የታሠሩ ጋዜጠኞችና የማይገደቡ መብቶቻቸው

0
988

በኢትዮጵያ ለእስር የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን ጉዳዩን በተመለከተ ክትትል የሚያደርጉ ድርጅቶች ሲናገሩ ይደመጣል።
በ2012/13 የወጣው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርትን ብንጠቅስ እንኳ፣ ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በዓመቱ ውስጥ በአገሪቱ የሚገኙ 51ሺሕ ታራሚዎችን በወህኒ ቤት እንደጎበኘ ያመላክታል።
ሰዎች ወደ ማረሚያ ቤት ለመውረድ የሚገደዱባቸው የተለያዩ ምክንያትቶች ይኖራሉ። ከእነዚህም ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን መጣስ አንዱና የወቅቱ ግንባር ቀደሙ መንስዔ ነው። ከ2014 በፊት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በርካታ ሰዎች ታሥረው እንደነበር ኢሰመኮን ጨምሮ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ሲዘግቡ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ከአቅም በላይ የሆኑ አገራዊ ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍትሔ ለማምጣት ታስቦ እንደ አንድ አማራጭ የሚወሰድ ውሳኔ መሆኑ ይታመናል። ሆኖም ግን፣ በርካታ ሰዎች በዘፈቀደ ወደ እስር ቤት የሚወርዱበት አጋጣሚ እንዳለም የኢሰመኮ መግለጫ ያሳያል።
ለአብነትም በ2012 መጋቢት 30 እና ነሐሴ 30 የኮቪድ ወረርሽኝን ሥርጭትን ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ወደ ተግባር ከተቀየረ በኋላ፣ 1ሺሕ 600 ዜጎች ‹‹ዐዋጁን ጥሳችኋል›› ተብለው እንደታሠሩና፣ ‹‹ዜጎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ዘፈቀዳዊና ሕገ-ወጥ ነው›› በማለት መግለጫ አውጥቶ ከእሥር እንዲለቀቁ ማድረጉን የወቅቱ የኢሰመኮ ሪፖርት አመላክቶ ነበር።

ታዲያ ከዚህ በኮቪድ ወርሽኝ ምክንያት ከታሠሩት ሰዎች መካከል ጋዜጠኞችም ተጠቃሽ ስለመሆናቸው ኢሰመኮ ገልጾ ነበር።

በወቅቱም ከጋዜጠኞች መካከል፣ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስና ኤልሳቤጥ ከበደ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ፣ 12 ጋዜጠኞችና የካሜራ ባለሙያዎች ከአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ሞት ጋር በተያያዘ፣ የአውሎ ሚዲያው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው በምዕራብ ወለጋ ከተገደሉ የአማራ ተወላጆች ጋር በተያያዘ፣ እንዲሁም የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሌሎችንም ጨምሮ ታሥረው እንደነበር ኢሰመኮ በ2012/13 ሪፖርቱ ገልጾ ነበር።

የጋዜጠኞች መታሠር አሁንም ቢሆን እየቀጠለ መምጣቱ ይነገራል። ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) በ2021 ባወጣው መረጃ መሠረት፣ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን መረዳት ተችሏል።
ድርጅቱ በቅርቡ ካወጣው መረጃ መረዳት የተቻለው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ 293 ጋዜጠኞች በእሥር ቤት መቆየታቸውን እና 24 ጋዜጠኞች ደግሞ ለሞት መዳረጋቸውን ነው።

ይኸው ድርጅት በ2020 ያወጣው ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በዓለማችን 274 ጋዜጠኞች ወደ እሥር ቤት እንደወረዱና 26 ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሠራተኞች በሥራቸው ምክንያት መገደላቸውን ያብራራል።
በመሆኑም የጋዜጠኞች የመታሠር አጋጣሚ በአንድ ዓመት ልዩነት ብናነጻጽር እንኳ፣ በዓመቱ ከ273 ወደ 293 ከፍ በማለት የ20 በመቶ ጭማሪ እንዳሳዬ መገንዘብ ይቻላል።

የዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጆኤል ሲሞን ‹‹ጋዜጠኞችን ዜና ዘግበዋል በሚል ማሠር የአምባገነን አገዛዝ መለያ ነው›› እንዲሁም፣ ‹‹በተለይ ማይናማር እና ኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነትን በሩን በአሰቃቂ ሁኔታ መዝጋታቸው በጣም አሳዛኝ ነው›› ሲሉ በሪፖርታቸው አስቀምጠዋል።

በአገራችን በቅርቡ ያለውን ነባራዊ እውነታ ብንመለከት እንኳ፣ በ2014 ከታሠሩት ጋዜጠኞች መካከል ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ፣ ታምራት ነገራ፣ መዓዛ መሐመድ፣ እያስፔድ ተስፋዬ ተጠቃሽ ናቸው።
ተጠርጣሪ ነው የተባለ አካል ተይዞ መታሠሩ ትክክለኛ አሠራር ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው ጋዜጠኞች ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ መቆየቱ ግን በብዙዎች ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል። ይህም አሁን የተሠሩ ጋዜጠኞች ከእስከሁኖቹ ለየት የሚያደርጋቸው፣ ፍትሐዊ ያልሆነ አሠራር ነው በማለት የጋዜጠኞቹ ቤተሰቦች ሲያወሱ ይደመጣሉ።

የታሣሪ ቤተሰቦቻቸው እንደሚሉት ከሆነ፣ ቅሬታቸው ፍትሐዊ ባልሆነው የጋዜጠኞቹ መታሠር ሳይሆን፣ የታሠሩበት ቦታ አለመታወቁ ላይ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
የአሐዱ ሬድዮ የዜና ክፍል ኃላፊና አርታኢ የሆኑት የጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ አባት፣ ወርቁ አብርሃ የተሠማቸውን ስሜት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሚከተለው መልኩ በደብዳቤ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከጥቅምት 16/2014 ጀምሮ፣ በሬድዮ ጣቢያው በተሠራ ዘገባ ምክንያት ልጃቸው ክብሮምን በተጠርጣሪነት በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው የሚናገሩት አባት፣ በወንጀል የተጠረጠረ ኹሉ ሕግ በሚፈቅደው መንገድ በቁጥጥር ሥር ውሎ፣ ወንጀሉ ተጣርቶ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ ወይም መለቀቅ ትክክለኛ አሠራር መሆኑን አልተቃወሙም።

ወርቁ በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት ከሆነ ግን፣ የመላ ቤተሰቡን ቅስም የሠበረው የክብሮም መታሠር ሳይሆን፣ ፍርድ ቤት ቀርቦ በዋስ እንዲለቀቅ ከተወሠነለት በኋላ ፖሊስ ሊለቀው አለመቻሉ ነው።
ኢሰመኮም በድረ-ገጹ ‹‹ከጥቅምት 16/ 2014 ጀምሮ በእሥር የቆዩት ክብሮም ወርቁ በኅዳር 9/2014 በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ከተፈቀደላቸው ጊዜ ጀምሮ ኢሰመኮ ይህን መግለጫ እስካወጣበት ጊዜ ድረስ፣ የተያዙበት ቦታ ለቤተሰቦቻቸው ባለመነገሩ የቤተሰብ ጥየቃ መብታቸው ያልተከበረላቸው ከመሆኑም በላይ፣ ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁ ኮሚሽኑን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስበው ነው›› ሲል መግለጹ ይታወሳል።

ኢሰመኮ አክሎም፣ በአስቸኳይ ጊዜ ኹኔታም ውስጥ ቢሆን ታሣሪዎች ያሉበት ኹኔታ ሊታወቅና በቤተሰብ እና በሕግ አማካሪ የመጎብኘት መብቶቻቸው ሊጣሱ አይገባም ሲል አሳስቧል።
ጋዜጠኛ ክብሮም ያሉበትን ማወቅ እንዳልተቻለና ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ እንዳልተፈቱ የጋዜጠኛው አባት ጠቁመዋል።

‹‹ለቀናት ደጅ ብንጠናም ከባድ የልብ ቀዶ ጥገና ያደረገውን ልጄን እንኳን የሚፈታልኝ፣ያለበትን አውቃለሁ የሚለኝ አጥቼ ተጉላላሁ›› የሚሉት የጋዜጠኛው አባት፣ ‹‹በመጦሪያዬ የታሠረ ልጄን ፍለጋ መንከራተት ብቻ ተረፈኝ›› ሲሉ ነው የደረሰባቸውን እንግልት ያብራሩት።
የክብሮም አባት ልጃቸውን ለማስፈታት የሚመለከተውን አካል ኹሉ ቢጠይቁም፣ ልጃቸው ካለበት ችግር መውጣት እንዳልቻለ በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።

‹‹የፍርድ ቤት ውሳኔ ተጥሶ ግልጽ ባልሆን አሠራር የት እንዳለ እንኳን በማላውቅበት ሁኔታ፣ የታሠረብኝን ልጄን ከእሥር ለማስለቀቅ፣ ለኢትዮጰያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ለኢትዮጰያ ዕምባ ጠባቂ ተቋም፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አመልክቼ አባ ከና የሚለኝ አጣሁ ያሉት ወርቁ አብርሃ፣ ከዚያ በኋላ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደብዳቤ ለመጻፍ ወስንኩ ብለው ደብዳቤውን እንደጻፉ ተናግረዋል።

አገራችን ጦርነት ላይ ብትሆንም ይህንን ሠበብ አድርገን ‹‹በሕግ ሥም ሕግን እንድንጥስ የሚያዝ የመንግሥት መመሪያ የለም›› የሚሉት ወርቁ፣ ክብሮም ከሽብርተኛ ቡድኑ ጋር ግንኙነት የለውም ብቻ ሳይሆን የሚጠየፋቸውም ናቸው ብለዋል። ለኢትዮጵያ ብቻ ባያዳላ ኖሮ ክብሮምን በአሐዱ ሬዲዮ፣ ያውም በኃላፊነት ቦታ ማግኘት ባልተቻለም ነበር ሲሉ ይመሰክራሉ።

ወርቁ አብርሃ ልጃቸው ጋዜጠኛ ክብሮም የታሠረው ምናልባት በሥሙ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ያስቀመጡ ሲሆን፣ የልጃቸውን ሥም “ክብሮም” ብሎ መሠየም ኃጢያቱ ምን እንደሆነና አባት ባወጣው ሥም ልጅ ለምን ዋጋ ይከፍላል ሲሉ ጠይቀዋል።
ክብሮም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ተላላኪ ለመሆኑ ፖሊስ ቅንጣት ያህል ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቅ ውሳኔ ቢሰጠውም፣ ፖሊስ ሊለቀው እንዳልቻለ ነው አዲስ ማለዳ ከጋዜጠኛው አባት መረዳት የቻለችው።
በልጃቸው መታሠር ከደረሰባቸው ቅሬታ በተጨማሪ፣ የቤተሰብም ሥም አብሮ በመጉደፉ የደረሠባቸው የሞራል ውድቀት በካሳ ሊተካ አይችልም የሚሉት ወርቁ፣ መንግሥት ልጃቸው በፍርድ ቤት የተሰጠው የዋስትና መብቱ ተከብሮ ወደ ቤቱ እንዲመለስ እንዲያደርግ እና እናቱን ከሠርክ ለቅሶና ሐዘን እንዲታደጋቸው አሳስበዋል።

ከጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ በተጨማሪ ሌሎች ጋዜጠኞችም እንደታሠሩ የታሣሪ ቤተሰቦች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ እንዲሁም ኢሰመኮን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ኹሉ እየመሠከሩ ነው።
ከእነዚህም መካከል የ‹‹ተራራ ኔትወርክ›› መሥራች የሆኑት ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በክብሮም ወርቁ ላይ የተፈጸመ ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማቸው እየተነገረ ነው። ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ባሳለፍነው ታኅሳስ 1/2014 ሲሆን፣ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ያሉበት ቦታ ባለመታወቁ ቤተሰቦቹ ጭንቀት ላይ እንደነበሩ ኢሰመኮን ጨምር የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ሲዘግቡ ቆይተዋል።

በተመሳሳይ ለእሥር ከተዳረጉት ውስጥ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ይገኙበታል። ባሳለፍነው ታኅሳስ 2/2014 ሲቪል በለበሱ ፖሊሶች ወደ ማረሚያ ቤት የተወሠዱት ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድን በተመለከተም አዲስ ማለዳ ቤተሰቦቿን ያነጋገረች ሲሆን፣ ቅሬታቸውን በሚከተለው መልኩ ገልጸዋል።

‹‹የብሮድካስት ፈቃድ ሳይኖርሽ ብሮድካስት አድርገሻል ብለው›› ሲቪል የለበሱ ኹለት ፖሊሶች ከቤት መጥተው ወስደዋታል የሚሉት የመዓዛ ባለቤት ሮቤል ገበየሁ ናቸው። እንደ ሮቤል ገለፃ፣ ምንም እንኳ መዓዛን ባሳለፍነው ታኅሳስ 8/2014 ፖሊስ ወደ ፍርድ ቤት ይዟቸው ቢሄድም፣ በኋላ ላይ “መርማሪ አልመጣም” በሚል ሠበብ ቀጠሮ እንዲራዘም መደረጉን ነው ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት።

መንግሥት በመዓዛ ላይ እንዲህ ያደርጋል ብዬ አስቤ ስለማላውቅ በድርጊቱ ተገርሜአለሁ የሚሉት ሮቤል፣ መዓዛ መሐመድ በሰሜን ወሎ፣ በተለይም በወለጋ ዙሪያ ላሉ ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ሥራዎችን የምትሠራ በመሆኗ ማበረታታት ሲገባ፣ የቤተሰቧን ስሜት በሚጎዳ መልኩ ለእሥር መዳረጓ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ይገልጻሉ።

ጊዜዋን የምታሳልፈው ችግር ስለደረሰባቸው ሰዎች ስትሯሯጥ ነው፤ ለልጇ እንኳ ጊዜ የላትም። እኔ ነኝ ቤት ውስጥ ያለውን ኹኔታ ራሱ የምከታተለው የሚሉት ሮቤል፣ እንዲያውም መንግሥት ይደግፋታል ብለን ስናስብ ነገሩ እንዲህ በመሆኑ ከማስገረምም በላይ አስደንግጦናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አያይዘውም፣ ጋዜጠኛዋ የልጅ እናት እና ሕመምተኛ አዛውንት አባት ተንከባካቢ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ከወለጋ አካባቢ ቤተሰቦቿ የሞቱባት ልጅ አምጥተው በፍቃደኝነት የሚያሳድጉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ባለቤታቸው በመታሠራቸው እነዚህ ኹሉ ሰዎች ችግር ላይ በመውደቃቸው የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በተመለተ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ከሚያስተምሩ የሕግ መምህር ተመስገን ሲሳይ (ፕ/ር) ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ ምላሻቸውን በሚከተለው መልኩ አቅርባዋለች።

ሐሳብን በነጻነት መግለጽን በሚጠቅሰው የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 29 መሠረት፣ ማናኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን መግለጽ እንደሚችል ይደነግጋል የሚሉት መምህሩ፣ ከዚህም በተጨማሪ አጠቃላይ ከመገናኛ ብዙኃንና ከመረጃ ነጻነት ዐዋጅ ጋር ተያይዞ መገናኛ ብዙኃንና ባለሙያዎቻቸው ያላቸውን መብቶችና ኃላፊነቶች የተቀመጡ ቢሆኑም፣ መብቶቹ ግን ገደብ የላቸውም ማለት አይደለም ነው ያሉት።

ለአብነትም በአንቀጽ 29 የተቀመጡት መብቶች የአገር ሠላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ፣ የወጣቶችን ሞራል ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ ኹኔታዎች ሲያጋጥሙ፣ የሚገደቡበት ኹኔታ አለ የሚሉት ተመስገን፣ ይህም በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ወቅት ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።
እነዚህ መብቶች በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ወቅት ቢገደቡም፣ የሚዲያ ባለሙያ በሕግ ከተያዘ በኋላ በምን ዓይነት መልኩ መስተናገድ እንዳለበት በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ውስጥም የተቀመጡ መሥፈርቶች አሉ ብለዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ተጠርጥሮ የተያዘ አካል ከተያዘ በኋላ በአግባባቡ በሕግ ሊስተናገድ እንደሚገባ ተደንግጓል ያሉት ተመስገን፣ አያይዘውም ይህ ማለት የተያዘውን ግለሰብ ሊሠወር ወይም አድራሻው ሊጠፋ የማይገባ መሆኑን አመላካች ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ተመስገን አያይዘውም፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ወቅት የሚገደቡ መብቶች እንዳሉ ሆነው፣ የሰውን ልጅ መሠወርና ማጥፋት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል በማለት አብራርተዋል።

በሆነ ጉዳይ ተጠርጥሮ የታሠረ ሰው የታሠረበት ቦታ መታወቅ እንዳለበትና በቤተሰቦቹ መጎብኘት እንዳለበት ዕሙን ነው።

አንድ የታሠረ ሰው ካሉት መብቶች መካከል አንዱ በቤተሰብ፣ በኃይማኖት አባት፣ እንዲሁም በሕግ ባለሙያዎቹ የመጠየቅና የመጎብኘት መብት አለው የሚሉት የሕግ መምህሩ ተመስገን ሲሳይ ናቸው።
ከተመስገን አባባል መረዳት የተቻለው፣ የታሠረ ሰው የመጎብኘት መብት በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ሊገደብ የማይችል ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ ታራሚው ቢታመም መታከም፣ የቤተሰቦቹን ደኅንነት ማወቅ፣ ብሎም በጠበቃ ወይም በኃይማኖት አባት አማካይነት የምክር አገልግሎት ማግኘት ስለሚያስፈልገው መሆኑን ነው መረዳት የተቻለው።

አክለውም፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ወቅትም ቢሆን የታሠሩ ሰዎችን ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጠበቆቻቸው፣ ከኃይማኖት አባታቸው ጋር እንዳይገናኙ ማድረግ የማይገባና የተከለከለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
ሌላኛውና በብዙዎች በኩል ቅሬታ ያስነሳው ጉዳይ፣ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ተጠርጥረው የታሠሩ ሰዎች ሕግ ጥሳችኋል በተባሉበት አካባቢ በሚገኝ ማረሚያ ቤት መቀመጥ ሲገባ ይህ እየሆነ ያለው በተቃራኒው መሆኑ ነው።

ይህን በተመለከተም የሕግ መምህሩ ማንኛውም ተጠርጣሪ መታሠር ያለበት ወንጀሉን በፈጸመበት አካባቢ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አይይዘውም፣ ወንጀሉ ከተፈጸመበት አካባቢ ውጭ ሰውን ወስዶ ማሠርና መሠወር ፍጹም የሆነ የመብት ጥሠት መሆኑን መገንዘብ ይገባል ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማኅበር በበኩሉ፣ ባሳለፍነው ታኅሳስ 5/2014 ባወጣው መግለጫ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታሠሩ ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑንና ጋዜጠኞች በትክክል ባልታወቀ ምክንያት መታሠራቸው በጋዜጠኝነት ትግበራ ነጻነት ላይ ለወደፊት እንከን እንዳይሆን አሳስቧል።

ማኅበሩ አክሎም፣ በጸጥታ ኃይሎች የታሠሩ ጋዜጠኞች የሕግ መብታቸው ተጠብቆ ፍትሕ እንዲያገኙና በቤተሰቦቻቸውም የመጎብኘት መብታቸው እንዲከበር አሳስቧል።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here