የዛዲግና ሕወሓት ፍቺ

0
562

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ዛዲግ አብርሃ ከሕወሓት ለመልቀቅ ጥያቄ ማስገባታቸው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በርካቶች ሲቀባበሏቸው ከሰነበቱ ጉዳዮች አንዱ ነው።

ለትምህርት ሔደው በእንግሊዝ ለንደን የሚገኙት ዛዲግ ከሕወሓት ጋር ለመለያየት ያስወሰናቸው ምክንያቶች በዋናነት ኹለት መሆናቸውን ገልጸዋል። አንዱ ድርጅታቸው ሕወሓት በእነ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና ደመቀ መኮንን መሪነት የመጣውን የለውጥ ጉዞ ለመቀበል እየዳዳው ሲያልፍም ለውጡን እየተቃወመ መሆኑ ነው። ሕወሓት በተዳጋጋሚ ከፌደራሉ መንግሥትና ከመሪው ግንባር ኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ጋር አልተጣጣመም በሚል ሲተች ይሰማል።

ኹለተኛው የዛዲግ ምክንያት በራያ የተነሳው የማንነት ጥያቄ ሲሆን የዛዲግን የትውልድ አካባቢ ራያን የሚያስተዳድረው የትግራይ ክልል መንግሥት ምላሹ አፈ ሙዝ በመሆኑ እንደሆነ ገልፀዋል። በዚህ የተከፉት ዛዲግ የሕወሓትን ምላሽ የኮነኑ ሲሆን ከድርጅቱ ጋር መቀጠል አለመፈለጋቸውን ገልጸው መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል።

ዛዲግ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚንስትር ዴኤታ እንዲሁም የጠቅላይ ሚንስትሩ የሚዲያና ዴሊቨሪ ዩኒት ሚንስትር ሆነውም አገልግለዋል።

በሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ያገለገሉት ዛዲግ ከሕወሓት አባልነታቸው ራሳቸውን ባገለሉበት ደብዳቤ በቀጣይ ከሳቸው እሳቤ ጋር የሚስማማ መርህ ያለውን ድርጅት ተቀላቅለው እንደሚታገሉ ልጸዋል። ይህን ተከትሎም ብዙዎች ‹‹አዴፓን ሊቀላቀሉ ይችሉ ይሆናል›› የሚል ግምታቸውን እያስቀመጡ ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here