ዳሰሳ ዘ ማለዳ (የካቲት 4/2012)

Views: 564

 

ሁለት ታዳጊዎችን አግቶ ገንዘብ የጠየቀው ግለሰብ የ25 ዓመት እስር ተፈረደበት

በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ የሰባት  ዓመት ህፃንና የ17 አመት ታዳጊን ከብት በመጠበቅ ላይ እያሉ አግቶ ገንዘብ የጠየቀው ግለሰብ የ25 ዓመት እስር ተፈረደበት። የጠገዴ ወረዳ ፍርድ ቤትም በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሳለፉን ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ያተገኘው መረጃ ያመላክታል። ተከሳሽ ወንጀሉን የፈፀመው በስግብግብነት፣ በጦር መሳሪያ፣ በአፍቅሮ ንዋይ የሰው ልጅን ከገንዘብ በማሳነስ እንዲሁም በተደጋጋሚ የተፈፀመና ህፃናትን ለርሃብ፣ ለጥምና ለእንግልት የዳረገ መሆኑ ገልጿል።(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2025 የታዳሽ ሀይልን ተደራሽ ለማድረግ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር አስታወቀ። በፈረንጆቹ 2025 በመላ ኢትዮጵያ የታዳሽ ሀይልን ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ እየሰራ መሆኑንም ሚኒስቴሩ  አስታውቋል።በኢትዮጵያ የታዳሽ ሀይል በ1998 ዓ.ም በክልል ከተሞች የተጀመረ ሲሆን፥ አሁን ላይ በዚህ አገልግሎት ከ7 ሺህ በላይ የገጠር ከተሞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የብልጽግና ፓርቲ አመራር የሆኑት ታዬ ደንደአ በቢሸፍቱ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ብርና ሌሎች ንብረቶች ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸው ገለጹ። ታዬ ዘረፋው ያጋጠማቸው ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሾፍቱ በሄዱበት ወቅት ቢን ኢንተርናሽናል በተባለ ሆቴል ምሳ ለመመገብ መኪናቸውን አቁመው በገቡበት ጊዜ “የመኪናቸው በር በማስተር ቁልፍ ተከፍቶ” እንደተሰረቀባቸው ተናግረዋል። (ቢቢሲ አማርኛ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

ባለፉት ሰድስት ወራት ውስጥ ለ1 ሺህ 270 ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘለቀ ደላሎ ገለጹ፡፡ በይቅርታውም ከመከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች፣ በክልል ፍርድ ቤት ተፈርዶባቸዉ የፌዴራል ፍርድ ቤት ስልጣንና ኃላፊነት የሆኑ እንደ ቼክ፣ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውርና መሰል ጉዳዮች፣በፌዴራል ፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው በክልል የሚታረሙ፣ በዝውውር በክልል ታስረው ያሉ ታራሚዎች ተጠቃሚ መሆናቸዉን አብራርተዋል፡፡(ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) በሚል በአገሪቱ የሚስተዋለው ቁማር እንዲቆም ከስምምነት መደረሱን የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ የብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ግን በጉዳዩ ላይ የተለየ አቋም እንደያዘ ተነግሯል፡፡ የሚኒስትሩ የወጣቶች ስብዕና ልማት ዳይሬክተር አቶ አለሙ ሰኢድ የስፖርት ውድድር ቁማር እንዲቆም መወሰኑን ገልፀዋል። (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በኮሮና ቫይረስ የሚከሰተው በሽታ ‘ኮቪድ-19’ (Covid-19) የሚል ስም ተሰጥቶታል ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ደ/ር) አስታወቁ፡፡ ክትባቱም በ18 ወራት ውስጥ ሊቀርብ እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡በቫይረሱ ለሚከሰተው በሽታ ስም እንዲሰጠው ያስፈለገው በቫይረሱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ1 ሺህ በላይ መድረሳቸውን እና በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ ነው ብለዋል።(ቢቢሲ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ34 ሺ በላይ የዲጂታል መታወቂያ መሰጠቱን የከተማዋ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ መላክ መኮንን አስታወቁ፡፡ በግማሽ ዓመቱ ከ66 ሺህ በላይ ዲጂታል የሕትመት መታወቂያ ለከተማዋ ነዋሪዎች ለመስጠት ታቅዶ ከ34 ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያ ተሰጥቷል፡፡ ለአፈጻጸሙ ማነስ በምክንያትነት የተጠቀሱት  የህትመት መሳሪያዎች እጥረት፣የኔትወርክ መቆራረጥ፣የሰው ሃይል እጥረት  እንደሆነም አማካሪው አስረድተዋል።(ኢትዮኤፍኤም)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

ሰላሳ ዓመታት ከተረፈ-ምርቶች በሚወጣ መጥፎ ጠረን አካባቢን እና ህብረተሰብን ሲያውክ ኖሯል የተባለው የአዲስ አበባ ቄራዎች ድረጅት እና አንድ ሌላ መንግስታዊ ተቋም በአንድ የሕግ ባለሞያ መከሰሳቸውን ተነገረ፡፡ ከሳሹ የሕግ ባለሞያ የሕዝብን በጤናማ አካባቢ የመኖር መብት ለማስከበር በግላቸው በመንግስታዊ ተቋማቱ ላይ የከፈቱት ክስ በሰለጠነው ዓለም የተለመደ ቢሆንም ፤ለሀገራችን ግን አዲስ እንደሆነ ተነግሯል፡፡(ሸገር ኤፍ ኤም )

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com