘት አንዱ ሥራችን ነው። ተጎጂዎችን በቁስ ብቻ ሳይሆን በሥነ-ልቦናም ረገድ እንዲረዱ እናደርጋለን።
በሌላ በኩል በልማትም እንሳተፋለን። በዚህ ሥራው ማኅበራችን በስፋት ባይታወቅም፣ በጣም የተጎዱና መንግሥት የማይደርስባቸው አካባቢዎች በመገኘት ጥልቅ የውኃ ጉድጓድ እንቆፍራለን፤ ተፈጥሮን እንንከባከባለን፤ ዛፎችን እንተክላለን፤ ስለአደጋ ቅድመ-ዝግጅት ሕረተሰቡን እናስተምራለን፤ ኮሚቴዎችን እያደራጀን የቅድመ-ጥንቃቄ ሥራዎችን እንሠራለን፤ እንዲሁም ምርጥ ዘርን በማቅረብ የማኅበረሰቡ ኑሮ እንዲሻሻል እንሠራለን። ከልማት ጋር በተያያዘ ባለፈው 2013 ብቻ ከ800 ሺሕ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎችን ሠርተናል። ይህ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ አስወጥቷል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአባላትና የበጎ ፈቃደኞች ማኅበር እንደመሆኑ፣ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ አባላትና 200ሺሕ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞችም አሉት። ከዚህ ውስጥ ወደ43 ሺሕ የሚሆኑት በመጀመሪያ የሕክምና ዕርዳታ የሠለጠኑ ናቸው።
በዋናነት የምትታወቁበት የአምቡላንስ አገልግሎታችሁ ላይ በርካታ ቅሬታዎች ይቀርባሉ። ተሸከርካሪዎቹን ከከተማ ከተማ ለሰው ማመላለሻነት ከመጠቀም ጀምሮ፣ ለኮንትሮባንድና ከተፈቀደላቸው ዓላማ ውጭ ለግልም ሆነ ለቡድን ፍላጎት ማሟያ ይውላሉ መባሉን እንዴት ያዩታል?
በአሁኑ ጊዜ ወደ600 አምቡላንሶች አሉን። በትግራይ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተገናኘ ከገጠመው የአምቡላንሶች መጥፋትና ከሥራ ውጭ ከመሆናቸው በቀር ይህን ያህል አምቡላንሶች አሉ። ከአምቡላንስ ጋር በተገናኘ የሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች አሉ። በጄኔቫ ስምምነት መሠረት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርን ዓርማ ያለአግባብ መጠቀም በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ያስቀጣል ተብሎ የተደነገገ ነው። ይህ ቢሆንም ግን የተጠቀሱትን የመሳሰሉ ችግሮች ይስተዋላሉ።
አምቡላንሶቻችን በጣም ጉዳት ያለባቸው አካባቢዎች በደኅንነት ሥጋት ምክንያት አልፈው የማይሄዱባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ለምሳሌ ጦርነት ሲሆን እንደልባቸው መንቀሳቀስ አይችሉም። በዚህ አይነት ጊዜ ዓርማዎቻችንን ያለአግባብ በተለያዩ መንገዶች ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በመጀመሪያ ለሚመለከታቸው አካላት ለማስተማር እንሞክራለን።
የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ንቅናቄ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን የሚጥሱ ተግባራት እንዳይፈጸሙ እናደርጋለን። ተልዕኳችን ሰብዓዊነት ብቻ ስለሆነ ይህን ሕብረተሰቡ እንዲያውቅና ከማይሆን ተግባር እንዲቆጠብ እንሠራለን። አንዳንዴ በየወረዳው ያሉ ሠራተኞቻችን አምቡላንሶቻችንን አልፎ አልፎ አላግባብ ሲጠቀሙ ይገኛሉ። ለኮንትሮባንድ ሲጠቀሙባቸው አንድ ኹለት ጊዜ አጋጥሞናል። ሕዝብን ሲያመላልሱም ወደ 3 ጊዜ የተያዙ አጋጥመውናል። እንዲህም ሆኖ ሲገኝ በቀጥታ ነው የምናባርረው።
እዚህ ላይ ግን ሕብረተሰቡ ማወቅ ያለበት ኹሉም አርማችን ያለባቸው ተሸከርካሪዎች አምቡላንስ አለመሆናቸውን ነው። የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡም ሆኑ የኃላፊዎች መጠቀሚያ የሆኑ ታርጋችንን የሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎች መኖራቸውም ልብ ሊባል ይገባል። በሌላ በኩል፣ የቀይ መስቀል ዓርማ ያለው አምቡላንስ ኹሉ የእኛ ላይሆን ይችላል። አንዳንዴ ዓርማችንን ይዘው ከውጭ የሚገቡ ተሸከርካሪዎችም አሉ። እኛም በቀለም ሸፍነን የምንሸጣቸው የተጎዱ ተሸከርካሪዎቻችን በጊዜ ሒደት ዓርማችን መልሶ ሊታይ ይችላል። መከላከያም ሆኑ ሌሎች ተቋሞችም መሣሪያ የማይጭኑበት አምቡላንስ ሊኖራቸው እንደሚችል ይታወቃል። ቀይ መስቀል የተፈጠረው በጦርነት ውስጥ ስለነበር ዋና ሥራው በጦርነት የሚጎዱ ወታደሮችንም ሆነ ነዋሪዎችን ሕይወት መታደግ ነው።
ጦርነቱ ከተጀመረ ዓመት እንደማለፉ ማኅበራችሁ የተቋቋመበትን ዓላማ በአግባቡ ተወጥቷል ትላላችሁ?
የቀይ መስቀልም ሆነ የቀይ ጨረቃ ማኅበራት ሲቋቋሙ መንግሥትን ይተካሉ ተብሎ አይደለም። የመንግሥት አጋዥ እንዲሆኑ ነው። ነጻ፣ ገለልተኛ፣ የማያዳሉ ሆነው ማኅበረሰቡን ማገልገል ነው ዓላማቸው። የዛሬ 86 ዓመት አፄ ኃይለሥላሴ ባወጡት ዐዋጅ መንግሥት በተወካዩ አማካይነት ፈረንሳይ ተገኝቶ በፈረመው መሠረት ነው የተቋቋምነው። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ማኅበሩ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። አሁን እንዳሉት 6ሺሕ እንደሚሆኑት በርካታ በጎ አድራጊ ተቋማት አገራችን ውስጥ ሳይበረክቱ ጀምሮ ሲሠራ የነበረ ነው።
ጦርነቱ ጋር በተያያዘ ትልቁን ሥራ የሚሠራው የመንግሥት የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ነው። 95 በመቶ የሚሆነውን ተቋሙ ወረዳ ድረስ ባለው አደረጃጀት ተጠቅሞ የሚሠራው ነው። እኛ ጊዜያዊ ድጋፍ እንጂ ዓመቱን ሙሉ የሚዘልቅ ድጋፍ አናደርግም። ጦርነቱ እንደተከሰተ ሰሞን ባደረግነው ዳሰሳ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉልና ደቡብን በመሳሰሉ በሌሎች አካባቢዎች ወደ 2 ነጥብ 53 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ ይፈልጋል ብለን ነበር። ለዚህም ወደ 9 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሎ ነው ወደ ሀብት ማሰባሰብ የተንቀሳቀስነው። አሁን አንድ ዓመት ቢሆነውም የጠየቅነውን ያህል ሀብት አላገኘንም። ያገኘነው ከ500 እስከ 600 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ወጪ ያደረግነው ግን ከዛ በላይ 800 ሚሊዮን አካባቢ ነው። እኛ ካቀድነው አንዳንዴ 5 በመቶውን ብቻ የምንፈጽምበት ወቅት አለ። እኛ ምግብ ነክ የሆኑና ያልሆኑ ድጋፎችንም ጨምሮ ገንዘብም እንሰጣለን።
ዕርዳታ በማከፋፈሉ ሒደት በርካታ ቅሬታዎች ይቀርባሉ። አንድ ቦታ ብቻ ማተኮር፣ የቅርርብ ሥራን የተመለከተና የመዘግየት ስሞታዎች በተደጋጋሚ ከመነሳታቸው አኳያ የእናንተ ምላሽ ምንድን ነው?
ዕርዳታ ማከፋፈሉን በተመለከተ፣ አንደኛ በየክልሎች ባሉ ቅርንጫፎች የዳሰሳ ጥናት ይካሔዳል። ቀጥሎ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር የተቋቋመ ግብረኃይል አለ፤ ከእሱ ጋር በመሆን በአካባቢው ያለ ፍላጎት ምንድን ነው በሚል ለማወቅ ይሞከራል። ከላኩልን መረጃ ተነስተን ምን ያህሉን መርዳት እንደምንችል እኛ እንወስናለን።
በዕርዳታ ማከፋፈሉ ሒደት ትልቁ ያጋጠመን ችግር የጊዜ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ፣ ወልዲያ ላይ ለማከፋፈል ሁሉን የማጣራትና የመመዝገብ ሥራ ከጨረስን በኋላ ከተማዋ በመያዟ ተፈናቃዩ ተበትኖ ወደደሴና አጎራባች ከተሞች መጥቶ እንደ አዲስ ለመጀመር ተገደን ነበር። ሌላው ከባንክ ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጋቸውን ራሳቸው እንዲገዙ ገንዘብ በምንሰጥበት ወቅት ከወቅታዊው ኹኔታ ጋር በተገናኘ ችግር ይገጥማል። እኛ በአብዛኛው ዱቄትና ዘይት የምንሰጥ ሲሆን፣ ለሕፃናት አልሚ ምግቦችን፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ እንደአካባቢው የኑሮ ውድነት ከ4ሺሕ እስከ 6ሺሕ ለኹለት ወር የሚሆን ገንዘብም እንሰጣለን። ይህን ለማድረግ ከባንኮች ጋር በተዋዋልነው መሠረት የሚጣራው ሥራ ሲካሄድ ጊዜ ይወስዳል። ሌላው የተፈናቃዩ ቁጥር ተለይቶ በአስተዳደሩ እስኪሰጠንም ጊዜ ይወስዳል።
በእንቅስቃሴ ላይ ከሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች ሌላው፣ ኹለት ሦስቴ ተፈናቅለው ገንዘብ ይገባላችኋል ጠብቁ ተብለው የሚጠብቁ ተፈናቃዮች ጉዳይ ነው። ጦርነቱ የፈጠረው ቀውስ ብዙ ነገር ያስከትላል። በዚህ ዓይነት ወቅት ችግር የሚጠበቅ ነው። አምቡላንሶቻችን በጎ ፈቃደኞቻችንና ሠራተኞቻችን ሊጎዱ ይችላሉ። ለምሳሌ አንዳንድ ከተሞች ከተያዙ በኋላ አብረውን ከሚሠሩ ጋር የነበረን ግንኙነት ተቋርጧል። ደሴ ላይ ግን ከኹለት ሳምንት በፊት ሠራተኞቻችን በዓለም ምግብ ድርጅት በኩል ሠላም መሆናቸውንና የመድኃኒት እጥረት መኖሩን መልዕክት ልከውልናል (ኢሜል አድርገውልናል)። በርካታ ተግዳሮቶች ቢገጥሙም እነሱን እያለፍን ሥራችንን እያከናወንን እንገኛለን።
አንዳንድ አምቡላንሶቻችሁ ቁስለኛ ለማምጣት አንሄድም እንደሚሉና ሌሎች ደግሞ ከሚጠበቅባቸውም በላይ አማራጭ እያጡ በአንድ ጊዜ አራት ያህል ቁስለኞችን ለረጅም ርቀት ሲያጓጉዙ እንደነበር ተሰምቷል። ሠራተኞቻችሁን ወደ ጦር ቀጠና ሒዱና አገልግሉ ብላችሁ ማስገደድ ትችላላችሁ?
በጣም አስቸጋሪ ነው። ጦርነቱ በተቀሰቀሰ ሰሞን በሰሜን ምዕራብ ቀጠና ጥሪ ቀርቦልን ተንቀሳቅሰን ነበር። ቁስለኞችን እስከጎንደር፣ በወሎ በኩልም ደሴ ድረስ ወደ ሕክምና ተቋማት ስናመላልስ ነበር። ትግራይ ውስጥ 256 የሚሆኑ አምቡላንሶች ነበሩ። እነሱና በጎ ፈቃደኞቻችን ውኃ በማቀበልና በሌላም ያግዙ ነበር። በወቅቱ ብዙዎቹ አምቡላንሶቻችን ተሰውረውብን ነበረ። አንዳንዶቹ በተፋላሚ ወገኖች ይወሰዱብንና አላግባብ ሲጠቀሙባቸው ታዝበናል። ጦርነት ባለበት አካባቢ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ ራሱ ከባድ ነው። በዚህን ዓይነት ወቅት ቆቦ፣ አላማጣ፣ጎንደር ወይም ማይካድራን የመሳሰሉ አካባቢዎች የአምቡላንስ ሹፌሮች ቁጭ ብለው ሲመለከቱ ማየት ያሳዝናል። ሰው ነጥቆ ሊወስድም ይችላል። ይህ በጦርነት ውስጥ ሊያጋጥም ይችላል። ሠራተኞቻችን ተገደው ካልሆነ በስተቀር ለማገልገል ዝግጁ ናቸው።
በእንዲህ ዓይነት ወቅት ሠራተኞቻችንም ሆኑ በጎ ፈቃደኞች መጎዳት የለባቸውም። ለእነሱም ደኅንነት ማሰብ አለብን። ለሕይወታቸው አስጊ እስካልሆነ ድረስ ግን ገለልተኛ ሆነው ሕብረተሰቡን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል። እስካሁን ሥራቸውን በተገቢው አልሠሩም የሚል ጥቆማ አልመጣልንም። የአካባቢው አስተዳደሮች አንዳንዴ አስገድደው ሊወስዱ ስለሚችሉና ሌሎች ተሸከርካሪዎች ሸሽተው ስለሚወጡ እኛ መቆየት ይጠበቅብናል። ያንን አጋጣሚ ተጠቅመው ልዩልዩ ወገኖች ሊያስገድዱም ሆነ አስፈራርተው ሊነጥቁ ይችላሉ።
በአንዳንድ ከተሞች ሠራተኞቻችን ግንኙነት ቢቋረጥብንም ከጦርነት ቀጠናው ሳይወጡ ቆይተዋል። አንዳንዴ አምቡላንሶች ቁስለኛ ይዘው ሔደው ወደቦታቸው ለመመለስ ያልቻሉ ሲኖሩ እንዲቀሩ ይደረጋል። ሥርጭቱ በአማራ ክልል ስር ስለሆነ ወደ ክልሉ ዋና ከተማ ወደባህር ዳር የምንልክበት ጊዜ አለ። በጦርነት ወቅት ተመሳሳይ ችግሮች ቢከሰትም፣ እንዲህ አደረጉ ወይም አላደረጉም የሚል ስሞታ እስካሁን ሪፖርት አልተደረገልንም። በማስረጃ የተደገፈና በማኅበረሰቡ የታየ ነገር ካለ ቢነገረንና ብናውቀው የምንማርበት ይሆናል።
አንዳንዴ ለአንድ ወገን ከለላ ሆነው የጦር መሣሪያ ማከማቻና መጓጓዣ አድርገው የተቋሙን ዓርማ እንደሚጠቀሙበት በተለያዩ አገራት ጭምር ይሰማል። ይህ ዓይነት ድርጊት እንዳይፈጸም ከማስተማር ባሻገር ሕጋዊ ዕርምጃ በሚመለከተው አካል እንዲወሰድ እናደርጋለን።
ከቀይ መስቀል ተግባራት መካከል የጦር ምርኮኞችን መጎብኘት አንዱ እንደሆነ ይነገራል። በዚህ ረገድ እስካሁን የጎበኛችኋቸው አሉ?
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበራት በውስጣቸው ሦስት አካላት አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ነው በግጭትና ጦርነት ውስጥ ስለተያዙ የጦር ምርከኞች የሚመለከተው። ሌላው የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚሰጠው አካል ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የማኅበራቱ ፌደሬሽን ተብሎ የተቋቋመው በሠላም ጊዜ፣ የተፈጥሮ አደጋ በሚደርስበትም ጊዜ በመደበኛነት ድጋፍ የሚያደርግ ነው። ብሔራዊዎቹ ደግሞ በኹለቱም ተፈጥሯዊም ሰው ሠራሽም አደጋ በሚከሰት ጊዜ እንዲያግዙ ተደርጎ ነው የተዋቀረው።
ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንዱ እስረኞችንና የጦር ምርኮኞችን መጎብኘት ነው። የተጠፋፉ ቤተሰቦችንም ማገናኘት ላይም ይሠራል። ይህ በምስጢር የሚሠራ እንደመሆኑ ዓለም አቀፉ ተቋምን የሚመለከት ነው። የራሳቸው ቢሮ ያላቸውና ላለፉት 40 ዓመታት ያህል አብረውን ሲሠሩ የነበሩ ናቸው። እነሱ በዚህ ረገድ ብዙ ሥራዎችን እየሠሩ ስለመሆኑ እርግጠኛ ብሆንም፣ ከእኛ ይልቅ ራሳቸው ቢናገሩ መልካም ነው።
ጦርነቱ ከተከሰተ ከባለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ማኅበራችሁ ላይ ምን ያህል ጉዳት ደርሷል? የወደመባችሁስ የንብረት መጠን ይታወቃል?
ይህን ለማወቅ ንብረት ቆጠራ ውስጥ ገና አልገባንም። በመጀመሪያ ወቅት ጦርነቱ ትግራይ ውስጥ እያለ በክልሉ ከነበሩን ከ200 በላይ አምቡላንሶች 60 የሚሆኑት ብቻ ነበሩ አገልግሎት የሚሰጡት።
ማኅበሩ ካሉት 600 ማይሞሉ አምቡላንሶች ከ200 በላይ ትግራይ ያሉ ናቸው ሲሉ፣ ከሲሦው በላይ የሚሆኑት የማኅበሩ አምቡላንሶች ትግራይ ክልል ነበር የሚሠሩት?
አዎ፣ በማኅበሩ ሥር ካሉ አምቡላንሶች ከአንድ ሦስተኛው በላይ ትግራይ ውስጥ ነው ሲያገለግሉ የነበሩት። ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከሺሕ በላይ አምቡላንሶች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉት። ከነዛ መካከል የተወሰኑትን በመጠቀም እነሱም ተመሳሳይ ሥራን ይሠራሉ። በትግራይ ከ20 ዓመታት ገደማ በፊት የነበሩ ባለሥልጣናት፣ ትግራይ ውስጥ ያለው ቀይ መስቀል ጥሩ አገልግሎት እየሠጠ ስለሆነ በትግራይ ጤና ቢሮ ሥር የነበሩ አምቡላንሶችን ያስተዳድር ብለው በጀቱን እያሰቡ በእኛ ሥር እንዲሆኑ ያስተላለፏቸው አምቡላንሶች አሉ። ከ100 በላይ የሚሆኑትን በሙሉ ነበር ከነበጀቱ ያስተላለፉት። እስከ 100 ሚሊየን ብር ድረስ የሚያድግ በጀት መድበው በአራት ቁጥር ታርጋ ሆነው ይሠሩ ነበር። የትግራይን ለየት የሚያደርገው ይህ ነው። አምቡላንሶቹ ታርጋ ሳይቀይሩ ሲሠሩ ስለነበር ነው ችግር ውስጥ የገባነው። እዛ የነበሩ መከላከያዎችም ጭምር የመንግሥት ንብረቶች ናቸው በሚል ደሞዙም ሲቆም እንዲቆሙ ተደርጎ ነበር።
ስለውድመቱ ስንመለስ፣ ገና ጦርነቱ ስላልተጠናቀቀ መረጃ ማግኘትም ስላልተቻለ የትኞቹ ወደሙ የትኞቹስ ተረፉ የሚለውን ለማወቅ አልቻልንም። አንዳንድ ቦታ ከምንሰማው ውጭ ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም። ለምሳሌ፣ ወለጋ አካባቢ በታጣቂ ቡድኖች ኹለት መቃጠላቸውን ሰምተናል። አዲግራትና አላማጣ የወደሙ ፋርማሲዎች መኖራቸውን ሰምተናል። እንደቀይ መስቀል ጦርነቱ ያስከተለውን ቀውስ ገና ማወቅ አልቻልንም። ለወደፊት የጉዳቱን መጠንና ዓይነት አውቀን ይፋ እናደርጋለን።
ትግራይ ክልል በመንግሥት ተሸከርካሪ የአምቡላንስ አገልግሎት መስጠታችሁን ተከትሎ ከተፈጠረው ችግር አኳያ ተመሳሳይ ሥራ ትቀጥላላችሁ ወይስ ኹሉም አካባቢ በተመጣጣኝ እኩል እንዲዳረስ አድርጋችሁ አገልግሎት ትሰጣላችሁ?
በመንግሥት ደረጃ ለአምቡላንሶቹ የሚበጀተውን ነበር ቀጥታ ለቀይ መስቀል የሚሰጡት። አምቡላንሶቹ ንብረትነታቸው የእነሱ ስለሆኑ ከአገር አቀፍ ሥርጭት አኳያ የሚቆጠሩት በጤና ቢሮ ካሉት ጋር ነው። እኛ ማስተዳደር እንጂ እንደእኛ አንቆጥራቸውም። እኛ ነጻና ገለልተኛ ሆነን ስለምንሠራ ለመንግሥትም ሪፖርት አናደርግም።
የእኛን አምቡላንሶች የሚገዛው የየአካባቢው ሕዝብ ነው። ለምሳሌ አንድ ወረዳ ላይ ለማቋቋም መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ። ይህን ያህል በጎ ፈቃደኛ፣ ይህን ያህል ብር በባንክ አካውንት፣ ይህን ያህል አባልና የአምቡላንስ አገልግሎት መስጠት የሚችል ተብሎ መስፈርቱን ከታለፈ ነው የሚፈቀደው። በወረዳም ሆነ በዞን ደረጃ የየራሱ መስፈርት አለው እንጂ የፈለገ ገንዘብ ስላለው ብቻ ገዝቶ አገልግሎት መስጠት አይችልም። ለምሳሌ፣ አንድ ወረዳ ተነስቶ 10 አምቡላንስ ልግዛ ቢል አይችልም።
ሌላ ወረዳ ምንም ሳይኖረው አንዱ መስፈርቶቹን አሟልቶ 10 ሊኖረው ይችላል ማለት ነው?
በኮታ ሳይሆን በመስፈርት ነው የምንሰራው። እኛ አይደለንም የምንገዛላቸው፤ ሕብረተሰቡ ራሱ ነው የሚገዛው። ነገር ግን ሁሌ በግዢ አይሆንም፤ በእርዳታ ሊገኝም ይችላል።
ግብረሠናይ ድርጅቶችን በተመለከተ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለውጭ ጫና የተጋለጡ ናቸው በሚል በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስሞታ ይቀርብባቸዋል። የእናንተን ማኅበር ጨምሮ በለጋሾች ተጽዕኖ ሥር ይወድቃሉ ስለመባሉ ምን አስተያየት አሎት?
እኛ በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ መርሆዎች መሠረት፣ በጄኔቫ ሕግጋትና ፕሮቶኮሎች መሠረት ነው የምንሠራው። ከእኛ ጋር መሥራት ከሚፈልጉ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ አብረውን ከሚሠሩ ዕርዳታ እናገኛለን። 8 ከሚሆኑ እህት ማኅበራትም ጋር አብረን እንሠራለን። ከ6 ሚሊዮን አባላቶቻችን የምንሰበስበው የአባልነት መዋጮ አለ። ወደ10 ሺሕ የሚሆኑ የድርጅት አባላትም አሉን። ከእነሱም የምንሰበስበው ገንዘብ አለ። መንግሥትም ድጎማ ያደርግልናል። ከገቢ ማስገኛ ሕንጻዎቻችን፣ ከፋርማሲዎቻችንና ከሌሎችም የምናገኘው ገቢ አለ። በአጠቃላይ 200 ሚሊዮን ገደማ ከውስጥ ገቢ እንሰበስባለን። ይህን ደሞዝን ለመሳሰሉ ለተለያዩ ወጪዎቻችን እናውለዋለን። ክልሎችም ከሚሰበስቡት ለእኛ ፈሰስ የሚያደርጉት እስከ 30 በመቶ ገቢያቸው ቢኖርም፣ አንዳንዶች ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ የማንቀበላቸው ጊዜ አለ። ለዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ኮሚቴም ዓመታዊ መዋጮ እንከፍላለን። በአጠቃላይ ከእነዚህ መንገዶች ካገኘነውና በተለያዩ ምክንያቶች ከማኅበረሰቡ ከምንሰበስበው ላይ ነው ዕርዳታ የምንሰጠው።
ተጽዕኖ ሥር ትወድቃላችሁ ለሚባለው ለምሳሌ፣ የአንድ አብሮን የሚሠራ የውጭ አገር ዕርዳታ ተቋም አሰባስቦ ያመጣውን ዶላር በአገሩ መንግሥት በተቋቋመው የዕርዳታ ተቋም አማካይነት ከእኛ ጋር በሚፈራረሙት መርህ መሠረት ከእኛ ጋር አብረው ለመሥራት ይፈልጋሉ። የእኛ መዋቅራችን ሠፊ ስለሆነና ብዙ ወጪ ስለማያስወጣቸው እኛን ተጠቅመው ዕርዳታ ማድረስ ይፈልጋሉ። እኛ በዚህ ዓይነት አሠራራችን ምክንያት የመጣብን ምንም አይነት ተጽዕኖ የለም። እኛ ከጀርባ ሆነው ከሚለግሱ (ባክ ዶነርስ) ጋር ምንም ግንኙነት የለንም። እኛ ግንኙነታችን አብረውን ከሚሠሩ እህት ማኅበራት ጋር ነው። አብረን ለመሥራት የምንፈራረማቸው ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ጦር መሣሪያንም ሆነ ሲጋራ ንግድ ጋር በመሳሰሉ ድርጊቶች የሚሳተፉ ከሆነ አብረናቸው አንሰራም።
ምዕራባውያኑ እንደእናንተ ዓይነት ግብረ-ሠናይ ተቋማትን ዓላማቸውን ለማስፈጸም ይጠቀሙበታል መባሉንስ እንዴት ያዩታል?
በዚህ ጉዳይ አቋማችን ግልጽ ነው። ሰብዓዊነትን የሚጎዳ፣ ገለልተኛነታችንን የሚያሳጣን ተግባር ውስጥ እንደማንገባ ስምምነታችን ውስጥም እናካትታለን። መርሃችን በማናቸውም መንገድ ወገን እንድንይዝ አይፈቅድም። ሠራተኞቻችን የዚህን መርህ ተፃራሪ በሆነ መልኩ ሲሠሩ ከተገኙ በቀጥታ እናባርራለን። ማንኛውም አካል ሠራተኞቻችን በማይገባቸው ተግባር ላይ ስለመሳተፋቸው ማስረጃ ካቀረበልን ዕርምጃ እንወስዳለን።
ለሕዝብ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
ባለፉት 86 ዓመታት የተፈጥሮ አደጋም ሆነ ሰው ሠራሽ ጦርነትን የመሳሰሉ አደጋዎች ሲኖሩ ሕብረተሰቡ ሰብዓዊነትን በመደገፍ ልዩ ልዩ ዕርዳታዎችን ሲያደርግልን ቆይቷል። በተለያዩ መንገዶች ለደገፉን ምስጋናችንን እያቀረብን፣ በተለያዩ ባንኮች ባሉን አካውንቶችና በዘረጋናቸው የ‹ኦንላይን› አማራጮች ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን። በግቢያችንም ውስጥ ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን የማይበላሹ ምግቦችንና አልባሳትን እያሰባሰብን ለሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ስለምናዳርስ ኹሉም የተቻለውን እንዲያግዝ መልዕክት እናስተላልፋለን። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ገና ስለሚቀር፣ ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ሕብረተሰቡ ልገሳውን እንዲያጠናክር እንጠይቃለን።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014



