‹‹251 ኮሚዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ›› የነዋሪውን የቤት ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ቤት ገንቢውና ገዢው እንዲገናኝ ለማድረግ ኤግዚቢሽንና ባዛር ለአራተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ሊያካሂድ መሆኑን ገለጸ።
ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ካለው ፈጣን የከተማ ልማት ጅማሮና ዕድገት አንጻር፣ በየጊዜው የሚፈጠረውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት በየዓመቱ 381 ሺሕ ቤቶች መገንባት እንዳለባቸው በጥናት መጠቆሙን የተገነዘበው 251 ኮሚዩኒካሽንና ማርኬቲንግ፣ የተገነቡ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ይዞ መቅረቡን ነው መረዳት የተቻለው።
ኤግዚቢሽኑ የሚካሄደው የፊታችን ታኅሳስ 23ና 24/2014 በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል መሆኑ የተመላከተ ሲሆን፣ 251 ኮሚዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ በየዓመቱ በሚዘጋጀው በዚህ ኤግዚቢሽን በርካታ ሪልስቴቶች የገነቧቸውን ቤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አመላክቷል።
በሪልስቴቶች ተገንብተው ከሚቀርቡት ቤቶች በተጨማሪ፣ ‹ፈርኒቸር› ቤቶች፣ ቤት አስዋቢዎች፣ የግንባታ፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የቤት ማስዋቢያ ዕቃ አቅራቢዎች፣ በአንድ ጣሪያ ሥር እንደሚገናኙ ነው የተገለጸው።
ኤግዚቢሽኑ፣ ቤት ገንቢውና ገዢው፣ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ እንግዶች እንዲገናኙ ከማድረግ በተጨማሪ፣ የፊታችንን የገና በዓል የተደረገውን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገራቸው ለሚመጡ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች የአገር ምርቶችን እንዲጠቀሙ ለማበረታታትና ዘላቂ ደንበኛ ለማፍራት ምቹ አጋጣሚን ይፈጥራል ነው የተባለው።
በግል ባለሀብቶች የተያዙ ከ600 በላይ ሪልስቴት ቢዝነሶች በአገሪቱ መኖራቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ፍላጎትን ከሞላጎደል በማሟላት ረገድም ታላቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014


