“ከተባበርን ቁስላችን ቶሎ እንደሚሽር እርግጠኛ ነኝ”

0
914

የዚህ ሣምንት እንግዳችን በሥፋት የሚታወቁት ባላገሩ ተብለው ነው፡፡ ተሾመ አየለ ሕጋዊ መጠሪያቸውም ነው፡፡ ሰሜን ሸዋ ተወልደው ያደጉት እኚህ ግለሰብ ባላገሩ በሚል ሥያሜ የሚጠራ አስጎብኚ ድርጅት አላቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚከሠቱ ግጭቶችም ሆኑ የተለያዩ አካላቶች በሚሠነዝሩት ጥቃት ፈጥነው ለተጎጂዎች በመድረስ ሥማቸው በሠፊው ይነሳል፡፡

ከወሎ ግዛት እስከ ሰሜን ሸዋ ዘልቆ የነበረውን ወራሪ ኃይል በማስወገድ ዘመቻ ላይ ከመንግሥት ታጣቂዎችና ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ተቀላቅለውም ቆይተዋል፡፡ ስለአጠቃላይ ሒደቱም ሆነ ስለወቅታዊው ኹኔታው ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ስለራስዎ ትንሽ ቢያስተዋውቁን?
ሰሜን ሸዋ እንደማንኛውም የአገርቤት ልጅ ተወልጄ ካደኩ በኋላ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ የወታደር ልጅ ነኝ። አሁን የራሴን ሥራ እየሠራሁ ነው የምገኘው። ባላገሩ አስጎብኚ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪጅ ነኝ።
አሁን ባለው አገራዊ ችግርና ቀውስ የተለያየ አደረጃጀት ላይ ድጋፍ እያደረግኩ፣ ከመደገፍም ባለፈ በራስ ሥንቅ፣ትጥቅና በጀት አገሬን ለማገልገልና አገሬን ነጻ ለማውጣት፣ ከወራሪዎች ለመከከላከል፣ ከመከላከያችን፣ ከልዩ ኃይላችን፣ ከፋኖ፣ ሚሊሻና ከኹሉም የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን አሁን ለጊዜውም ቢሆን የተመዘገበውን ድል ዐይተናል።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮያን ሲፈጥር ታላቅ አገር አድርጎ የፈጠራት ናት። ኢትዮጵያዊ በመሆኔም በጣም ኩራት ይሰማኛል።

አንዳንዴ አገራችን እና እኛ ያለንን ዋጋ በትክክል የተረዳነው አይመስለኝም። ዋጋ ስላለን፣ አገራችን ዋጋ ስላላትና ታላቅ አገር ስለሆነች ነው ነጮቹም ይህን ስለሚየውቁ እየተጋፉንና እየተዳፈሩን ያሉት። ኢትዮጵያውያን አንዴ ስንፈጠር የሰው ልጅ መገኛ ሆነን ነው የተፈጠርነው። እግዚአብሔር አምላክ ዋጋ የሠጣት አገር ናት። እና ይህን ዋጋ ማወቅና መጠቀም ያስፈልጋል።

አንዳንድ ኢትዮጵያውያን በሥንፍና ታጥረው ኢትዮጵያ ደሃ ነች የሚሉ ሰዎች አሉ። ደሃ አገር ብትሆን ኖሮ ነጮች ከእኛ ጋራ ሊገዳደሩን አይችሉም ነበር። ኢትዮጵያ ደሃ አገር አይደለችም። ድህነታችን ተፈጥሯችንን መጠበቃችን ነው። ለዚህ ኹላችንም ከመጣብን አደጋ ለመትረፍ ኹሉም ሰው ሊተባበር ይገባል የሚል ዕምነት አለኝ።

ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ጀግና ወልዳለች፤ በፊትም አሁንም ብዙ ጀግኖች አሏት። ኢትዮጵያን የሚደፍሩ ኹሉ ሲረግፉ፣ ሲያፍሩ፣ ሲኮማሸሹ ነው እስከዛሬ የምናውቃቸው። አሁንም በተመሳሳይ እየሆነ ያለው ይህ ነው። እግዚአብሔርም ስለሚጠብቀን፣ ጀግና ሕዝብም ስላላት እዚህ ደርሰናል ማለት ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ኹኔታ እንዴት ይገመግሙታል?
በዋናነት ማወቅ ያለብን ችግሮች በማንኛውም ጊዜ ሊፈጠሩ ይችላሉ። ብልህ ሆነን ለችግር መፍትሔ መፈለግና ጥቅም ወደሚያስገኝ ነገር መቀየር ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ትልቅ ነገር ገጥሟት ከርሟል፤ በኢኮኖሚ ተጎድተናል፤ ብዙ ምስቅልቅልና ዓለም አቀፍ ጫና ሊደረግብን ተሞክሯል፤ መጥፎ ጊዜያትን አሳልፈናል።

እንዲህ ያሉ መጥፎ ቀናትን ልናልፍ የምንችለው ተባብረን በመሥራት፣ ተናብበንና ተከባብረን፣ ረጅም ሰዓት በመሥራትና በመደማመጥ፣ በመደራጀት ላይ ያተኮረ ሥራ ከሠራን፣ ከደረሰው በደል የተሻለ ሆነን የምንወጣበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለብን ይሰማኛል።
ያለፉት ዓመታት የነበሩት በተለይ በዚህ ወረራ፣ በተለይም አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ አካላት ሲያደርጉ የነበረውን ነገር ዐይተናል። እኛ ደግሞ ከእነሱ ተሽለን መገኘት መቻል አለብን። አስቀድሞ እንዳልኩት ኢትዮጵያ የማትፈርስ አገር፣ የማታጎነብስ አገር መሆኗን መረዳት ያሻል።
ስለዚህ ስላለፉ ዓመታት ወደኋላ መመለስና ማሰብ አያስፈልገንም። ወደፊት የተጎዱ አካባቢዎችን እንዴት ማገዝ አለብን፣ የተጎዱ ወንድሞቻችንን እንዴት መደገፍ አለብን፣ በጀግንነት የተሰዉ ወንድሞቻችንን ቤተሰቦች እንዴት መርዳት አለብን፣ ታሪኩን እንዴት አድርገን መዘከርና መጻፍ አለብን፣ የወደሙ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ተቋማትን እንዴት ማዳን መቻል አለብን የሚለውን፣ በኃላፊነት ኹላችንም በአገር ውስጥም በውጪም ያለን ኢትዮጵያውያን በዛ ላይ ከተባበርን ቁስላችን ቶሎ እንደሚሽር እርግጠኛ ነኝ።

ዘመቻውን በማስተባበርና በአካልም በመሳተፍ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። አጠቃላይ ዘመቻው ምን ይመስላል?
ዘመቻው በጠቅላላ ከአየር ኃይሉ እስከ እግረኛ ድረስ፣ ከአዋጊው እስከ ተዋጊ ድረስ ያለው ተነሳሽነት፣ በሚሊሻው፣ በፋኖው፣ በአፋር አናብስት ጀግኖች፣ አፋር ልዩ ኃይል፣ ላስታዎች፣ ጎንደር … በጠቅላላ ጥምር ኃይሉ የሚገርምና ድንቅ የሚያስብል ብቃት የታየበት ነው። አልፎ አልፎ ተራ የግለሰብ ፍላጎቶችና አንዳንድ ጉድለቶች ቢታይም፣ ይህ እንደመንግሥት ነው ተብሎ መወሰድ የለበትም። ከአሁን ቀደምም ሊደረጉ እንደሚችሉት የግለሰብ ፍላጎት በተለያየ ጊዜ ታሪክም አንደሚያሳየን ባንዳዎች ሊኖሩ ይችላሉ።

እንጅ በአብዛኛው ጊዜ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ እንደሚወራው እገሌ ስላልተዋጋ ነው፣ እገሌ ስላልደገፈ ነው የሚለው ነገር ከእውነት የራቀ ነው። በአካል ነበርን፤ መከላከያችንም እኛም በጣም በተናበበና በተከባበረ፣ በወንድማማችነት መልኩ ነው ስንሠራ የነበረው። ኹሉም ከአዋጊ እስከ ተዋጊ፣ ከአየር ኃይል እስከ እግረኛ ድረስ የነበረው ጥምረት እጅግ ድንቅ እና ሊመሰገን የሚገባ ነው። እንጅ በተለያ አካላት እንደሚወራው በዛ መልኩ አይደለም።

ዕፁብ ድንቅ ሊያሰኝ ሊያስመሰግን፣ ለወደፊትም ወራሪዎች ኢትዮጵያን ከመውረራቸው በፊት አንዴ ሳይሆን ሚሊዮን ጊዜ ደጋግመው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ክስተት የሆነ ነው። ኢትዮጵያውያን ለአገር መሞትን ያሳዩበት ታላቅ ገድል ነው የተፈጠረው።

በሕዝብ ረገድ ባለፉት ወራት አንዴ ተስፋ መቁረጥ መልሶ ተስፋ ማድረግ ይስተዋላል። በሕዝቡ ያለውን ተነሳሽነት እንዴት ያዩታል?
የሕዝቡ ተነሳሽነት ያኔም ነበር አሁንም አለ። ምክንያቱም ከተማው ላይ ያሉ፣ ቦታው ላይ ሳይሄዱ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ሆነው እንደሚጽፉት አይደለም እውነታው። ሥጋቶች ነበሩ፣ ብዙ ነገር መጥተው አጥፍተዋል። ከዚህ ነገር እንዴት ወደፊት ተምረን መሥራት አለብን የሚለው የተሻለ ይሆናል ብዬ ነው የማስበው።

በቅርቡ መንግሥት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች አርስዎ በቦታው ተገኝተው ስሜት የገለጹበት ምስል በማኅበራዊ ሚድያ ልዩ ስሜት ፈጥሮ ነበር። ያንን ሁኔታ መለስ ብለው ቢያስታውሱን?
በወቅቱ ወራሪው ኃይል ከትግራይ እስከ ሸዋ፣ ከትግራይ እስከ አፋርና ከትግራይ እስከ ጎንደር ድረስ በሰው መሬት ላይ የማይሆን ሥራ ሲሠሩ ነበር። በረገጡባቸው አካባቢዎች በሙሉ ማኅበረሰቡን ሲያስጨንቁ፣ ተቋም ሲጎዱ፣ የበሉበትን እያበላሹ፣ ያላቸውን አሟጠው እየበሉባቸው እየለበሱባቸው፣ ሕጻናትን ከመድፈር ጀምሮ ታላላቅ ውድመትን ሲያደርሱ ነበር። እኛ በደረስንት አካባቢና ጥምር ጦሩ በገባበት አካባቢ፣ ማኅበረሰቡ ሲያሳየው የነበረው ደስታ እጅግ ይገርም ነበር። ስሜታዊ ያደርጋል። በጣም ሕፃናት ያለቅሱ ነበር፤ እናቶች ደስታቸውን በእንባ እየተናነቃቸው ነበር ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑና መከላከያንና ጥምር ኃይሉን ሲያመሰግኑ የነበረው።

በዛ ሰዓት ወንድ፣ ሕፃን፣ ሴት፣ አዛውንት፣ ጳጳስ፣ ቄስ ሳይል ማኅበረሰቡ ያለቅስ ነበር። ይህ ስሜት ምን ያህል ጎድተዋቸው፣ ምን ያህል ጨቁነዋቸውና ተጽዕኖ ፈጥረውባቸው እንደነበር ማሳያ ነው።

የተጎዱ ማኅበረሰቦችን መልሶ ከማቋቋም አኳያ፣ ምግብና አላብሳት ያስፈልጋል። ንብረታቸው የወደመባቸውን በዘላቂነት ለማቋቋምስ ምን መደረግ አለበት?
ማኅበረሰቡ በአገር ውስጥም በውጪም ያለን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ሁላችን በያለንበት አለን ማለት ይገባል። አንደኛ ኹሌ ሩዝና ዘይት ወይም የሚበላ ነገር ሠጥተን ብቻ በዘላቂ ረዳን ማለት አይደለም። ሕይወት ስለሚቀጥል ዛሬ የረዳነው ነገር ነገ ያልቃል። ስለዚህ ሳንሰለች አምስት ጉርሻ የምንጎርስ ከሆነ፣ ሦስቱን ጎርሰን ኹለቱን ለወገኖቻችን ማሰብ ያስፈልጋል። በሬዎቻቸው የታረዱባቸውና የተበሉባቸውን በሬ እንዲያገኙና በበሬ እንዲያርሱ ማድረግ፣ በኢኮኖሚ የተጎዱትን እንዲያገግሙ ማድረግ፣ ኻያ አራት ሰዓት ባንሠራ እንኳ 15 ሰዓት በሙያችን ሠርተን አገር እንደ አገር ከፍ እንድትል ማድረግ፣ የወደሙትን ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶችና ተቋማትን ወደ ነበሩበት መመለስ፣ ውጪ አገር ያሉ ኢትዮያውያን እና ኢትዮጵያን የሚወዱ አገራት ቶሎ ብለው በተሻለ ሁኔታ ቶሎ ወደ ግንባታ እንዲገቡ ማድረግ ይጠበቃል።

ለምሳሌ አንድ የወደመ ሆስፒታል ሸዋሮቢት፣ ኮምቦልቻ ወይ ደባርቅ ሊሆን ይችላል፤ የተለያዩ አካባቢዎችን አንድ ክልል ኹለትና ሦስት ነገሮችን በኃላፊነት ቢወስድ። ምክንያቱም የአማራና የአፋር ክልሎች ከሌሎች ክልሎች በተለየ መልኩ በኢኮኖሚም በሥነ-ልቦናም በጣም ጫና ውስጥ ስለነበሩ፣ ሌሎች ጉዳት ያልደረሰባቸውና ያልተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው አለን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ የሆነ መፍትሔ መስጠት ይኖርባቸዋል።
ቆርቆሮ ነቅሎ ቆርቆሮ መቀየር፣ ወይም ጭቃ አራግፎ ጭቃ መሥራት ሳይሆን፣ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደ አገር መሥራት ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ።

ወላጆቻቸውን በጦርነት ያጡ አዳጊ ሕፃናትም በርካታ ናቸው። እነዚህንስ ለማገዝ ምን መደረግ አለበት?
እነዚህን አዳጊ ሕፃናት በትምህርት ቤቶች በነጻ እንዲማሩ፣ ትራንስፖርትና ሕክምና ነጻ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ አባት እናት ሆነን ባንተካላቸውና የእነሱን ያህል ፍቅር ባንሰጣቸውም እንኳ፣ ቢያንስ ችግር እንዳያገኛቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ልዩ ክብካቤና ልዩ ትኩረት ለወታደር ልጆች፣ ለልዩ ኃይልና ለፋኖ፣ አፋር አካባቢ ለነበሩ የተጎዱ እህቶችና ወንድሞች፣ ለኹሉም ተጋድሎ ላደረጉት አለን ብለን ቋሚ የሆነ ነገር ልናደርግላቸው ይገባል።

ለምሳሌ፣ ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንድ ሞዴል የሆነ ነገር ዐይቻለሁ። ከሱ ተምረን ማኅበረሰቡም የተሻለ ነገር እንዲያደርግ ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ኹሌም ከመንግሥት የምንጠብቀው ነገር ትክክል አይደለም። አሁን ጦርነት ላይ የቆየ መንግሥት አገር ስለሆነች፣ ከመንግሥት ብዙ መጠበቅ የለብንም። ስለዚህ እኛው ራሳችን እንደውዴታም እንደግዴታም አድርገን በዚህ ነገር ተሳትፈን ለዜጎቻችን እና ወገኖቻችን ዕገዛ ማድረግ ያስፈልጋል።

እንደ ሕፃናት አንባ ቋሚ የሆነ ልጆችን የሚንከባከብ ተቋም ይመሥረት የሚል ሐሳብም አለ። እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ከተቻለ የሚቻለውን በሙሉ እናድርግ። ኹላችንም ተባብረን አቅም በመፍጠር ማድረግ የምንችለውን በአፋጣኝ ከመተግበር የሚያግደን ነገር መኖር የለበትም፡፡

ከቱሪዝም ጋር በተገናኘ ዘርፉ በዚህ ጦርነት በጣም እንደተጎዳ ይታወቃል። እርስዎም በዚህ ዘርፍ ነውና የተሠማሩት። አሁን ላይ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ተጋብዟል። በዚህ ላይ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ቱሪዝሙ አሁን በጦርነቱ ብቻ ሳይሆን ላለፉት ኹለት ዓመት የኮቪድ ወረርሽኝ ሥርጭት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የመጀመሪያ ተጎጂ ነበር። ሆቴሎች፣ አስጎብኚዎችና በዘርፉ ላይ የተሠማሩ ኹሉም ግለሰቦችና ተቋማት ተጎድተው ነው የከረሙት። አሁን ደግሞ ቱሪዝም የሚፈልገው ሠላም ነው፤ ቱሪዝሙ በጣም ተጎድቷል።

ቱሪዝሙን እንዲያገግም ለማድረግ አንድ ትልቁ መፍትሔ ነው ተብሎ የታሰበውና መንግሥት የተወሰደው አቅጣጫ በጣም ሊደነቅ የሚገባ ነው፤ ለዚህም ላመሰግን የምፈልገው ነገር ነው። ነጭ ሳንጠብቅ፣ የእኛው ራሳችን ኢትዮጵያውያን አንድ ሚሊዮን ጎብኚዎች ወደ አገራቸው እንዲመጡ መደረጉ፣ ዘርፉ ላይ ላሉ ባለሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ቤት አከራዮች፣ ባለታክሲዎች፣ ቡና ሻይ ለሚያቀርቡ፣ በቱሪዝም ዘርፍ በአስጎብኝነት፣ በምግብ አብሳይነት የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተስፋ የሚሰጥና የሚያነቃቃ፣ ይበል የሚያሰኝ ነገር ነው።

እንግዶቻችንም በሠላም ገብተውንልን በሠላም አገራቸውን ጎብኝተው፣ ቤተሰቦቻቸውን አግኝተው፣ ጉዳቱን ዐይተው፣ የተጎዱትን ደግፈውና ገንዘባቸውን በባንክ ዘርዝረው አገራቸውን ከፍ አድርገው እንደሚመለሱ እርግጠኛ ነኝ፤ እንደዛ ይሰማኛል። ምክንያቱም ከዛ ተነሥተው ሥራ ትተው ሲመጡ ይህ ቁጭት አድሮባቸው እንደሆነ እርግጠኛ ስለሆንኩኝ ነው።

ስለዚህ የእነሱ ጉዞ አንደኛ በኢኮኖሚ መነቃቃት ነው። ኹለተኛ ነጮቹ ዘመዶቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ አትብረሩ ብለው ቀይ መስመር ኢትዮጵያ ላይ ሲያደርጉ፣ የእኛ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ይህንን ቀይ መስመር አልፈው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ፣ አንዱ የትግል አቅጣጫ የትግል መስመር ስለሆነ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፤ ትልቅ ዕገዛም ያደርጋል ብዬ አስባለሁ።

ጎብኚዎች ከመጡ በኋላ ረጅም ጊዜ እንዲቆዩና በተጎዱ አካባቢዎች ቆይተው ገቢ እንዲያስገኙ አዳዲስ መዳረሻዎችን ይፋ የማድረግ ሐሳብ ቀርቧል። በዚህ ላይ ያሰባችሁት ነገር አለ?
አብዛኛውን ጊዜ የፈጀሁትና እስከ አሁንም ያለሁት የጸጥታ ማስከበሩ ላይ ነው። ቢሯችን… ኹሉም አስጎብኚ ድርጅት ባልልም፣ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ሆኖ ነው ያለው።

እነዚህ ጎብኚዎች በሚመጡ ጊዜ ታድያ አዲስ ብቻ ሳይሆን ነባሮቹ እንደ ላሊበላና የተለያዩ አካባቢዎች ሲሄዱ፣ ድሮ እንደሚያውቁት ምቹ ላይሆን ይችላል። የውኃ መቆራረጥ፣ የመብራት መቆራረጥ፣ የባንክ ሲስተም አለመሥራት አለ። እነዚህን አውቀው ልክ ወታደር ነን ብለው አስበው እንዲስተናገዱ አደራ ማለት እፈልጋለሁ።

ሌላው ባለሆቴሎች፣ መኪና አከራዮች 30 በመቶ ለመቀነስ ቃል ገብተናል። እኛም በቃላችን መሠረት ቅናሽ አድርገናል። ሌሎችም አስጎብኚ ድርጅቶችና ተቋማት በተለይም ሆቴሎች፣ በተለይ ጉዳት ያልደረሰባቸው አካባቢ ያሉትም ቅናሽ አድርገው አገልግሎት እንዲሰጡ አደራ ለማለት እፈልጋለሁ።

አዲስ መዳረሻን የማስተዋወቅ ጉዳይን በተመለከተ፣ እንደ እኛ የባላገሩ አስጎብኚ ድርጅት የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራን ነው ያለነው። በነገራችን ላይ ጦርነቱ የተካሄደባቸው አካባቢዎች፣ በሥም የማያውቋቸው ቦታዎች ስላሉ ወራሪው ኃይል ምን ያህል ኪሳራ እንዳደረሰ በዛውም ጉብኝት መዳረሻ አድርገን እየሠራን ነው ያለነው። ሔደውም እንዲጎበኙና የተጎዱትን እንዲያግዙ በፕሮግራማችን እያስተዋወቅን ነው የምንገኘው።

ኬንያ ዘርፉ እንዳይጎዳ ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች ጥሪ አድርጋለች ይባላል። ከዳያስፖራው በተጨማሪ የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለማበረታታት እዚህ እኛ አገር ያለው ሥራስ ምን ይመስላል?
የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ የመጎብኘት ባህላችን በጣም ያነሰ ነው። ይህ መነቃቃት መቻል አለበት፣ ቁጭት ሊፈጥርብን ይገባል። የማናውቃት ያልጎበኘናት አገር ስለሆነች ብዙ ላትናፍቀን ትችላለች። ስለዚህ በየቀኑ አምስትም ዐስርም ብር ቢሆን ቁጠባን ባህል አድርገን፣ በምንችለው አጋጣሚ ኹሉ አገራችንን የመጎብኘት ባህል መኖር አለበት።

ኹለት ትርፍ አለው። አንደኛ አገራችን እናውቅበታለን። ኹለተኛ የወደቀውን ኢኮኖሚ ማነቃቃት እንችላለን። እንዲሁም አንዱ ባህል ከሌላው ባህል ጋር የመተዋወቅ ዕድል ስለሚፈጥር፣ በዚህ መልኩ የአገር ውስጥ ጉብኝት ላይ መንግሥትም እንደ መንግሥት፣ አስጎብኚ ድርጅቶችን እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትም፣ ተባብረን የአገር ውስጥ ቱሪዝሙን ለማሳደግ መሥራት እንዳለብን ይሰማኛል።

ለአዲስ ማለዳ አንባቢዎች ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው፣ ‹ዞሮ ዞሮ መግቢያው ጭራሮ› የሚባል ነገር አለ። እንግዲህ ጉልበተኞችም እንደ አመጣጣቸው እየተመለሱ ነው ያሉት። ከጉልበተኛ ወይም ከአሸባሪ ጋር ያለን ኹኔታ እያለቀ እንዳለ ነው የሚሰማኝ። ኢትዮጵያውያን እንደ ኢትዮጵያውያን ትርፍ ሥራ ሠርተን በመከባበር፣ በመተባበር፣ በመደማመጥ፣ በመተዛዘን፣ ይቅርታን በማስቀደም ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ ማስቀጠል ያስፈልጋል።

ምክንያቱም እየተዋጋን ያለነው አንድ ወይም ኹለት ቡድን ጋር አይደለም። የኢትዮጵያ ዕድገት የማይፈልጉ አካላት ጣልቃ ገብነት ስላለ፣ እነዚህን ማሳፈር የምንችለው ሥራ በመሥራት ስለሆነ ነው። አገራችንንና ራሳችንን መቀየር ካስፈለገ፣ ሥራችንን ከስምንት ሰዓት ወደ 15 ሰዓት፣ በክፍያ ብቻ ሳይሆን የነጻ የሙያ አገልግሎት በመስጠት፣ ጎረቤትና ማኅበረሰብን በማሰብ፣ ተጨማሪ አገልግሎት በመስጠትና ያለውን በማሻሻል፣ ሠላም በማድረግ፣ እንዲሁም በመተባበር ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ አለብን ብዬ አስባለሁ።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here