የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እና የዋጋ ግሽበት

0
1990

በኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ከተያዘው ታኅሳስ 1/2014 ጀምሮ ቀድሞ ይሸጥበት በነበረው ዋጋ ላይ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ የተደረገው ማሻሻያ በአንድ ሊትር እስከ አምስት ብር የሚደርስ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርብበት ዋጋ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑ መረጃዎች ያሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ የነዳድ ምርቶች መሸጫ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ የሆነው፣ መንግሥት ገበያ ለማረጋጋት ከሚያደርጋቸው ድጎማዎች ውስጥ በመካተቱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚቀርበውን የነዳጅ ምርት ወጪ 75 በመቶ የሚሆነውን መንግሥት እየሸፈነ እንደነበር መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

ይሁን እንጅ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ የተደረገው የነዳጅ መርቶች መሸጫ ዋጋ ጭማሪ፣ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የታሪፍ ጭማሪ ማስከትሉን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ አሁን ባለው የዋጋ ግሽበት ላይ ሌላ አቀጣጣይ ምክንያት እንዳይሆን ተስግቷል፡፡
አዲስ የተደረገው የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ከዓለም የነዳጅ ዋጋ መጨር እና በኢትዮጵያ አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ መንግሥት ያለበትን ወጭ ለመቀነስ የታሰበ እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙዎች ይገልጻሉ፡፡

በሰሜኑ በኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንደጎዳው ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ኢኮኖሚው የዋጋ ግሽበት እና የጦርነት ጫና እያስተናገድ ባለበት ሁኔታ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ችግሩን እንዳይባባስ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚሻ ባለሙዎች ይጠቁማሉ፡፡ የነዳጅ መርቶች መሸጫ ዋጋ ጭማሪ መሳየቱን በዋጋ ግሽበት ላይ የሚያስከትለውን ተጽዖኖ የአዲስ ማለዳው መርሸ ጥሩነህ ባለሙያዎችን አነጋግሮ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አደርጎታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ ምርቶችን የማቅረብ እና የመሸጫ ዋጋ የመተመን ሥልጣን ያለው ሲሆን፣ በዚህም የነዳጅ ምርቶችን የመሸጫ ዋጋን በየወሩ ይከልሳል። የነዳጅ ዋጋ በየወሩ እንደየሁኔታው የሚከለስ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ወራት ከአውሮፕላን ነዳጅ ውጭ ያሉት የነዳጅ ምርቶች ባሉበት ዋጋ እረግተው እንዲቆዩ ሲደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

ባሳለፍነው ሣምንት የታኅሳስ ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ አዲስ የዋጋ ማስተካከያ ማደረጉን የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር መግለጹ የሚታወስ ነው። አዲስ በተደረገው የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ማሻሻያ መሠረት፣ ቤንዚን ላይ በተደረገ የዋጋ ማስተካከያ ባለፈው ወር ሲሸጥበት ከነበረው ዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሊትር 31 ብር ከ74 ሣንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል።

እንዲሁም፣ ነጭ ናፍጣ 28 ብር ከ94 ሣንቲም፣ ነጭ ጋዝ 28 ብር ከ94 ሣንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 23 ብር ከ73 ሣንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 23 ብር ከ29 ሣንቲም፣ እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ 58 ብር ከ77 ሣንቲም እንድሸጥ ተወስኗል። የዋጋ ማሻሻያው ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የነዳጅ ማከፋፋያ ጣቢያዎች በአዲሱ ዋጋ እየሸጡ ይገኛሉ።

አዲስ የተደረገው የነዳጅ ምርቶች የዋጋ ጭማሪ፣ የዓለም አቀፍ ነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ከዚህ በፊት ከነበሩት ጊዜያት በላይ ከፍተኛ ጉድለት ያስከተለ በመሆኑ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ማሻሻያው ያስፈለገው፣ የአገር ውስጥ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ከጎረቤት አገራት የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር እስከ 100 ፐርስንት ልዩነት በማሳየቱ እና ምርቱ ለከፍተኛ ኮንትሮባንድ የተጋለጠ በመሆኑ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋን መከለስ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።

የታኅሳስ ወር 2014 የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ በ2013 ጥር ወር ላይ ከተደረገው የዋጋ ማስተካከያ ቀጥሎ የተደረገ ጭማሪ ሲሆን፣ አዲሱ ማስተካከያ በ2013 በጥር ወር ከተደረገው የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር እስከ አምስት ብር ብልጫ አለው።
በ2013 ጥር ወር ላይ የተደረገው ማስተካከያ ከአሁኑ ጋር መሸጫ ዋጋ ጋር በሊትር ሲነጻጸር፣ ቤንዚን ከ25 ብር ከ82 ሣንቲም ወደ 32 ብር ከ74 ሣንቲም፣ ነጭ ናፍጣ ከ23 ከ04 ሣንቲም ወደ 28 ብር ከ94 ሣንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ ከ20 ከ27 ሣንቲም ወደ 23 ብር ከ73 ሣንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ ከ19 ብር ከ77 ሣንቲም ወደ 23 ብር ከ29 ሣንቲም፣ እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ ከ35 ብር ከ12 ሣንቲም ወደ 58 ብር ከ77 ሣንቲም ከፍ ብሏል።

በነዳጅ ምርቶች ላይ የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ላይ የተወሰነ የታሪፍ ማሻሻያ መደረጉም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አርብ ታኅሳስ 8/2014 በተሰጠው መግለጫ ገልጿል። በዚህም የታሪፍ ማሻሻያው ከዚህ በፊት በነበረው የጭነት እና የሕዝብ ትራንሥፖርት አገልግሎት ዋጋ ጭማሪ ማድረጉ፣ በሌሎች አገልግሎቶች እና ምርቶች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት እንደሚያደርግ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሌሎች ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመጣው የዋጋ ግሽበት ላይ ሌላ አቀጣጣይ ምክንያት እንደሚሆን በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ክፍሉ ደገፉ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

“የነዳጅ ዋጋ መጨመር ዋነኛ የዋጋ ግሽበት አቀጣጣይ ነው” የሚሉት ክፍሉ፣ መንግሥት የዋጋ ጭማሪውን ካለው ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር ያለበትን ጫና ለመቀነስ ያደረገው ቢሆንም፣ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዖኖ ቀላል አለመሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ገበያ የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየወሩ የሚያወጣው ሪፖርት ያመላክታል። በኢትዮጵያ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በአንድ ምርት ላይ የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ ሲደረግ የሌሎች ምርቶች መሸጫ ዋጋ አብሮ ማደጉ የተለመደ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው።

የኢኮኖሚ ተንታኝ የሆኑ ሥማቸው እንዲጠቀሰ ያልፈለጉ ባለሙያ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በኢትዮጵያ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በአንድ ምርት የዋጋ መጨመር ላይ ስበብ አድርጎ የሚከስት ነው ይላሉ። ለዚህም እንደ ማሳያ የሚያነሱት ከዚህ ቀደም የዶላር ምንዛሬ ጭማሪ ሲከሠት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከዶላር ጋር የማይገኛኙ ምርቶች ሳይቀሩ ለዋጋ ግሽበቱ ሠበብ ምክንያት መሆናቸውን በማንሣት ነው።

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚነካቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ አስገዳጅ ነው የሚሉት ባለሙያው፣ የትራንሥፖርት ዋጋ ሲጨምር በትራንሥፖርት ተጓጉዘው ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች መሸጫ ዋጋቸው መጨመሩ የማይቀር ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶችን ለገበያ የምታቀርብበት ዋጋ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር አናሳ ቢሆንም፣ በሌሎች ምርቶች ላይ የዋጋ መናር እንዳይፈጥርና ገበያ ለማረጋጋት መንግሥት ከውጭ የሚያስገባውን ነዳጅ በኪሳራ እንደሚሽጥ መገለጹ የሚታወስ ነው።
ከሰሞኑ ከተደረገው የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ ከአንድ ዓመት በፊት በ2013 በጀት ዓመት የጥር ወር ተድርጎ በነበረው ክለሳ፣ በወቅቱ በነበረው የትራንሥፖርት ዋጋ ላይ እና ተያያዥ አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ የሚታወስ ነው። በወቅቱ የተደረገውን ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ መንግሥት የትራንሥፖርት ታሪፍ ማሻሻያ ቢያደርግም፣ የተደረገው ማሻሻያ ተመጣጣኝ አይደለም በሚል አድማ የትራንሥፖርት አገልግሎት በመቋረጡ፣ ተጠቃሚዎች ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ በዕጥፍ እንዲከፍሉ ተገደው እንደነበር አዲስ ማለዳ በወቅቱ መዘገቧ ይታወሳል።

በ2013 ጥር ወር ላይ ተደርጎ የነበረው የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ማሻሻያ፣ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ መሆኑን መንግሥት መግለጹ የሚታውስ ነው። ከ2011 ሚያዝያ ወር ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ቢያሳይም፣ መንግሥት ጭማሪውን በመሸፈን እስከ 2013 ጥር ወር ድርስ 24.05 ቢሊዮን ብር ማውጣቱን መግለጹ የሚታወስ ነው።

በወቅቱ በተደረገው ማሻሻያ ወቅትም እንደተነገረው፣ በዓለም ገበያ ጭማሪ እያሳየ የመጣውን የነዳጅ ዋጋ መንግሥት ኹሉንም የዋጋ ጭማሪ ሸፍኖ ከሔደ በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጸዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ፣ መንግሥት 75 በመቶውን ሸፍኖ፣ ቀሪው 25 በመቶ ደግሞ ሕብረተሰቡ እንዲሸፈን ማድረጉን ገልጾ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በ2013 በአራት ዙር ያወጣቸው ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ከውጭ ላስገባቻቸው የነዳጅ ምርቶች 72.6 ቢሊዮን ብር ወጭ አድርጋለች።

የአራቱን ሩብ ዓመታት በቅደም ተከትል ስንመለከት፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 878.7 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የነዳጅ ምርቶችን አስገብታ 12.8 ቢሊዮን ብር ። በኹለተኛው ሩብ ዓመት 937.9 ሺሕ ሜትሪክ ቶን አስገብታ 14.7 ቢሊዮን ብር ፣ በሦስተኛው ሩብ ዓመት 960 ሺሕ ሜትሪክ ቶን አስገብታ 20.8 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም በአራተኛው ሩብ ዓመት 943.1 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የነዳጅ ምርቶች አስገብታ 24.3 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጋለች።

የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት እንደሚያሳው ኢትዮጵያ ለምታስገባቸው የነዳጅ ምርቶች የምታወጣው ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ነው። ለምሳሌ የአራተኛውን ሩብ ዓመት ብንመለከት ያስገባችው የነዳጅ ምርት መጠን ከሦስተኛው ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጽር የ16.9 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቅናሽ ቢያሳይም የተከፈለው ብር በተቃራኒው ጨምሯል።

የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ በመጣበት በዚህ ወቅት የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ሌላ አቀጣጣይ ምክንያት እንዳይሆን ከወዲሁ ስጋት ፈጥሯል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ግሽበት ኹኔታ በተመለከተ፣ አስከ ባለፈው ኅዳር/2014 ያለው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ33 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በቅርቡ ባወጣው ሪፖት መግለጹ የሚታወስ ነው። የባለፈው ኅዳር ወር የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው 2013 ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ38.9 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።

ያለፈው ኅዳር ወር ከጥቅምት ወር ጋር ሲነጻጸር በእህሎች፣ በአትክልትና ጥራጥሬ ዋጋ በአብዛኛው ቅናሽ አሳይቷል። ሩዝ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ሽንብራና ምሥር የዋጋ መጠነኛ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል። በተጨማሪም ሥጋ፣ ወተት፣ አይብና ዕንቁላል፣ ቅመማ ቅመም (በዋናነት ጨውና በርበሬ) ቅናሽ አሳይተዋል።

የምግብ ዘይትና ቅቤ በመጠኑ ቅናሽ ያሳዩ ሲሆን፣ በአንፃሩ ቡናና ለስለሳ መጠጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የ‹ኢንዴክሱ› ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25.2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ አነቃቂዎች (ጫት)፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጅ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች (የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማሰገጫዎች፣ ሕክምና እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው ተብሏል።

አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ጥቅምት ወር 2014 ጋር ሲነጻጸር በ0.6 መቶ እና የምግብ የኢንደክሱ ክፍሎች በ1.7 መቶ ቅናሽ አሳይተዋል። በተመሳሳይ ወቅት የምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት በ1.0 ነጥብ ከመቶኛ ጭማሪ አለው። ባለፈው ወር 34.2 በመቶ ከደረሰ በኋላ፣ በኅዳር 2014 ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ወደ 33 በመቶ ዝቅ ብሏል።

የኅዳር 2014 ወራዊ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ1.8 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት 1.0 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የረዥም ጊዜ ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት አዝማሚያ እንደሚያሳየው ከመኸር ወቅት የግብርና ምርት ጋር በተያያዘ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት የምግብ ዋጋ ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል።

ይሁን እንጂ፣ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን የምግብ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ በነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ ሊስተጓጎል እንደሚችል እየተገለጸ ነው። የነዳጅ ምርቶች የዋጋ መጨመር የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ማስከተሉን ተከትሎ፣ ከገጠር ወደ ከተማ ተጓጉዘው ለገበያ በሚቀርቡ የምግብ ፍጆታዎች ላይ ጭማሪ ማስከተሉ አይቀሬ መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢኮኖሚ ተንታኝ ጠቁመዋል።

መንግሥት በየጊዜው እያሻቀበ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር እስካሁን ተሸክሞ የቆየውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የማይቻል መሆኑን የሚገልጹት ክፍሉ(ዶ/ር)፣ መንግሥት ለወቅታዊ ሁኔታ የሚያወጣውን ወጭ ለመሸፈን የሚያወጣው ወጭ በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ለማድርግ ምክንያት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጅ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ ማድረጉ በየጊዜው እያደገ በመጣው የዋጋ ግሽበት ላይ ተጨማሪ ትኩሳት እንዳይሆን ሥጋት አላቸው። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በመጣው የትራንሥፖርት ዋጋ ጭማሪ ሌሎች ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ከተከሰተ አሁን ባለው የዋጋ ንረት ላይ ተጨማሪ ችግር ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

የኢኮኖሚ ተንታኙ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ እየተለመደ የመጣው በአንድ ምርት ዋጋ መጨመር ምክንያት ሌሎች ምርቶች ላይ የሚከሰተው የዋጋ ጭማሪ በነዳጅ ላይ ሲሆን ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁመዋል። የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ በተደረገው የትራንሥፖርት ጭማሪ፣ በተለይ በምግብ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ የማይቀር መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት አሁን እየገሰገሰ ባለበት ኹኔታ ከቀጠለ፣ በጦርነት ከተጎዳው ኢኮኖሚ ጋር ተደራርቦ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ እንደሚሆን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪው ይገልጻሉ።

የዋጋ ንረቱ እንዳይቀጣጠል ምን ይደረግ?
በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ለመጣው የዋጋ ግሽበት እንደ ምክንያት ከሚነሱት መካከል የብር ሥርጭት መጠን መጨመር አንዱ መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ኹለቱም ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የኢኮኖሚ ተንታኙ፣ በኢትዮጵያ ለሚታየው የዋጋ ግሽበት ከብር ሥርጭት መጠን መብዛት በተጨማሪ፣ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ አባባሽ ምክንያቶች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። የነዳጅ ዋጋ መጨመር ደግሞ ብዙ ነገሮችን ስለሚያጣቅስ ችግሩን ሊያባብሰው እንደሚችል ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ከገጠመው ወቅታዊ ኹኔታ ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ መግባቱን ተከትሎ መንግሥት ያለበትን ወጪ ለመሸፈን ስለሚቸገር የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማድረጉ በራሱ የሚኮነን አለመሆኑን ተመራማሪው ይገልጻሉ። አሁን ባለው ወቅታዊ ኹኔታ መንግሥት ካለበት ወጪ አንጻር የነዳጅ ምርቶች ጭማሪን መሸከም እንደማይችል ኹለቱም ባለሙያዎች ይስማማሉ።

ይሁን እንጅ፣ የተደረገው የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ጭማሪ አሁን ካለው ወቅታዊ ኹኔታ ጋር ተዳምሮ የዋጋ ግሽበቱን እንዳያባብሰው ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያስፈለግ ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል።

የኢኮኖሚ ተንታኙ አክለውም ከነዳጅ ምርቶች የዋጋ ጭማሪ ጋር ግንኙነት ያላቸው አገልግሎቶችና ምርቶች ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ፣ ግንኙነት ወደሌላቸው ምርቶች እንዳይሸጋገር በተቆጣጣሪ አካላት በኩል ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪን ከመቆጣጠር በተጨማሪ፣ ምናልባትም አዳዲስ የቁጥጥር ሥርዓቶች እስከ መዘርጋት የሚደርስ ሥርዓት መትከል እንደሚገባ እና ተገቢ ያልሆነ የብር ሥርጭትን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here