ነገ፣ የካቲት 3 ቀን 2011 የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልት በአፍሪካ ኅብረት ቅፅር ጊቢ ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን አስመልክተው ብርሃኑ ሰሙ ስለ አዲስ አበባ ሐውልቶች መገንባት እና መልሶ መፍረስ ያወጉናል።
በቻይና መንግሥት ዕርዳታ የተገነባው የአፍሪካ ኅብረት አዲሱ ሕንፃ የተመረቀ ዕለት፣ ግቢው ውስጥ ለጋናዊው ንክሩማ ሐውልት ሲቆም፣ ዐፄ ኃይለሥላሴ በመዘንጋታቸው በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ትልቅ ቅሬታ ፈጥሮ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ከኢትዮጵያ እንዲነሳ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ለነበሩት፣ ለሊቢያው ፕሬዚዳንት ጋዳፊና ደጋፊዎቻቸው ማሳመኛ ታሪካዊ ትንታኔ ያቀረቡት አቶ መለስ ዜናዊ፤ የዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልት በአፍሪካ ኅብረት ግቢ እንዲሠራ ተፅዕኖ ማሳደር እንዴት አልቻሉም? የሚል ጥያቄም በወቅቱ ያነሱ ወገኖች ነበሩ።
ለዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልት እንዳይሠራ ዋነኛው ምክንያት መለስ ዜናዊና ፓርቲያቸው ኢሕአዴግ ናቸው ብለው የሚያምኑም ነበሩ። በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ፣ በሕንፃው ምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፥ አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ሕንፃ የተገነባው አጥፊዎች ይታሰሩበት በነበረ የማረሚያ ቤት ግቢ መሆኑን አመልክተው አዲሱ ሕንፃ የአፍሪካና አፍሪካዊያን ነጻነት በአስተማማኝ መሠረት ላይ መቆሙን ማሳያ ነው ብለው ሐሳባቸውን የገለጹበት አካሔድ ታሪክን ለመሻማት ፈልገው ነው ያሉም ነበሩ።
አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በኅብረቱ 29ነኛ ስብሰባ፣ በአፍሪካ ኅብረት ቅፅር ግቢ ለዐፄ ኃይለሥላሴና ለመለስ ዜናዊ ሐውልት የመሥራት ዕቅድ መያዙን ሲነገር፣ በዚህም ውስጥ “የታሪክ ሽሚያው” ከወዲያኛው ወደዚህ ዘመን ተንከባሎ መምጣቱ በግልጽ ታይቶ ነበር ቢያስብልም፣ አሁን የተሠራውና የካቲት 3 ቀን 2011 በአፍሪካ ኅብረት ግቢ የሚመረቀው ሐውልት የዐፄ ኃይለሥላሴ ብቻ መሆኑ ግልጽ ሆኗል።
‘ለመለስ ዜናዊ ሊሠራ ታስቦ የነበረው ሐውልት ለምን ቀረ?’ ቢባል ኢሕአዴግ በአፍሪካ ኅብረት ዕቅድና አሠራር ላይ ጣልቃ የመግባት አቅሙ ተዳከሞ ወይም ጣልቃ ገብነቱ አይጠቅመኝም ብሎ አውቆ ትቶትም ይሆናል። ክስተቱ ግን ብዙ የሚያነጋግር ነው። የምሥረታ ታሪኩ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የሆነው አፍሪካ ኅብረት፥ ኃይል፣ ሥልጣንና ጉልበት ያለው ሁሉ እንደፈለገ የሚጠመዝዘው ነው ወይ? የሚል ጥያቄም ያስነሳል። እንደዚያ ባይሆን አሁን ተግባራዊ የሆነው የዐፄ ኃይለሥላሴን ሐውልት ቀድሞውንስ ንክሩማ ጋር ያልተሠራበት ምክንያት ምን ነበር? ኅብረቱ ለመለስ ዜናዊ ሊሠራ ያቀደው ሐውልትን ላለመሠራቱስ ምን ምላሽ ይኖረው ይሆን?
“አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው” እንዲሉ፥ አፍሪካ ኅብረት ያከበርነውን ሊያከብርልን፣ ያዋረድነውን ዝቅ አድርጎ እየተመለከተ የሚሠራ ይመስላል።
ኢትዮጵያዊያን “አያያዛችን እየታየ” የተከበርንበት ብቻ ሳይሆን ዝቅ ብለን የታየንበት አጋጣሚና እውነታ መኖሩ ዛሬ የተከሰተ፣ በድንገት የሆነ ሳይሆን ተደጋግሞ በታሪካችን የታየ እና የሚታይ ነው። ለውጭ ጠላት አልበገር ባይነታችን በአድዋ ድል ብቻ የቆመ አይደለም፤ የፋሽስት ጣሊያንና የሶማሊያ ወረራን በድል ያጠነቀቅንበት ታሪክ የክብርና ኩራታችን መገለጫ ናቸው። እርስ በእርስ በመጠላለፍ ከበቂ በላይ ዋጋ መክፈላችንን በተመለከተ፥ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ዛሬ የደረሰው የፖለቲካ ትርምሳችን አንዱና ዋነኛው ማሳያ አድርጎ ማቅረብ በቂ ነው።
ከአሁን ቀደም ካካሔዳቸው 4 ተሐድሶዎች፣ በዓይነቱ ለየት ያለ መታደስ እያደረገ ያለው ኢሕአዴግ መራሔው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ አሁን በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ለዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልት በመሠራቱ ቅር የሚሰኝ አይመስልም። ጥር 25 ቀን 2011 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምክክር ባዘጋጁት መድረክ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚ,ኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመድረኩ የተገኘሁት የፓርላማ (የጠቅላይ ሚኒስትርነት) ካባዬን ለብሼ አይደለም። ከናንተ ለመማርና እኔም ያለኝን ሐሳብ ለማካፈል ነው” ባሉበት መድረክ የአፍሪካ ኅብረት ለዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልት ማሠራቱን አመልክተው፣ የኅብረቱ መሪዎች በሚገኙበት የሚመረቀው ሐውልት አባቶቻችንን፣ ጀማሪዎችን፣ ታሪክና ያለፈውን ዘመን ማክበር መጀመራችንን ስለሚያመለክት ጥሩ ነው የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በቃል በሰጡት ምስክርነትም “ዐፄ ኃይለሥላሴን ስናወድስ ኢትዮጵያም ትወደሳለች” ነበር ያሉት።
በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዘመን ለገሀር የሚገኘው የይሁዳ አንበሳ ሐውልት ከቦታው ተነስቶ ሮም ከተወሰደ ከዓመታት በኋላ የተመለሰ ነው።
ያለፈውን ትውልድ፣ ዘመንና ሥራ እንደሚገባው አለማክበር በብዙ አጉዱሎናል። ይህንን ጉዳት ዐፄ ኃይለሥላሴን ብቻ ማዕከል አድርጎ በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ አይቸግርም። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት ለአገርና ሕዝብ ይሰጠው የነበረው አገልግሎት ታላቅ ከመሆኑ አንፃር “ሥሙ” ቢጠላ እንኳን ተግባሩ መቀጠል ነበረበት ብለው የሚቆጩ ምሁራን ቁጥር ጥቂት አይደለም። በኪነ ጥበብ፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በእርሻ… ታላላቅ ሥራ የሠሩ ኢትዮጵያዊያንን እና ለኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት አስተዋፅዖ ላደረጉ የውጭ ዜጎች ጭምር ዕውቅና እየሰጠ ይሸልም የነበረው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት ያከናውን የነበረውን ተግባር የሚመጥን ቀርቶ የሚቀራረብ ሥራ የሚሠራ ሳይገኝ 40 ዓመታት ተቆጠሩ።
ከ30 ዓመታት ጥረት በኋላ መቋቋም የቻለው “ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ” የንጉሠ ነገሥቱን ሥምና ተግባር ማየትና መስማት ያለመፈለግ በፈጠረው ጥላቻ ምክንያት ነበር “ዩኒቨርስቲው” በአዲስ አበባ ሥም እንዲጠራ ምክንያት የሆነው። በመንግሥት መቀመጫ ወይም በአገሪቱ ዋና ከተማነት 132 ዓመታትን ያስቆጠረቸው አዲስ አበባ የዐፄ ኃይለሥላሴን ጨምሮ በርካታ ሐውልቶች በአደባባዮቿ ቆመው ሲነሱ በተደጋጋሚ አይታለች።
ደብዛቸው የጠፉ ሐውልቶች
በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዘመን ለገሀር የሚገኘው የይሁዳ አንበሳ ሐውልት ከቦታው ተነስቶ ሮም ከተወሰደ ከዓመታት በኋላ የተመለሰ ነው። በዚያው የወረራ ዘመን ጊዮርጊስ የሚገኘው የዐፄ ምኒልክ ሐውልት ከቦታው ተነስቶ 4 ኪሎ ቤተ መንግሥት ግቢ ከተቀበረ በኋላ በነጻነት ማግስት ወደነበረበት የተመለሰ ነው። ሳይመለሱ በዚያው የቀሩትም ብዙ ናቸው። አደባባይ ተሰይሞላቸው ሐውልት ከቆመላቸው በኋላ ያገኙትን ክብር የተነፈጉ መሐል ሌኒን፣ ቦብማርሊና ፑሽኪን ይገኙበታል። ከአዲስ አበባ ከተማ አደባባዮች የተነሱት የዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልቶች ቁጥር ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።
ከየአደባባዩ ተነስተው በብሔራዊ ሙዚየም ግቢ እንዲሰባሰቡ የተደረጉት የዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልቶች ታሪክ ምን እንደሚመስል፣ የታሪክ ምሁሩ አቶ ክንፈ በርሔ “በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ስለሚገኙ ታሪካዊ ሐውልቶች የተቀረፁበት ወቅትና አሁን ያሉበት ሁኔታ” በሚል ርዕስ የ43 ሐውልቶችን ታሪክ አጥንተው በ2001 በዝርዝር አቅርበዋል።
የዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልቶች በኮተቤ መምህራን ማሠልጠኛ ግቢ፣ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት፣ በትምህርት ሚኒስቴር ግቢ፣ በሲኒማ ኤምፓየር ደጃፍ፣ በ3ኛ ክፍለ ጦር (ክብር ዘበኛ) ማሠልጠኛ ይገኙ እንደነበር ሐውልቶቹ መቼ፣ ለምን ዓላማ እና በእነማን በጎ ፈቃደኝነት እንደተሠሩ፣ የተሠሩበት ቁስ ምን እነደሆነ፣ በቀረፃው (በግንባታው) የተሳተፉት እነማን እንደነበሩና ስለቁመት መጠናቸው… ጭምር በዝርዝር አጥንተዋል – የታሪክ ባሙያው።
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ የተለያዩ አራት ሐውልቶች ይገኙ እንደነበር፣ እየደርግ መንግሥት የንጉሡ ሐውልቶች ከየአደባባዩ እንዲነሱ ከወሰነ በኋላ የዩኒቨርሰቲው ሐውልቶች የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ በጥናታቸው ያመለከቱ ሲሆን፥ ከአዲስ አበባ ውጭ ለዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልት አሠርተው ስለነበሩ ኢትዮጵያዊያንም አንስተዋል። ዐፄ ኃይለሥላሴ የነገሡበትን 25ኛ ኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ በወሎ ጠቅላይ ግዛት ይገኙ የነበሩ የመንግሥት ሹማምንትና ሠራተኞች በመዋጮ አስቀርፀው ለንጉሠ ነገሥቱ ያበረከቱት ሐውልት አንዱ ነው።
የ25ኛ ኢየቤልዩን በዓልን ምክንያት በማድረግ ተሠርቶ፣ የመፍረስ አዳጋ ያልገጠመው ብቸኛው ቅርስ ብሔራዊ ቴአትር ደጅ የሚገኘው የሞዓ አንበሳን ምስል የያዘው ሐውልት ነው። ይህ ሐውልት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በፈረንሳዊያን ባለሙያዎች አስገንበቶ ጥቅምት 30 ቀን 1948 ለንጉሠ ነገሥቱ ያበረከተው ነው። በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት (በወመዘክር) ግቢም መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም የዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልት በክብር ተቀምጦ ይገኛል።
ዐፄ ኃይለሥላሴ በሥልጣን ዘመናቸው ትምህርት፣ ጤና፣ ንግድ፣ ኢንደስትሪ… በአገሪቱ እንዲስፋፋ ላደረጉት አስተዋፅዖ ኢትዮጵያዊያን ሐውልት በማስቀረፅ አክብሮትና ምስጋናቸውን ለማቅረብ ሞክረዋል። የሐውልቶቹ ብዛት ለንጉሠ ነገሥቱ የተሰጠው ውዳሳና ሙገሳው በዝቷል ያስብል ይሆናል። ደርግም ለሌኒንና ማርክስ በአገሪቱ ዋና ከተማ ሐውልት ለማቆም ያነሳሳው፣ “ለጌቶቹ” ያለውን አድናቆት ለመግለጽ ነበር። ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ በየጥጋጥጉ ሐውልት ለማቆም የታየው ፍላጎትም ተመሳሳይ ነው። ሐውልት ማቆም በሕግና ስርዓት ካልተመራ፣ በአፍሪካ ኅብረት ውሳኔ እንደታየው፣ ደስ ያለው አካል ሲፈቅድ የሚሳካ፣ አኩራፊ ሲኖር የሚቀር ነው የሚሆነው።
ምንም ሆነ ምን በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ለዐፄ ኃይለሥላሴ ሐውልት መቆሙ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት ታሪክ ሠሪውን ብቻ ሳይሆን “ኢትዮጵያን ያስወድሳል”። አዲሱ ሕንፃውን በ“ከርቸሌ” ያሠራው የአፍሪካ ኅብረት፣ ቦታው ወህኒ ቤት በነበረበት ዘመን በቀላሉ ይገባበት እንዳልነበር ሁሉ፥ ዛሬም ወደዚያ ግቢ ለመግባት ለብዙ ኢትዮጵያዊያን ከባድ ነው። በፎቶና ቴሌቪዥን ካልሆነ በስተቀር ለዐፄ ኃይለሥላሴ የሚቆመውን ሐውልት ለማየት ዕድሉ የለም።
ዐፄ ኃይለሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አሁን ኅብረት) መመሥረት ላደረጉት አስተዋፅዖ ሐውልት እንዲቆምላቸው ተወስኖ ተግባራዊ መሆኑ እሰየው የሚያስብል ነው። ንጉሣቸውን ሌሎች ዕውቅና ሳይሰጧቸው በፊት፣ ኢትዮጵያዊያን አክብረው ያሠሩላቸው ሐውልቶች የብሔራዊ ሙዚየም “እስረኞች” ከሆኑ 43 ዓመታት አስቆጥረዋል። እነዚህን ሐውልቶች ነጻ አውጥቶ ወደነበሩበት ቦታ መመለስ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን ይበልጥ አያስወድስም ወይ?
ቅጽ 1 ቁጥር 13 የካቲት 2 ቀን 2011