ዶላርን ለአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ንግድ መጠቀምን የመቀየር ዘመቻ

0
815

ከኢትዮጵያ ብሎም ከአፍሪካ ጉስቁልና ጀርባ ብዙ ያደፈጡ ነገሮች መኖራቸውን በርካቶች ይስማሙበታል። አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ተስማምተው በይፋ ወደ አፍሪካ በመግባት ለበርካታ ዓመታት አኅጉሪቷን ከመዘበሩ በኋላ ለቀው ቢወጡም፣ አሁንም ድረስ በመሠሪ ሥራቸው አፍሪካን የርስበርስ ግጭት ዓውድማ፣ የሥደት መነሻ እንዲሁም የጥልቅ ድህነት መገኛ እንድትሆን አድርገዋታል ማለት ይቻላል።

ኹለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ያደረሰውን ትልቅ የኢኮኖሚ ድቀት ተከትሎ፣ በሐምሌ ወር 1936 አሜሪካ ብራይተንዉድ ላይ በተደረገ ኮንፍረንስ፣ ዛሬ አይ.ኤም.ኤፍ.ተብሎ የሚጠራው ዓለም አቀፉ የገንዘብ አበዳሪ ተቋም እንደተመሠረተ ይነገራል። ዓላማው በጦርነት የወደመውን የአውሮፓ አህጉር መልሶ ለመገንባትየትብብር የገንዘብ ማዕከል መገንባት በሚል የነበረ ቢሆንም፣በውስጡ ግን የጥቂት አገራትን የበላይነት የሚያረጋግጥ ሴራ እንደነበረው በብዙዎች ይታመናል። የአንድ አገር የመገበያያ ገንዘብ (ዶላር) የበርካታ አገሮች የጋራ መገበያያ እንዲሆን የሐሳብ ጥንስሱ የተጣለውም ከዚያ አሜሪካ የበላይ ከሆነችበት ኮንፈረንስ ጀምሮ እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ።

አገሮች ቀድሞ ለሚደረግ የንግድ ልውውጥ ወርቅን እንደዋነኛ መገበያያ ይጠቀሙ እንደነበርም ይታወቃል። ይሁን እንጂ ከዓመታት በኋላ ዶላር በአገራት መካከል ለሚደረግ የንግድ ልውውጥ ጥቅም ላይ ሲውል አገራት በወርቅ ዶላር መግዛት መጀመራቸው ነው የሚነገረው። ይህም አሜሪካ በነበራት በርካታ የወርቅ ክምችት ላይ ተጨማሪ ወርቅ ማግኘት እንድትችል ያደረጋት ሲሆን፣ በኋላ ግን ወርቅ እንደገና ተፈላጊነቱ እየጨመረ ሲመጣ በወርቅ ዶላር መግዛቱን በማስቀረት ከዶላር ጋር ያለውን ትሥሥር አሜሪካ አቋርጣዋለች።

ከዚያም በቀጠለ በአገራት መካከል ከሚደረግ የንግድ ልውውጥ በተጨማሪ፣ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ አገር በቀል የንግድ ተቋማት ሳይቀሩ ግብይታቸውን በዶላር ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይህ ደግሞ የዶላር ዕጥረት የሚፈጥር በመሆኑ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል አገሮች ዶላርን እየገዙ እንዲያከማቹ አስገድዷቸዋል ነው የሚባለው። ይህም አሜሪካ ዶላርን በመሸጥ ብቻ ጥቅም እንድታገኝ አስችሏታል።

ይህ የአሜሪካ ድርጊት ከአውሮፓ ወጥቶ በመላው ዓለም ተግባራዊ መሆን ሲጀምር፣ በተለይ ለአፍሪካ የመርዶ ያህል እንደሚሆን የገመቱ መኖራቸው ይነገራል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እንዲሁም በዩኒቲ ዩንቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ደምመላሽ ሀብቴ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ላይ ለአዲስ ማለዳ በሠጡት ማብራሪያ፣ ዶላር ዓለም አቀፍ መገበያያ በመሆን ተጽዕኖው እየጎላ የመጣው ከፈረንጆች 1973 ጀምሮ ነው ይላሉ። ዶላር ለዓለም አቀፍ ንግድ የዋለበት ምክንያትም እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ አገሮች ባደረጉት የንግድ ሥምምነት እንጂ በኃይልአይደለም። በውጭ ገበያ ሻጭና ገዥ በሚያደርጉት ግብይት ዋጋ የሚተምኑት በዶላር እንዲሆን ሥምምነት ላይ ተደርሶ ነው። ከዚያ በፊት ግን ወርቅን መሠረት ያደረገ ግብይት ነበር የሚደረገው ብለዋል። ባለሙያው አክለውም፣ከዚያ ጊዜ ወዲህ የወርቅን ቦታ ዶላር እንዲተካው በመደረጉ ብዙ አገሮች ጫና ውስጥ መውደቃቸውን አውስተዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ያላደጉ አገራት፣ ግብርና መር የሆነ ኢኮኖሚያቸውን ወደ ኢንዱስትሪ መር ለመቀየር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ፣ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከአደጉ አገራት በሚገዙበት ጊዜ ግዴታ ዶላር የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ጠቅሰው፣የዶላር ዕጥረት እያጋጠማቸው ሲሄድ በዚያው ልክም በዋጋ ግሽበት መጎዳት መጀመራቸውን ነው ባለሙያው ያነሱት።

በአገራት መካከል የሚደረገው የውጭ ንግድ ግብይት በብዙ አገሮች ተቀባይነት ባለው ዶላር ይሁን እንጂ፣ ሌላ መገበያያ የለም ማለት አይደለም። ባለሙያው እንደገለጹትም፣ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ምንዛሪ ያለው ፓውንድ አንዱ ነው። ይህም የሆነው ተፈላጊነቱ የላቀ በመሆኑና በቅኝ ግዛት ዘመን በርካታ አገሮች ከእንግሊዝ ጋር በፈጠሩት ቁርኝት የመጣ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም።

ሆኖም በዚህ ከቀጠለ የከፋ የምጣኔ ሀብት ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ፣ አሜሪካም ትሁን ምዕራባውያኑ በዚህ መልኩ ያላደጉ አገራት ላይ ጫና መፍጠራቸውን መከላከል እንደሚገባ ነው የጠቆሙት። ይህን ተጽዕኖ ለመቀነስምሦስት የመፍትሔ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ነው ያሳዩት።

የመጀመሪያው ዶላርን የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ግዴታ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ለመሸመት መጠቀም ነው። እስካሁን ባለውም ሁኔታ፣ ካለው ዝቅተኛ ኢኮኖሚ አንጻር፣ ኢትዮጵያን ለማሳደግ በሚደረግ የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ከዶላር ሙሉ በሙሉ መላቀቅ እንደማይቻል ተናግረዋል። ሆኖም ዶላርን አስፈላጊ ለሆነ ግዥና ሽያጭ ብቻ ጥቅም ላይ ማዋል ተጽዕኖውን እንደሚቀንሰው ለማሳየት ሞክረዋል።

ቀጣዩ የመፍትሔ አማራጭ ያሉትከአገራት ጋር በራስ ገንዘብ መገበያያት መቻል ሲሆን፣ ይህምተጽዕኖውን ለመቀነስ ጉልህ ድርሻ አለው።በአገራት መካከል የርስበርስ ትሥሥርን ከማሳደግም በላይ ቀልጣፋ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር ያደርጋል። ለአብነትም ከቻይና ጋር ለሚደረግ የንግድ ልውውጥ ዶላርን መጠቀም አቁሞ በኹለቱ አገራት መገበያያ ገንዘብ ለመጠቀም ሥምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ነው ያሉት ባለሙያው። በዚህ ረገድ የሚፈጠረውን የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ከማስወገድ አልፎ ዶላር ወይም ፓውንድ ለመግዛት የሚውል ተጨማሪ ገንዘብ ማትረፍ እንደሚቻልም ገልጸዋል።

ሌላው መፍትሔያሉት፣ የዓይነት ግብይት ሥርዓትን (bartering system) መከተል ነው። ይህ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመለዋወጥ የሚደረግ የንግድ ዘዴ የቀድሞዋ ሶቭዬት ኅብረት አገሮች ለ50 ዓመት ገደማ በግብይት ሥርዓት ከምዕራባውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖራቸው ሲጠቀሙበት ኖረዋል። የግብርና ምርት የምታመርት አንዲት አገር፣ መኪና ከምታመርት ሌላ አገር ጋር በተተመነ ዋጋ ልውውጥ ያደርጋሉ። ይህም ግብይታቸውን ከምንዛሪ ገንዘብ ነጻ ያደርገዋል።

በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ እስካሁን ከ20 በመቶ ማለፍ ያልቻለ ነው ያሉት ባለሙያው፣ አህጉሪቱ ከላይ የተጠቀሱትን የንግድ ሥርዓት አማራጮች መጠቀም ብትችል ዕድገት እንደምታመጣ ገልጸዋል። ነዳጅ፣ የግብርና ምርት፣ የማሽን መለዋወጫዎችን፣ ማዕድናትንና የእንስሳት ውጤቶችን በስፋት ለዓለም ገበያ የምታቀርበው አፍሪካ፣ እስካሁን ድረስ ማደግ ያልቻለችው ዶላርን መሠረት ካደረገው የንግድ ግብይት መውጣት ባለመቻሏ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የዚህም ማሳያው በአህጉሪቱ ባሉ አገሮች የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት በመኖሩ፣ ኹሉም የአፍሪካ አገራት ምርታቸውን የሚያቀርቡት ለአፍሪካ ገበያ ሳይሆን፣ ዶላር ማግኘት ለሚያስችላቸው ለምዕራባውያን ገበያ መሆኑ ነው ብለዋል። አፍሪካውያንየሚገበያዩበትአንድ ወጥ ገንዘብ ቢኖር ወይም በየራሳቸው ገንዘብ መገበያያት ቢችሉ ግን የአንዱን ምርት ለሌላው በማቅረብ ሠፊ ገበያ መፍጠርናከምዕራባውያን ጫና ወጥተው በቀላሉ ማደግ እንደሚችሉ አመላክተዋል።

ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከቅኝ ገዥዎች ነጻ የሆኑ በርካታ አገራት እስካሁን የፖለቲካ እንጂ የኢኮኖሚ ነጻነት እንዳላገኙ ይነገራል። በዚህም ከ150 በለይ አገራት አሁንም ድረስ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ከጦርነቱ በኋላ የተዘረጋው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት (Global Economic Order) ካፒታሊስት የሆኑ አገሮችን እንዲጠቅም ሆኖ የተበጀ እንደሆነ ምሁራን ይገልጻሉ። ይህም ሥርዓት ድሃ አገራት ያደጉ ካፒታሊስት አገሮች ጥገኛ ሆነው እንዲኖሩና ጥሬ ዕቃቸውን በርካሽ እንዲሸጡ፣ በተመሳሳይም የበለጸጉ ካፒታሊስት አገሮች የፋብሪካ ምርት ውጤቶችን ለድሃ አገራት በውድ ዋጋ እንዲሸጡ የሚያደርግ ነው።

አሁን ላይ ይህ ሥርዓት መቀየር ያለበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስላል የሚሉት ደመላሽ፣ ጫና የደረሰባቸው አገሮች በተናጠልና በቡድን ሆነው ለመከላከል ሙከራ ሲያደርጉ እንደሚስተዋል አንስተዋል። አውሮፓም በሌሎች ታዳጊ አገራት ላይ የራሷን ጫና በማሳደር ላይ ብትሆንም፣ ራሷን አሜሪካ መር ከሆነው የአሁኑ የዓለም ኢኮኖሚ ሥርዓት ተጽዕኖ ለማላቀቅ፣የአውሮፓ ኅብረትንበመመሥረት እና የአባል አገራቱን ቁጥር በማሳደግ የራሷን አህጉራዊ የንግድና የኢኮኖሚ ትሥሥር መፍጠሯን ነው የተናገሩት። ይህም ለአፍሪካውያን ጥሩ ተሞኮሮ መሆን እንደሚችልና አፍሪካምየራሷን የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመፍጠር መሥራት እንደሚገባትአጽንዖት ሰጥተውበታል።

በተጨማሪም፣ ከፈረንጆች 1989 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ ትልቅ ጫና እየፈጠረ ያለውን ካፒታሊዝም ለመመከት ‹‹BRICS›› በሚል መጠሪያ፣ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ ኅብረት መሥርተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ነው የገለጹት። በአፍሪካም የሰሜን፣ የደቡብ፣ የምሥራቅና የምዕራብ የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች በመኖራቸው፣ ይህን ታሳቢ አድርገው ቢንቀሳቀሱ ከጫናው መውጣትና የዕድገት ጎዳና ውስጥ መግባት እንደሚቻል ያወሳሉ።

ሶሻሊዝም እንደ ሥርዓት ከወደቀ ጀምሮ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኅብረት የሚመራው የኢኮኖሚ ሥርዓት ካፒታሊዝምንመርህ ያደረገ የአንድ አካል የበላይነት የገዘፈበት በመሆኑ፣ በተለይ ያላደጉ አገራት ከካፒታሊዝም ሥርዓት ውጭ ሌላ አማራጭ እንዳይኖራቸው ያደረገ መሆኑ ይነገራል። ይህም የድሃ አገራትን ጉስቁልና ያባባሰ ሲሆን፣ አሜሪካም በሌሎች አገራት ላይጨዋነት የጎደላት በሕግ የማትመራ አገር እንድትሆን አድርጓታል ነው የሚባለው።

ቻይናና ሩሲያ በዚህ ረገድ ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ የሚደርሰውን ጫና ለመከላከል በግንባር ቀደምትነት ከሚንቀሳቀሱ አገራት ውስጥዋናዎቹ መሆናቸውንሲገልጹ ይስተዋላል። በዚህም አንድ ጊዜ በዓለም ላይ የጋራ የሆነ መገበያያ ገንዘብ መኖር አለበት ሲሉ፣ ሌላ ጊዜም በኹለቱ አገራት መካከል የሚደረጉ የንግድ ልውውጦችን በራሳቸው መገበያያ ገንዘብ ለማድረግ ሙከራ አሳይተዋል። ይህም በአሜሪካ የሚጣልባቸውን ማዕቀብ ከማክሸፍም በላይ በዶላር ዕጥረት የንግድ እንቅስቃሴያቸው እንዳይሰተጓጎል እና በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ከሚቸገሩ አገራት በላይ ፈጣን ዕድገት እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል ነው የሚባለው።

ኢትዮጵያም ከዚህ ጫና ለመውጣት ከሚንቀሳቀሱ አገራት ጋር አብሮ በመሰለፍ ዶላርን መሠረት ባደረገው ንግድና ኢኮኖሚ ከሚደርስባት ጫና ራሷን መከላከል እንደሚገባት ምሁራን ይጠቁማሉ። አሁን ላይ ይህን ዓይነት እንቅስቃሴ በይፋ ብትጀምር የሚደርስባት ወከባና ጫና የበለጠ ሊሆን ይችል ይሆናል የሚሉ አሉ። ነገር ግን፣ አሁን ሳትሞክር ከሚደርስባት ኢኮኖሚያዊ ጫና ለውት ብታደርግ የሚደርስባት በእጀጉ የሚያንስ በመሆኑ ጥረት ማድረግ አለባትም ይላሉ ምሁራኑ። ቢሆንም ደግሞ ማንኛውም አገር የፈለገውን የማድረግና የመረጠውን የኢኮኖሚ መንገድ የመከተል ሙሉ መብት ስላለው፣ የሚወስነው ከጫናው ለመውጣት የሚያደርገው የትግል ዘዴ ነው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው የገለጹትም፣ በተለይ የአፍሪካ አገራት ከገቡበት የኢኮኖሚ አዘቅት ለመውጣት በመጀመሪያ የጠቀሱትንመፍትሔ እንደ አስፈላጊነቱ ከመጠቀም በተጨማሪ፣ በኹለተኛና ሦስተኛነትያቀረቡትየመፍትሔ አቅጣጫ ላይ በደንብ ማተኮር እንደሚገባ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው የአፍሪካ አገራት አሁን ካለባቸው የኢኮኖሚ ውድቀት የባሰ ችግር የሚያጋጥማቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።

አፍሪካም በዶላርና ሌሎች የውጭ ምንዛሪዎች የሚደርስባትን የኢኮኖሚ ተጽዕኖ የ”#በቃ”(#NoMore) ዘመቻ አንድ አካል አድርጋ የራሷን መገበያያ ገንዘብ በመፍጠር እና አስቀድሞ በኅብረቱ አባል አገራት የታሰበውን አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጠና አጠናክራ በመቀጠል፣ በኢኮኖሚ ማደግና ከአዲሱ ቅኝ ግዛት መላቀቅ ይኖርባታል በማለት ጠንከር ያለ ሀሳብ የሚሠነዝሩ አካላት በርካታ ናቸው።

በግለሰብና በኩባንያ ደረጃም፣ ዶላርን የሚያከማቹም ሆኑ ለንግድ ቻይናና ዱባይ የሚጓዙ ከዶላር ሌላ የየአገራቱን መገበያያ ገንዘብ በአማራጭነት እንዲጠቀሙ የመቀስቀስና የማግባባት ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም የሚናገሩ አሉ። በአንድ ጊዜ ለውጥ ማምጣቱ ከባድ ስለሚሆንም ከአሁኑ ጀምሮ ቀስ በቀስ መሠረታዊ አስተሳሰቦችንና መርሆዎችን በመለወጥ ወደ ተግባር መግባት እንደሚቻል ምሁራኑ ይጠቁማሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 164 ታኅሣሥ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here