ባለፈው ዓመት 386 በሚሆኑ ሀብት አስመዝጋቢዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ በተደረገ የሀብት ምዝገባ ትክክለኛነት ማረጋገጫ 53 በመቶ የሚሆኑት ትክክለኛ ሀብት ያስመዘገቡ ሲሆን፣ 47 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ትክክለኛ መረጃ ያልሰጡ በመሆናቸው፣ ከእነዚህ ውስጥ 13 የሚሆኑት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ክፍተት የተስተዋለባቸው መሆኑን ተከትሎ፣ በዚህም ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አፍርተዋል ለሚል ጥርጣሬ በቂ መረጃ እንደተገኘባቸው በፌደራል ፀረ ሙስና እና ስነ ምግባር ኮሚሽን የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት መስፍን በላይነህ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ሆኖም 47 በመቶ ከሚሆኑት ውስጥ ጥቃቅን ስህተት ሰርተው የተገኙ ሰዎች በድጋሚ እንዲያስመዘግቡ እና ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ይደረጋል። 13ቱ ላይ ግን ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ እና የክስ ሂደቱም በሚመለከተው አካል ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በዚህም አላግባብ ያፈሩት ሀብት በሐራጅ እስከመሸጥና እስከመወረስ ብሎም በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ነው የገለጹት።
በተደረገው የሀብት ትክክለኛነት ማረጋገጥ ሥራ ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት የተገኘባቸው አካላት፣ የህዝብ ጥቅም ጫና ውስጥ መግባቱንና ያልተገባ ሀብት ማፍራት መኖሩን አመላካች ናቸው ብለዋል ዳይሬክተሩ።
በሌላ መልኩ በተያዘው ዓመት የ400 ሀብት አስመዝጋቢዎችን የመረጃ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን መስፍን በላይነህ ገልጸዋል። እስካሁን ባለው የ100 ሀብት አስመዝጋቢዎች ላይ የመረጃ ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራ መሰራቱን ጠቁመው፣ የተገኘው ውጤት በሪፖርት መልኩ በቀጣይ ይፋ ይደረጋል ሲሉ ነው የተናገሩት። በዚህ ዓመት የሚደረገው የሀብት አስመዝጋቢዎች የመረጃ ትክክለኛነት ማረጋገጥ ሥራ በመንግስት አመራሮችና ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ ዘርፎች ኃላፊ በሆኑ አካላት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም አብራርተዋል።
በ2013 ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የመንግስት ሠራተኞች እና ባለሥልጣናት ሀብት ማስመዝገባቸው ተገልጿል። በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ ያላስመዘገቡ አካላት ደግሞ በ1000 ብር ቅጣት ተቀተው መመዝገባቸውን እንዲሁ ፀረ ሙስናና ስነምግብር ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታውሷል። በዚህም 3601 ከሚሆኑ የመንግስት ሠራተኞች እና ኃላፊዎች የተሰበሰበ 3 ሚሊዮን 601 ሺህ ብር በቅጣት ለመንግስት ካዝና ገቢ መሆኑ ተመላክቷል።
ሀብታቸውን ካስመዘገቡ 1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ውስጥ፣ እስካሁን ያስመዝጋቢዎችን ሀብት ትክክለኛነት ማረጋገጥ የተቻለው የ386 ሰዎችን ብቻ መሆኑን ያመላክታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 163 ታኅሣሥ 9 2014


