የአፍሪካ ኅብረት ለፍልስጥኤም ምን ይፈይድ ይሆን?

Views: 187

አንድም የፍልስጥኤም ተወካይ ባልተጋበዘበት ነበር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “..የእስራኤልንና የፍልስጥኤምን ሕዝብ ሕይወት የማሻሻል ርዕይ የሰነቀ የሰላምና ብልጽግና ርዕይ ነው” ያሉትን እቅድ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ያደረጉት። ይህንንም ተከትሎ ከተባበሩት መንግሥታትም የፍልስጥኤምን አገረ-መንግሥትነትን የተቀበሉ በርከት ሲሉ አሜሪካንና እስራኤልን ጨምሮ ጥቂቶች ፍልስጥኤምን እንደ አገር እውቅና አልሰጡም። እቅዱም ፍልስጥኤምን ከምድር ገጽ ለማጥፋት ያሰበ ነው ተብሏል። የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ይህን ጉዳይ አንስተው፣ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የአፓርታይድ ስርዓት በማጣቀስና በፍልሥጥኤም እየሆነ ካለው ጋር በማነጸጸር፣ የትራምፕን ድርጊትና እቅድ አውግዘዋል። ግዛቸው አበበም የአፍሪካ ኅብረትና የአፍሪካ መንግሥታት ለፍልስጥኤማውያን መብት መከበርና ለፍልስጥኤም አገራዊ ሕልውና መቀጠል የሚጠቅም ምን ፋይዳ ያለው ነገር ጠብ ያደርጉ ይሆን ሲሉ ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበርነትን ከግብጹ ፕሬዝዳንት የተረከቡት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በተናጠል ያዘጋጁትን የእስራኤል-ፓለስታይን የሰላም እቅድ መረር ባለ አነጋገር ኮንነውታል። ራማፎዛ ይህን በፍልስጤማውያን ላይ ተጫነ ያሉትን የሰላም ዕቅድ የደቡብ አፍሪካ የነጮች አፓርታይድ አገዛዝ በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ላይ ለዓመታት ጭኖት ከኖረው፣ ጥቁር አፍሪካውያንን ከሰው እኩል ከማያየው ከባንቱስታን የሽብር የአገዛዝ ስልት ጋር አመሳስለውታል። በርካታ የአፍሪካ መሪዎችም የትራምፕን ዕቅድ መቃወማቸውን ‹ታይምስ ኦፍ እስራኤል› የተባለው መገናኛ ብዙኀን ዘግቧል። ራማፎዛ እንደ አፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነታቸውም ሆነ እንደ ደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትነታቸው ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችም እንደ አገር መሪነታቸው አደገኛውን የትራምፕን ዕቅድ ለመቃወምና ለፍልስጥኤም አገራዊ ሕልውና ሊያርጉት የሚችሉት ምን ነገር ይኖር ይሆን?

ዶናልድ ትራምፕ “..የእስራኤልንና የፍልስጥኤምን ሕዝብ ሕይወት የማሻሻል ርዕይ የሰነቀ የሰላምና ብልጽግና ርዕይ ነው” ብለው የደሰኮሩለትንና በአጭሩ “የትራምፕ የሰላምና ብልጽግና ዕቅድ” ተብሎ የሚጠራውን እቅዳቸውን ይፋ ያደረጉት እ.ኤ.አ. ጥር 28/2020 ኋይት ሃውስ ውስጥ ከእስራኤል ፕሬዝዳንት ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ጊዜ ነው። በቦታው የተገኘ (የተጋበዘ) አንድም የፍልስጥኤም ተወካይ አልነበረም። እንዲያውም ‹ፎሬን ፖሊሲ› በድረ ገጹ ላይ የፍልስጥኤም ተወካይ በቦታው እንዳይገኝ ትራምፕ ራሳቸው ክልከላ እንዳኖሩ በሚገልጽ አርእስት ስር፣ ሰፊ ዘገባ ለንባብ አብቅቷል። ፎሬን ፖሊሲ አክሎም ትራምፕ የ40 ዓመት ዕድሜ ባለ ጸጋ ከሆነውን የእስራኤል ዕቅድ በቀጥታ ኮርጀው ያዘጋጁትን ፕሮፖዛል ለመተግበር በፍልስጤማውያንም ሆነ በሌሎች ላይ ጫና ማሳደርን እንደ ዋና ስትራቴጂ ሊጠቀሙ ይችላሉ ሲል ስጋቱን አስተጋብቷል።

ትራምፕ ይህን እቅዳቸውን ከጎናቸው ለነበሩት ለኔታንያሁ ቀደም ብለው አቅርበውት ‘ይህ ነገር ጥሩ አይመስልህም?’ ብለው መለኪያ በማጋጨት የኹለቱ ስምምነት ተገልጾበት ለአደባባይ አበቁት ብሎ መናገር ይቻላል። ነገሩን አሻጥር ወይም አራዳነት ብሎ መግለጽም ይቻል ይሆናል፤ ፍልስጤማውያን ‘ተረስተው’ የአሜሪካና የእስራኤል መሪዎች ፍልስጤማውያንን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለመወሰን ደፋር ሆነዋል። ዶናልድ ትራምፕ 181 ገጽ ስላለው ዕቅዳቸው ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ለእስራኤል የሚሰጡ ሙዳ ሙዳ ጥቅማ-ጥቅሞች ሲዘረዘሩና ፍልስጥኤም በብዙ ጥብቅ ቁጥጥሮች ስር የገባች የታሳቢ መንግሥትነት ሕልውና እንደሚሰጣት ሲተነትኑ፣ ከትራምፕ ጎን የቆሙት ቤንጃሚን ኔታንያሁ በደስታ ይፍለቀለቁ ነበረ ብሏል፤ ዘ-ጋርድያን።

ኔታንያሁ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መንግሥታቸው በአሜሪካ ድጋፍ የዮርዳኖስ ሸለቆንና የምዕራባዊው ዳርቻ ስፈራዎች የሚገኙባቸውን ቦታዎች ወደ እስራኤል ግዛት ፈጥነው እንደሚቀላቅሉ፣ ቢያንስ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት አዳዲስ ሰፈራዎች እንደማይገነቡ ተናግረዋል። ትራምፕ “ዛሬ እስራኤል ለሰላም ትልቅ እርምጃ እየወሰደች ነው…” ማለታቸውን የዘገበው ዘ-ጋርድያን፣ ትራምፕ ስለ ራሳቸው “… እኔ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኜ የተመረጥኩት ትንንሽ ጉዳዮችን በመፈጸም ጊዜዬን ለማባከን ወይም ከትልልቅ ችግሮች ለመሸሽ አይደለም….” ማለታቸውን አስነብቧል።

በዚያ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኔታንያሁ ዕቅዱን ‘የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ዕቅድ’ ብለው ሲያደንቁት ተሰምተዋል። በግልጽ እንደሚታየው እቅዱ ፍልስጤማውያንን ያገለለና እንደ ባለ ጉዳይም ያልቆጠረ አጀማመር ነው ያለው። ይህ እቅድ ከፈረንጆች አቆጣጠር ከኅዳር 2017 ጀምሮ በትራምፕ አማካኝነት በተዋቀረና በትራምፕ መሪነት በሚሠራ ኮሚቴ እየተዘጋጀ የቆየ ሲሆን፣ ትራምፕም ሆኑ ከሚቴው አንድም ጊዜ ቢሆን የፍልስጤማውያንን ተወካይ ጋብዘው በእቅዱ ላይ አላማከሩም።

አስገራሚው ነገር ትራምፕ የሰላም ዕቅድ እንዲዘጋጅ እንደሚሠሩ በተናገሩ በኹለት ወር ውስጥ የትኛውም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ያላደረገውን ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት ብሎ እውቅና የመስጠትና የአሜሪካን ኤምባሲ ወደ ኢየሩሳሌም የማዛወር እርምጃ መውሰዳቸው ነው። ከዚህ ሌላ ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ አቆጣጠር የካቲት 2017 ላይ አሜሪካ ኹለት መንግሥታት በሚለው መፍትሔ እንደማትገዛ በግልጽ ተናግረዋል። ትራምፕ ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ የሠሩት ነገር የፍልስጤማውያን ብርቱ ተቃውሞ ቀስቅሷል፤ ትራምፕም ሰበቦችን ደርድረው ለፍልስጥኤም የሚደረግ ዕርዳታ እንዲቋረጥ አድርገዋል።

ከተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ውስጥ 138 አገራት የፍልስጥኤምን አገረ-መንግሥትነት የተቀበሉ ሲሆን፣ አሜሪካንና እስራኤልን ጨምሮ በጣም ጥቂት አገራት ለፍልስጥኤም አገር መሆን እውቅና አልሰጡም። አሜሪካ የእስራኤል ሰፈራዎች ሕገ-ወጥ አይደሉም የምትለውም ለዚህ ነው። ዶናልድ ትራምፕ ለእስራኤልና ለፍልስጥኤም ሰላምና ብልጽግናን ያስገኛል ያሉትን እቅድ ያዘጋጁት፣ በዚህ የአሜሪካ አቋም ላይ ተመሥርተው ነው። እቅዱን ፍልስጥኤምን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የተቃረበ ፕሮጀክት ያስመሰለውም ይህ ነው።

የእቅዱን ይፋ መሆን ተከትሎ፣ የፍልስጥኤም መሪዎች ዕቅዱን ‘ለእስራኤል የሚያዳላ’ በማለት ወዲያውኑ ነው የተቃወሙት። የትራምፕን እቅድ የፍልስጥኤም ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ ‘የክፍለ ዘመኑ ጥፊ’ (slap of the century) ሲሉት የፍልስጥኤም ነጸ አውጭ ድርጅት (PLO) ዋና ጸሐፊ ሰዒብ አረካት ደግሞ ‘የክፍለ ዘመኑ ማጭበርበር’ (fraud of the century) በማለት እንዳጣጣሉት ሮይተርስና አልጀዚራ ዘግበዋል። ከእነዚህ መሪዎች በተጨማሪ አንዳንድ መገናኛ ብዙኀንም የትራምፕን ዕቅድ ለዚህ ክፍለ ዘመን ለየት ያለ ጉዳይ አድርገው አይተውታል። ዘ-ኢኮኖሚስት ‘የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ስርቆት’ ሲለው የእስራኤሉ ሐሬትዝ ደግሞ ‘የትራምፕ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ የሰላም እቅድ- የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ቀልድ ይሆናል’ ብሎ አጣጥሎታል።

ተቃውሞው ቀጥሎ የዓረብ ሊግ ‘ወደ ሰላም የማያመራ’ ብሎ ሲያጣጥለው የተባበሩት መንግሥታት እቅዱን በጥርጣሬ የተመለከተው መሆኑን በሚያሳብቅ አኳኋን ‘ከ1967ቱ የስድስት ቀን ጦርነት በፊት በነበረው ድንበር ላይ የተመሰረተ የኹለት መንግሥታት (የፍልስጥኤምና የእስራኤል) ሕልውናን የሚቀበል መፍትሔን ብቻ እደግፋለሁ’ በማለት በዋና ጸሐፊው በአንቶንዮ ጉተሬዝ በኩል መግለጫ ሰጥቷል። የአውሮፓ ኅብረት ዕቅዱን ‘ዓለም አቀፍ ስምምነት ያረፈባቸውን መመዘኛዎች የጣሰ፣ የፍልስጥኤምን ምድር ለመጠቅለል ያሰፈሰፈ፣ ከተተገበረም ከፍተኛ እክል የሚገጥመው’ ብሎታል። ቱርክ ‘የፍልስጥኤማውያንን መሬት ለመዝረፍ’ የተዘጋጀ ዕቅድ ነው ስትል፣ ኢራን ደግሞ ‘አካባቢውንና ዓለምን በቀጣይነት ለአስፈሪ ቅዠት የሚዳርግ’ ብላዋለች።

ቻይናና ሩስያ እቅዱ ‘የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔዎችንና ስምምነቶችን ረምርሞ ማለፍ የለበትም’ በማለት በተዘዋዋሪ የተቃወሙት ሲሆን፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ መጀመሪያ ላይ የሰላም ዕቅድ መዘጋጀቱን አድንቀው ቆየት እያሉ ደግሞ በተለያዩ ባለሥልጣኖቻቸው በሚሰነዝሩት ሐሳብ ‘ኹለት አገራት’ የሚለው ስምምነት ሊዘለል አይገባም፣ ‘አንዱን ወገን ያገለለ ዕቅድ አደገኛ መዘዝ ሊኖረው ይችላል’ ሲሉ ተሰምተዋል።

ቀጥሎ በሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ የዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኝ ለመሆን ከሚወዳደሩት የዴሞክራቲክ ፓርቲው ዕጩዎች ብዙዎቹ የትራምፕን እቅድ ተቃውመዋል።

የሰላምና ብልጽግና እቅድ የተባለው ፕሮጀክት በጥልቀት ሲመረመር ዶናልድ ትራምፕ ለፍልስጥኤማውያን ያላቸውን ጥላቻ ብቻ ሳይሆን ፍልስጥኤም ለምትባለው አገር ሕልውና ብዙም የማይጨነቁ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ተጨማሪ እርምጃ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።

የዶናልድ ትራምፕ ‘የሰላምና የብልጽግና ዕቅድ’ ዋና ነጥቦች ምን ምን ናቸው?
እቅዱ በኹለት ጎራ የተደራጁ ዝርዝር እቅዶችን የያዘ ሲሆን፣ ኹለቱ የእቅዱ ጎራዎች ‘ኢኮኖሚያዊ እቅድ’ እና ‘ፖለቲካዊ እቅድ’ ናቸው። ይህም ኹለቱ አገራት ሊስማሙባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን የሚኖራቸውን ድንበርም ጭምር ያካተተ ነው። የኢኮኖሚ እቅዱ ዋና ሐሳብ በቀጣዮቹ ዐስር ዓመታት ውስጥ ለአንድ ሚሊዮን ፍልስጥኤማውን የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የፍልጥኤምን ጠቅላላ አገራዊ ምርት በሦስት እጥፍ የሚያሳድግ የተባለለትን የ50 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ያካተተ ነው ተብሏል። ይህ ገንዘብ በዕርዳታና በዝቅተኛ ወለድ በሚመለስ ብድር የሚገኝ እንደሆነም በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ከተበተነው የእቅዱ ከፊል ቅጅ መረዳት እንደሚቻል ዘ-ጋርድያን ዘግቧል። በፖለቲካዊ ዕቅዱ ከተካተቱ ነጥቦች ውስጥ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፤

-ኢየሩሳሌም ያልተከፋፈለች የእስራኤል ዋና ከተማ ትሆናለች፤ የፍልስጥኤም ዋና ከተማ ከኢየሩሳሌም ምሥራቅና ሰሜን ዳርቻ ላይ ይሆናል።

-በእስራኤል ሰፈራ የተወረረው የፍልስጥኤም ምዕራባዊ ድርቻ (West bank) ምድር በሙሉ የእስራኤል ግዛት ይሆናል። ይህን ከምዕራቡ ዳርቻ ለሚወሰደው የፍልስጥኤም ምድር ማካካሻ ይሆንና እስራኤልን ከግብጽ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ ከሚገኘው የእስራኤል መሬት ተቆርሶ ለፍልስጥኤም ይሰጣል። ይህ ለፍልስጥኤም የሚሰጥ ምድር ለመኖሪያና ለእርሻ ሥራዎች እና የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎች ይገነቡበታል የተባሉ ኹለት ቦታዎችን ይይዛል።

-ምዕራባዊው ዳርቻ፣ ጋዛ ሰርጥና አዲሶቹን የፍልስጥኤም ምድሮች በፈጣን የባቡር መስመር ይገናኛሉ።

-የዮርዳኖስ ሸለቆ የሚባለው የፍልስጥኤሙ ምዕራባዊው ዳርቻ አካል የእስራኤል ግዛት ይሆናል።

-ፍልስጥኤም ምንም ዓይነት የታጠቀ ወታደራዊ ኃይል አይኖራትም። ሃማስና ሌሎች በጋዛ ሰርጥ ያሉ ታጣቂዎች ሁሉ ትጥቃቸውን ይፈታሉ።

-የአካባቢው የአየርና የባህር እንቅስቃሴ በሙሉ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ይሆናል።

-ፍልስጥኤም ያለ እስራኤል ይሁንታ የማንኛውም ዓለም አቀፍ ድርጅት አባል አትሆንም።

-ፍልስጥኤም ማንኛውንም እስራኤላዊና አሜሪካዊ ዜጋ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መክሰስም ሆነ በኢንተርፖል አማካኝነት ማሳደድ አትችልም።

-እስራኤል የትኛውንም የፍልስጥኤም ምድር ወታደራዊ ጠቀሜታ እንዳለው ካመነችበት ልትቆጣጠረው ትችላለች።

የትራምፕ እቅድ ፍልስጥኤም አደገኛ ቅርቃር ውስጥ እንድትገባ የሚያደርግ መሆኑን ከዚህ መረዳት ይቻላል። የአፍሪካ ኅብረት በ33ኛው የመሪዎች ስብሰባው ላይ ከፍልስጥኤም ተወካይ የቀረበለትን ጥሪ ተከትሎ፣ ለፍልስጥኤም አጋርነቱን የሚያሳይ አቋም የያዘ መስሏል። ታዲያ በዚህ ግርግር ያለ ዕርዳታ መኖር የማይችሉ አገራትን ጠቅልሎ የያዘው የአፍሪካ ኅብረት ለፍልስጥኤም ሊያደርገው የሚችለው ምን ነገር የኖር የሆን? ወደየአገራቸው ሲመለሱ በተናጠል ለምዕራባውያኑ ተጽዕኖ በመንበርከክ የሚታወቁት ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች አሜሪካና እስራኤልን በመቃወም አቋም ይይዛሉ ተብሎ የሚጠበቀው አንዴት ነው?

የእስራኤል ሰፈራዎች የተመሠረቱባቸው ቦታዎች ወደ እስራኤል ግዛት ይጠቃለላሉ የሚለው እቅድ ምን ያህል አደገኛ መሆኑን ለመረዳት ስለ ሰፈራዎቹ መረጃዎችን ማግኘት ግድ ይላል። ፍልስጥኤማውያን በምዕራባውያን በተለይም በአሜሪካ የተደገሱ የሰላም ስምምነቶች ያስገኙላቸው ጥቅሞች ኢምንት መሆናቸውን ያውቃሉ። የኦስሎው የሰላም ስምምነትና ካምፕ ዴቪድ ስብሰባዎች ለፍልስጥኤም ጥቅምን ከማስገኘት ይልቅ ‹ኢንቲፋዳ› የሚባለውን ታላቅ አመጽ የቀሰቀሱ አሳማሚ ሁኔታዎችን እንደወለዱ ፍልስጥኤማውያን አይዘነጉትም።

እስራኤል ሕገ-ወጥ ሰፈራዎቹን የጀመረችው በዓረቦችና በእስራኤል መካከል በ1967 (እ.ኤ.አ.) የተካሄደውን የስድስቱ ቀናት ጦርነት ተከትሎ ሲሆን በዚህ ጦርነት ድል ያደረገችው እስራኤል ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ምዕራባዊውን ዳርቻ ከዮርዳኖስ፣ ከሲናይ እስከ ስዊዝ ካናል ያለውን ቦታ እና ጋዛን ከግብጽ፣ የጎላንን ከፍተኛ ቦታዎች ከሶርያ አስለቅቃ በወታደራዊ ኃይሏ ቁጥጥሯ ስር አውላዋለች። ይህ ወታደራዊ ቁጥጥር ለዓመታት ቀጥሎ ከ1972 ጀምሮ ሰፈራ እየተካሄደበት የአይሁዳውያን ሲቪሎች መኖሪያ መሆን ጀመረ። በ1972 ብቻ እስራኤል በምዕራባዊው ዳርቻ 1182፣ በጋዛ ሰርጥ 700፣ በምሥራቅ ኢየሩሳሌም 8649፣ በጎላን 77 ሰፋሪዎችን አስፍራለች። በ1972 ምዕራባዊው ዳርቻ ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎችን ማስፈር ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያው ከተማ አከል የሆነ ትልቅ የሰፈራ መንደር ተቋቁሟል።

ከራሱ ከእስራኤል መንግሥት ማእከላዊ ስታትስቲክስ ቢሮ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ እስከ 2018 ባለው ጊዜ ውስጥ የእስራኤል መንግሥት እና እስራኤላውያን በተናጠል (እንደ ግለሰብ ወይም ቤተሰብ) ወረራ እያካሄዱ ሰፈራ የመሰረቱባቸው ቦታዎች ብዛት ከ130 በላይ ደርሷል። ከእነዚህ ውስጥ ዐስራ ስምንቱ በእያንዳንዳቸው ከአምስት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎች የሚገኙባቸው ናቸው። በእነዚህ ሰፈራዎች የሚገኙ ሕገወጥ ሰፋሪዎች ብዛት ወደ አንድ ሚሊዮን የተጠጋ ሲሆን፤ የፍልስጥኤም ዋና ከተማ የምትባለው ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ወደ ግማሽ ሚሊዮን፣ ሞደኒ ኢሌት (ላይኛው ኢሌት) ከ73 ሺሕ በላይ፣ ቢታር ኢሌት (ታችኛው ኢሌት) ከ50 ሺሕ በላይ፣ ማላ-አድሙም ወደ 40 ሺሕ እና አሪያል ከ20 ሺሕ በላይ በሚደርሱ ሰፋሪዎች በመወረር ትልልቅ ሕገ-ወጥ ሰፈራዎች እንደሚገኙባቸው ይታወቃል። የቀሩት ሰፈራዎች ደግሞ ከመቶዎች እስከ አምስት ሺሕ የሚደርሱ ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎችን ይዘዋል። ‹ምሾር አዱም› የተባለው ቦታ ደግሞ ለኢንዱስትሪያል ፓርክ ተብሎ ከሦስት የፍልስጥኤም ወረዳዎች በተነጠቀ መሬት ላይ የተሠራ ሲሆን፣ በዚህ ዘመን ከሦስት መቶ በላይ ኢንዱስትሪዎችና የቢዝነስ ተቋማት ሥራ ጀምረውበታል።

የሰፋሪዎች ቁጥር በእስራኤል ባለሥልጣናት ይፋ ከተደረጉባቸው ሰፈራዎች በተጨማሪ ወታደራዊ ጣቢያዎች ተብለው የተከለሉና በተለየ ምክንያት የያዙት ሲቪል ሰፈሪ ብዛት በግልጽ እንዳይታወቅ የተደረጉ ስድስት ሰፋራዎች አሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ በምዕራባዊው ዳርቻ በግል የተነሳሰሱ እስራኤላዊ ቤተሰቦችና ግለሰቦች፣ በቡድን እየተደራጁ፣ ያሰኛቸውን የፍልስጥኤማውያንን መሬት እየወረሩ የመሰረቷቸው በርካታ የመኖሪያ ቦታዎች አሉ። ‘Out Post Settlements’ በመባል የሚታወቁት እነዚህ ሰፈራዎች ያለ እስራኤል መንግሥት ዕውቅና የተመሰረቱና ነዋሪዎቻቸው በእስራኤል ማእከላዊ ስታትስቲክስ ጽሕፈት ቤት ቆጠራ ውስጥ ያልተካተቱ (ያልተመዘገቡ) በመሆናው ስንት አይሁዳውያንን አቅፈው እንደያዙ አይታወቅም። እነዚህ ሰፈራዎች በመላ ምዕራባዊ ዳርቻ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ እና ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የተንሰራፉ በመሆናቸው፣ ብዛታቸው የእስራኤል መንግሥት ከመሰረታቸውና እውቅና ከሰጣቸው የሰፈራ መንደሮችና ከተሞች ብዛት ጋር የሚወዳደር እየሆነ ነው።

የትራምፕ የሰላምና የብልጽግና እቅድ እነዚህ ሁሉ ሰፈራዎች የሚገኙበትም የፍልስጥኤም ምድር ነው በእስራኤል እንዲወረሱና በምትካቸው በግብጽ አዋሳኝ ድንበር ላይ ከሚገኘው የእስራኤል መሬት ለፍልስጥኤም እንዲሰጥ የሚፈልገው። ዘ-ጋርድያን ይህ በግብጽ ወሰን ላይ የሚገኝ ቦታ በጣም በረሃማና አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጿል። ፍልስጥኤማውያን ከዮርዳኖስ ወንዝ በሰፊው የሚጠቀሙበትንና 80 ሺሕ ሄክታር መሬት በመስኖ የሚያለሙበትን የዬርዳኖስ ሸለቆ ተወስዶባቸው በግልጽ አዋሳኝ በሚገኘው በረሃማ ቦታ የእርሻ ሥራ ያካሂዳሉ ብሎ እቅድ ማውጣት ምን ማለት ይሆን?

ሁልጊዜም ሰፈራዎች የሚካሄዱት የሰላም ድርድሮች እየተካሄዱና በስምምነትም ያለ ስምምነትም እየተበተኑ ነው። የፍልስጥኤማውያን ጠበቃ የሆኑት ሃማስና ፋታሕ በየፊናቸው፣ ሰፈራውን ቢቃወሙም የእስራኤል ሰፈራ ሊገታ አልቻለም። በድርድር፣ በሰላማዊ ዓመጽ፣ ኃይልን በቀላቀለ አመጽና ጥቃት በመፈጸምም ጭምር ፍልስጥኤማውያን መሬታቸውን ነጻ ለማድረግና ሰፈራውን ለመግታት ሞክረዋል። በእነዚህ ጊዜያት ፋታሕ አልፎ አልፎ መሣሪያ የተቀላቀለበት ተቃውሞ ቢያካሂድም፣ በአብዛኛው ግን በድርድርና የስምምነት ፊርማ ለማግኘት የመሞከር መንገድ ሲከተል ቆይቷል። በተቃራኒው ሃማስ ደግሞ በአብዛኛው ጊዜ ኃይልን በቀላቀለ ዓመጽና የጦር መሣሪያ በታከለበት ግብግብ ላይ ያተኮረ ተቃውሞውን አብዝቶ አካሂዷል።

ፍልስጥኤማውን ከሰላም ስምምነቶችና ኃይልን ከቀላቀለ አመጽ የትኛው እንደሚያዋጣቸው ለመወሰን ተቸግረው፣ እየተወዛገቡና እየተከፋፈሉ ነው የሚኖሩት። የሃማስ አመጽ ጋዛ ሰርጥን ከሰፈራ ነጻ ማድረጉ የኃይል አመጽን ጠቃሚነት ሲያሳያቸው፣ እስራኤል ጋዛ ሰርጥን ደጋግማ በጦር ኃይል ማጥቃቷና ጋዛ ሰርጥን ከአገር ይልቅ እስር ቤት በሚያደርግ ከበባና ማዕቀብ ስር ማስገባቷ ከኃያሏ እስራኤል ጋር ቀጣይነት ያለው ግብግብ አደገኛ መሆኑን ይነግራቸዋል።

ኃያላኑ መንግሥታት ጋዛን ነጻ ያወጣውን ሃማስን በአሸባሪነት ፈርጀው አበክረው ይኮንኑታል። ነገር ግን በሰላም ያምናል የሚባለው ፋታሕ የሚያስተዳድረው የምዕራቡ ዳርቻ፣ ቀስ በቀስ በእስራኤል ሲወረር የሚያሰሙት ተቃውሞ ጠንካራ ነው ማለት ይከብዳል። በሃማስ ላይ የማዕቀብ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጠንካራ የሆኑትን ያህል መሬት እየወረረች ሰፈራ በምትገነባው በእሰራኤል ላይ ትንሽ ማዕቀብ ስለ መጣል ሲታሰብ፣ ተባባሪ ለመሆን ፈቃደኞች አይደሉም። አክራሪ አይሁዳውያን ፍልስጥኤም የሚባል አገር እና ፍልስጥኤማዊ የሚባል ሕዝብ በአካባቢው እንዲኖር ፈጽሞ እንደማይፈልጉት ሁሉ፣ ሃማስም ለእስራኤልና ለአይሁዳውያን እውቅና የማይሰጥ ድርጅት ነው።

አክራሪ አይሁዳውያን ማንኛውንም ፍልስጥኤማዊ ብቻ ሳይሆን ከፍልስጥኤማውያን ጋር በሰላም ለመኖር የሚሹ አይሁዳውያንንም ጭምር እንደ ጠላት እንደሚቆጥሩና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለመግደል እንደሚፈልጉት ሁሉ፣ ሃማስም ማንኛውንም እስራኤላዊ ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን ያካሂዳል። ቤት ሠራሽ ሮኬቶችን ወዳሰኘው ቦታ የሚተኩሰውና ምቹ በሆነለት ቦታ ሁሉ ከተኩስ እስከ አጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ተጠቅሞ ጥቃት የሚሰነዝረው ማንኛውንም እስራኤላዊ በጠላትነት ስለፈረጀ ነው።

የሃማስ ዘመቻዎች ለአክራሪ አይሁዳውን ብቻ ሳይሆን ለእስራኤል መንግሥትም የራስ ምታት ሆነዋል። በርካታ የእስራኤል ፓርላማ አባላት እስራኤላውያኑን በጋዛ ማስፈር ዜጎችን ለእልቂት እንደማዘጋጀት አድርገው በመቁጠራቸው፣ በተደጋጋሚ በምክር ቤቱ ስብሰባዎች በጋዛ የሰፈሩ አይሁዳውያን በሙሉ ከጋዛ እንዲወጡ ውሳኔ ላይ አንዲደርሱ አስገድዷቸዋል። ይህን ውሳኔ ተከትሎ ነሐሴ 14/2005 እኩለ ሌሊት ላይ የተጀመረው ከጋዛ የመውጣት ዘመቻ መስከረም 12/2005 ላይ ተጠናቅቋል። የእስራኤል መንግሥት ዜጎቹን ከጋዛ ሲያወጣ በኃይል በተቆጣጠራቸው መሬቶች ላይ የተገነቡትን 21 የሰፈራ መንደሮች በቡልዶዘሮች አፈራርሷቸዋል።

በጋዛ የእስራኤል ሰፈራዎች የቀጠሉት ለ38 ዓመታት ብቻ እስከ 2004 ነው። እስራኤል በ38 ዓመታት የጋዛ ሰርጥ ወታደራዊ ቆይታዋ ከ7826 (እንደ አንዳንድ ምንጮች ከ8500) በላይ ሰፋሪዎችን ማስፈር አልቻለችም። ሕገ-ወጡ ሰፈራና ሕገ-ወጥ መንደር ምስረታው እስከ 2004 ባሉት 38 ዓመታት ውስጥ በምዕራባዊው ዳርቻ 235,263፣ በምሥራቅ እየሩሳሌም 176,566 እስራኤላውንን አስፍሮ ነበረ። ስለዚህ ቀድሞውንም ቢሆን እንደ ምዕራባዊው ዳርቻ በተጋነነ መጠን ሰፈራ ያልተካሄደበት ጋዛ ሰርጥም (Gaza Strip) ከ2005 ጀምሮ ከአይሁዳዊ ሰፋሪዎች ነጻ ሆኗል።

ሄለን ኮባን በ1984 ባሳተመችው The Palestinian Liberation Organization: People, Power, and Politics.’ በተባለ መጽሐፏ የኖቤል ተሸላሚው ያሲር አራፋት “….ፍልስጥኤማውያንን መኖሪያ የሌላቸው ነዋሪዎች ያደረገ ውርስ ትተውላቸው አልፈዋል…” ስትል ባስቀመጠችው ሃቅ፣ የፍልስጥኤም በተለይም የምዕራባዊው ዳርቻ ሁኔታ በትክክል ተገልጿል ማለት ይቻላል። ሄለን ኮባን፣ ያሲር አራፋት የኦስሎ ስምምነትን ከእስራኤል ጋር ከተፈራሙበት በኋላ ያሲር አራፋት በሚያስተዳድሩት በምዕራቡ ዳርቻ የሚካሄደው የመሬት ወረራ በእጥፍ ማደጉን ገልጻ፣ አራፋት ወረራውን ለመግታት የሚስችል ምንም ዓይነት ስትራቴጅ ያልነደፉ ከመሆናቸውም በላይ የመሬት ወረራውን የሚቃወሙ ፍልስጥኤማውያንን በማውገዝ፣ ተቃውሞ በሚያካሂዱ ፍልስጥኤማውያን ላይ በታጣቂዎች አማካኝነት ከረር ያለ እርምጃ በማስወሰድ አሳዛኝ ሥራ ይሠሩ እንደነበረ ገልጻለች። ይህ የሄለን ኮባን ትንታኔ የዘመኑ የፍልስጥኤም መሪዎች የሚጠብቃቸውን ፈተና ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።

ከዚህ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ትግል ወደየት ያመራ ይሆን? የአፍሪካ ኅብረትና የአፍሪካ መንግሥታትስ ለፍልስጥኤማውያን መብት መከበርና ለፍልስጥኤም አገራዊ ሕልውና ቀጣይነት የሚጠቅም ምን ፋይዳ ያለው ነገር ጠብ ያደርጉ ይሆን?
ግዛቸው አበበ በኢሜይል አድራሻቸው
gizachewabe@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com