በሱማሌ ክልል የተፈጠረውን ኹከትና ረብሻ መርተዋል በማለት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የቀድሞ የክልሉን ፕሬዝዳንት አብዲ ሙሐመድ ኡመርን (አብዲ ኢሌ) ጨምሮ በሌሎች 47 ሰዎች ላይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክሱን ረቡዕ፣ ጥር 29 ቀን አሰማ። በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾቹ፥ ቀኑ በግልጽ ባለታወቀ በሰኔ ወር 2010 በሱማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎቸ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ የጦር መሣሪያ እንዲያነሳ በማድረግ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ መንቀሳቀሳቸው በክሱ ተነቦላችዋል።
በዚህም በአንዳንድ የሶማሌ ብሔር ተወላጆች እና በሶማሌ ክልል በሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር በማሰብ በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶችን ማደራጀታቸውም በክሱ ተነስቷል።
የዐቃቢ ሕግ ክስ የተደራጀውን የወጣት ቡድን (ሄጎ) በገንዘብ እና በተለያዩ ቁሳቁሶች በመደገፍ፣ በጦር መሣሪያ ድጋፍ በማድረግ፣ ግጭቱ የሚመራበትና መልዕክት የሚተላለፍበት ሄጎ ዋሄገን የሚል የፌስቡክ ገጽ በመክፈትና በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ሰዎችን ሊያነሳሱ የሚችሉ መልዕክቶችን እንዲተላለፍ አድርገዋል ብሏል።
እንዲሁም በክልሉ ውስጥ ግጭት እንዲነሳ በማድረግና በግጭቱ ምክንያት የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ በመንግሥት እና በእምነት ተቋማት እንዲሁም በግለሰብ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ፣ ሴቶች እንዲደፈሩ እንዲሁም ኅብረተሰቡ እንዲፈናቀል ማድረጋቸውም በክሱ ተካቷል። በዚህም ተከሳሾች በፈፀሙት የጦር መሣሪያ ይዞ በማመጽ ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግሥት ላይ የሚደረግ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ከጥር 22 በተለዋጭ ቀጠሮ የቀረቡትና በዕለቱ የቀረበባቸውን ክስ ተረድተውት እንደሆነ የተጠየቁት የቀድሞ ፕሬዝዳንት አብዲ ሙሐመድ “ክሱን ተረድቸዋለው፥ ይሁን እንጂ የቀረበብኝ ክስ ሙሉ በሙሉ ከእውነት የራቀ ነው፤ ምንም የፈጸምኩት ወንጀል የለም” ሲሉ ለችሎቱ ገልጸዋል። ከአብዲ ሙሐመድ በተጨማሪም ራህማ መሀመድ ሀይቤ፣ አብዱራዛቅ ሰሀኔ ኢልሚ፣ ፈርሃን ጣሂር በርከሌ፣ ጉሌድ ኦበል ዳውድ እና ወርሰሜ ሼህ አብዲ ሸሂድን በችሎቱ ተገኝተው ክሳቸውን አዳምጠዋል። ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ ያቀረበውን መረጃ አያይዞ እንዲሰጣቸው የተከሳሽ ጠበቆች የጠየቁ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ማስረጃዎችን የመስጠት ኃላፊነት የለብኝም በሚል ተከራክሯል።
ክርክሩን ያዳመጠው ችሎቱም ዐቃቤ ሕግ መረጃዎችን ይዞ እንዲቀርብ በማዘዝ ለየካቲት 5 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011