የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ እየተሸጡ መሆኑ ተሠማ

0
877

ለልማት አገልግሎት በሚል መሬታቸውን ተነጥቀው የቆዩና በ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሳቸው አርሶ አደሮች፣ ቤት ቢደርሳቸውም ለማጠናቀቂያ (finishing) የሚሆን በቂ ገንዘብ ስለሌላቸው ቤቶቹን በሕገ-ወጥ መንገድ እየሸጡ መሆኑን አስተያየት ሰጭዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ከአስተያየት ሰጭዎቹ መካካል ኃይለሚካኤል አቦነህ የተባሉት ግለሰብ እንደሚሉት፣ ለልማት ዝርጋታ ተብሎ መሬታቸው በመንግሥት የተወሠደባቸው አርሶ አደሮች፣ ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኋላ በምትኩ ቤት ቢደርሳቸውም፣ በገንዘብ ችግር ምክንያት አጠናቀው መግባት ባለመቻላቸው ቤቶቹን በሕገ-ወጥ መንገድ እየሸጡ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሕግ መሠረት ቤት መሸጥ አይቻልም የሚሉት ግለሰቡ፣ ነገር ግን በርካታ አርሶ አደሮች ቤታቸውን እየሸጡ ነው ብለዋል። ለአብነትም “ጓደኛዬ ሽጧል” ሲሉ ዕማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
መሸጥ አይቻልም ይባላል እንጂ ሲቻል አይተናል የሚሉት ኃይለሚካኤል፣ ብዙ ሰዎች “በየትኛው ገንዘቤ ቤቱን አሟልቼ ልገባ እችላለሁ” በማለት በጣም በወረደ ዋጋ እየሸጡ ነው ብለዋል።

“መጀመሪያ ላይ በነበረው ውይይት ቤቱ ከተሠጠን በኋላ መሟላት ያለባቸው ነገሮች በመንግሥት እንደሚሸፈኑ በኮሚቴዎች አማካይነት ቃል ተገብቶልን ነበር” ያሉት ግለሰቡ፣ ነገር ግን የተገባው ቃል ተግባራዊ እየሆነ አይደለም ብለዋል።
የደረሰን ቤት የመብራት፣ የውኃ እንዲሁም የመንገድ አገልግሎት የለውም፤ ወጭውን መንግሥት ይሸፍናል። የሚቀሩትን ሥራዎች ለማጠናቀቅ ደግሞ በየሙያ መስካችሁ ተደራጁ እያሉን ቢቆዩም፣ ቁልፉን ካስረከቡን በኋላ ግን ዙረው አልተመለከቱንም ብለዋል ኃይለሚካኤል።

ሌላኛው ገብረመስቀል አቦነህ የተባሉት ግለሰብ በበኩላቸው ለልማት ተብሎ አንድ ሰው እስከ 20ሺሕ ካሬ መሬት ተወስዶበታል ያሉ ሲሆን፣ በወቅቱ በምትኩ የሚሠጣቸው ቤት እስከ መጨረሻው (ፊኒሽንጉ) ድረስ የሚሟላ እንደነበር ቢነገራቸውም፣ አሁን እየሆነ ያለው በተቃራኒው ነው ብለዋል።

የተሠጠን ቤት የተሟላ አይደለም የሚሉት ገብረመስቀል፣ ቤቱን ሙሉ አድርጎ ለመግባት እስከ 200ሺሕ ብር ስለሚጠይቅና አርሶ አደሮቹ ደግሞ ይህን የማድረግ አቅም ስለሌላቸው፣ ቤቱን ለመሸጥ እየተገደዱ መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል።
ግለሰቡ ጉዳዩን በተመለከተ የተመደቡ ተወካዮችን በቅርቡ ጠይቀው፣ “መንግሥት መፍትሔ ይሰጣል” የሚል ምላሽ ቢያገኙም፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ መፍትሔ እንዳላገኙ ነው ያስረዱት።
ቤቱን አሟልቶ ከማስረከብ በተጨማሪ፣ ለመተዳደሪያ የሚሆኑ ሱቆችን በየኮንደሚኒየሙ እንደሚሰጡን ቃል ገብተውልን ነበር የሚሉት ገብረመስቀል፣ ይህ ቃልም ተግባራዊ አልሆነም ሲሉ ነው ያስረዱት።

ግለሰቡ አክለውም፣ አርሶ አደሩ በግብርና ሥራ ሲተዳደር የነበረ መሆኑን ጠቁመው፣ በተነጠቀው መሬት ምትክ ቃል በተገባለት መሠረት የተሟላ ቤት ሊሰጠው ይገባል እንጂ 200ሺሕ ብር ከየት አምጥቶ የቤቱን ግንባታ ሊያጠናቅቅ ይችላል? ሲሉ ጠይቀዋል::
ሌላኛው ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብም በበኩላቸው፣ “የአርሶ አደር ልጆች ስለሆን ቤቱን አሟልተን መግባት አልቻልንም፤ በመሆኑም መንግሥት በገባልን ቃል መሠረት ቤቱን አጠናቆ ሊሰጠን ይገባል” ነው ያሉት።
አክለውም፣ እስካሁን ቤት ያልደረሳቸው ሰዎች መኖራቸውን የጠቆሙ ሲሆን፣ ቤት ደረሳቸው የተባሉት አርሶ አደሮች ደግሞ ቤቱን ለማሟላት የሚጠይቀው ወጭ ብዙ በመሆኑ መግባት እንዳልቻሉ ነው ያብራሩት።

አዲስ ማለዳ የቅሬታ አቅራቢዎቹን ጥያቄ ይዛ ከአዲስ አባባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የግንባታ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቶማስ ደበሌ ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ ቤቱን መሸጥ እንደማይቻልና ችግሩ ሊቀረፍ እንደሚችል በሚከተለው መልኩ አብራርተዋል።
ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ሥራዎች እንደተጓተቱ የገለጹት ቶማስ፣ ባለን የፋይናንስ አቅም መሠረት መሠረታዊ ሥራዎችን አጠናቀን ያስረከብናቸው ቤቶች አሉ። ቀሪዎቹን ደግሞ አጠናቀን እናስረክባለን ነው ያሉት።
አያይዘውም፣ ቃላችንን አናጥፍም፤ ግዴታችንን እንወጣለን፤ ግን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያለውን ወቅታዊ ኹኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡልን ሲሉ አስረድተዋል።

በከተማዋ ከ2ሺሕ 222 በላይ ሕንጻዎች አሉ ያሉት ቶማስ፣ ኹሉንም በአንድ ጊዜ አጠናቆ ማስረከብ ስላልተቻለ ነው እንጅ መንግሥትም አልሠራም አላለም ብለዋል።
ቶማስ አክለውም፣ የ20/80 ሱቆች ለነዋሪዎቹ ለመሰጠት ዝግጁ አይደሉም፤ ዝግጁ ሲሆኑ ግን የሚሰጧቸው ይሆናል ያሉ ሲሆን፣ በተረፈ ማንኛውም ቅሬታ አቅራቢ ቢሮ መጥቶ ጥያቄውን ያቅርብና ምላሹ እንሠጣለን ሲሉ ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here