የፖለቲካ አመራሮች ዜግነት እና የፖለቲካ ምህዳሩ

Views: 738

ሐሰን ሞአሊን የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር የውጭ ጉዳይና የአዲስ አበባ ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ ሲሆኑ የፓርቲው ማዕከላዊ እና አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ ደገሀቡር ከተማ የተወለዱት ሐሰን ኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥት ሲያቋቁም በወጣትነታቸው የከተማው አስተዳደር ዋና ፀሐፊ ነበሩ፡፡ ኦብነግ ለሦስት ዓመታት ክልሉን ካስተዳደረ በኋላ በህውኀት በጠላትነት እንደፈተፈረጀ የሚገልፁት ሐሰን የያኔ አጋሮቻቸው እንኳን ጠመንጃ አንስተው ሲወጡ እርሳቸው ግን ያንን እንዳላደረጉ ያስረዳሉ፡፡ በዚያን ጊዜ መሣሪያ ያነሱት እና ያላነሱትን ሳይለይ ህወኀት ጦርነት እንደከፈተባቸውም ያስታውሳሉ፡፡ በአካባቢው ባሉ ከተሞች ውስጥ እንዲገደሉ ስማቸው ከተላለፈ ዐስር ሰዎች ውስጥ ስማቸው እንደነበርም ጠቅሰው ከ20 ዓመታት በኋላ እንኳን እነዚያ ዘጠኝ ሰዎች የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ ያስረዳሉ፡፡

እርሳቸው የተረፉትም የአጎታቸው ልጅ ቤት ሔደው አምሽተው ሊመለሱ ሲሉ አንዲት ሴት መጥታ ቤትህ ተከቦ ስለነበር አትሒድ ካለቻቸው በኋላ አምስት ዘመዶቻቸው በእግር ከከተማው እንዳስወጧቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚያም በእህታቸው ባል መኪና ጅግጅጋ እንደገቡ፤ ብሎም ድሬዳዋ ስድስት ወር ተደብቀው እንደኖሩ ያስረዳሉ፡፡ ከድሬዳዋ በኋላ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ተደብቀው ከኖሩ በኋላ በኢትዮጵያ ፓስፖርት ወደ ውጭ አገር እንደወጡ ይገልጻሉ፡፡

የዛሬ ኹለት ዓመት አቅራቢያ በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረው የህወኀት የበላይነት ማክተሙን በሚገልጽ ሁኔታ የኦህዴድ እና ብአዴን ቅንጅት የሆነው ቡድን ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ በርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ወደ አገር ውስጥ እንደገቡ ይታወቃል፡፡ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እንዲሁም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና መሪዎች ሁሉንም ክልሎች በሚወክል መልኩ ወደ አገር ገብተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች በጋለ ስሜትና በደማቅ አቀባበል ለአገራቸው አፈር ከበቁ የከረሙ ሲሆን አሁን ባለው እውነታ ምርጫው የቀረው አምስት ወራት ብቻ መሆኑ ደግሞ እስከ አሁን ትኩረት ያልተሰጣቸው ጉዳዮች ብርሃን እንዲያርፍባቸው እያደረገ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ጉዳዮች አንዱ የእነዚህ የፖለቲካ መሪዎች የዜግነት ጉዳይ ነው፡፡

ከአገር ውጪ ያሉ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር እንዲገቡ የተደረገውን ጥሪ ተከትሎ የኦብነግ አመራሮች ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን ሐሰንም ከተመለሱት አመራሮች አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በዴንማርክ 24 ዓመታት የኖሩ ሲሆን በዚህ ጊዜም ዜግነታቸውን ቀይረው ነበር፡፡ እርሳቸውም ብቻ ሳይሆኑ የፓርቲው አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ግማሽ በግማሽ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው እንደነበሩም አክለው ያስረዳሉ፡፡ እርሳቸው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ፓስፖርታቸውን እንደመለሱ እና የውጭ ዜግነት እንደሌላቸውም አክለው ገልፀዋል፡፡

ፖለቲካ ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎም ይሁን በሌላ ምክንያት ከአገራቸው ተሰደው የከረሙት የተለያዩ የፖለቲካ ፖርቲዎች መሪዎች እና የአመራር አባላት በተለያየ ምክንያት የሌሎች አገሮች ፓስፖርት ይዘዋል ወይም ደግሞ ዜግነታቸውን ቀይረዋል፡፡ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆችም ሆኑ በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሱማሌ እና ሌሎችም ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የብሔር ፓርቲዎች አመራሮች ይህ ሁኔታ እንደሚነካቸው እየተዘገበ ይገኛል፡፡

ለውጡ ከመምጣቱ በፊት የሌላ አገር ፓስፖርት መያዝም ሆነ ዜግነትን መቀየር የዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ጭምር በመጠቀም ሲያድናቸው ከነበረው የህወኀት መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥት ለመሸሸግ ከማገዙም በተጨማሪ የጊዜውን የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቃወሙ አቋሞችን ወይም ሰነዶችን በኃያላን መንግሥታት ለማፀደቅ የሚረዳ ነበር፡፡

በመሆኑም እነዚህ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች እና አመራር አባላት ይህንን ከለላ በመጠቀም በዓለም ዙሪያ ዞረው በውጪው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ከመቀስቀስ እስከ ጦር ማደራጀት የሚደርስ ሥራ ሢሰሩ ቆይተዋል፡፡ ይህ ሥራም ለውጡ እውን እንዲሆን እና ከኢሕአዴግ ውስጥ የተነሳው የተቃውሞ ድምፅ እየጠነከረ እንዲመጣ ብሎም መንግሥት ላይ የሚደርሰው ጫና እንዲጠነክር በማድረግ ለለውጡ መከሰት ምቹ ሁኔታ ከፈጠሩ እውነታዎች መካከል ነው፡፡

ይህን አስመልክቶ ሐሰን ሲገልጹ የሌላ አገር ዜግነት መያዛቸው እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው ከሌሎች የተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ለመሥራት እንዲችሉ እና ሕዝብ እንዲቀሰቅሱ እድሉን አስፍቶላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከግንቦት ሰባት እና አርበኞች ጋር ለመሥራት፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ሌሎችም አገሮች ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመነጋገር እና አብሮ ለመሥራት የቻልነው ዜግነቱ ለእንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረልን ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አሉ ሐሰን በውጭ አገራት በነበረን ቆይታ ብዙዎቻችን በትምህርት እራሳችንን አሳድገናል፤ ዴሞክራሲ የሚሠራበት ስርዓት ምን እንደሚመስል ልምድ ወስደናል ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር እንዴት መሥራት እንዳለብን አውቀናል ብለዋል፡፡ ይህ ልምዳችን ደግሞ ለአገራችን አስፈላጊ ነው ባይ ናቸው፡፡

በህወኀት በሚመራው ኢሕአዴግ ጊዜ የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ይመራ የነበረው ከውጭ አገራት እንደነበር የሚከራከሩ ፖለቲከኞች የመጡት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችማሳያ ሆነዋቸዋል፡፡ ይህም በመሆኑ አመራሩ በየእለት ኑሮው የሕዝቡን ኑሮ ሳይካፈል እና አብሮ ሳያሳልፍ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ይሰጥ ስለነበር አንዳንድ ጊዜ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የማይሔድ ይሆን እንደነበር የአርበኞች ግንቦት 7 ሕዝብ ግንኙነት የነበሩት ኤፍሬም ማዴቦ ያስረዳሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ሕዝብ ማስተባበር ላይ፣ አገር ላይ የሚከሰቱ ነገሮችን በመከታተል፣ የገዢው ፓርቲ አመራሮችን በማወቅ ላይ በዓይን ማየት ከሌላ አገር ሆኖ እንደመስማት የሚሆን አይደለም፡፡ አሠራሮችን ለመገንዘብ እና ስትራቴጂ ለመንደፍ ከሕዝብ ጎን በአገር መሆኑ ብዙ አዲስ ነገር እንዳስተማራቸው ይገልጻሉ፡፡

የኢዜማ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ግርማ ሰይፉ ደግሞ ከዚህ ለየት ያለ አመለካከት ነው ያላቸው፡፡ ለእርሳቸው ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ የሚመራው ከውጭ ነበር፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሰዷል የሚሉት አመለካከቶች የተሳሳቱ ናቸው፡፡ በእርግጥ ይላሉ ግርማ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ምህዳር እየጠበበ በሔደ ቁጥር ሰዎች ስደትን እና የመሣሪያ ትግልን እንደአማራጭ ይወስዳሉ፡፡ አገር ውስጥ የቀሩት ደግሞ እየታፈሱ ይታሰራሉ ያሉት ግርማ ይህ ሁኔታ በአገር ወስጥ ያለውን ድምፅ በመቀነስ የማይታሰረው ከአገር ውጭ ያለው ሰው ድምፅ እንዲሰማ አድርጓል ባይ ናቸው፡፡

የእራሳቸውን ፓርቲ ኢዜማን እንደ ምሳሌነት በማንሳትም ከ23 አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ከውጭ የመጣው አንድ ሰው ብቻ ነው ሲሉ ከውጭ አገር የመጡ ፖለቲከኞች በቁጥርም ብዛት ያላቸው እንዳልሆኑ ይሞግታሉ፡፡ “ነገር ግን ፖለቲካ አመራር ላይ ነበሩ ወይም የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዲያስፖራው ነው የሚመራው ማለት ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከውጭ ነበር የሚመራው የሚለው አስተሳሰብ ትክክል ቢሆን ኖሮ አሁን ሁሉም ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ በጣም የተደራጀ አመራር የሚሰጥ የዲያስፖራ የፖለቲካ ቡድን ታገኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የለም፡፡”ሲሉ ሀሳባቸውን ያካፈሉን ግርማ ከለውጡ በኋላ በአገር ውስጥ ገብተው ባላቸው የፖለቲካ ተሳትፎ የፖለቲካውን ሥነ ምህዳር ቀይረውታል ለማለት ያስቸግራል ይላሉ፡፡ ወደ አገር ውስጥ በመምጣታቸው የተቀየረው ነገር የውጪው ጩኸት መቀነሱ ነው ያሉት ግርማ ውጤቱ የሚታየው ግን ወደ ፊት ነው ባይ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን ግርማ ከውጭ የመጡት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በቁጥርም አናሳ በተጽዖኖም ምህዳሩን ያልቀየሩ ናቸው ቢሉም የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የዳውድ ኢብሳ፣ ከማል ገልቹ፣ ጃዋር መሐመድ፣ እስክንድር ነጋ እና ሙስጠፌ ኡመር ዓይነት ሰዎች በፖለቲካው ላይ መካተት ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የኦሮሞ ብሔርተኝነት ላይ ዳውድ ኢብሳ እና ጃዋር መሐመድ ያሳደሩት ተጽዖኖ ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የፓርቲያቸው ብቻ ሳይሆን የዜግነት ፖለቲካ ምልክት ተደርገው የሚወሰዱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም አገሪቷ ውስጥ ካሉ ተጽዖኖ ፈጣሪ ጥቂት ፖለቲከኞች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ የእስክንድር ነጋ የአዲስ አበባ እንቅስቃሴም መንግሥትን እያስጨነቀው እንደሚገኝ እና አማራጭ የፖለቲካ አመለካከት እንደፈጠረ የሚታይ ነው፡፡ ሙስጠፌ ደግሞ ተራማጅ የክልል አመራር በመሆናቸው በመላው ኢትዮጵያ ተወዳጅነትን ያተረፉና ለሌሎችም የፖለቲካ መሪዎች በአርአያነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ ከላይ እንደተመለከትነው የኦብነግ ግማሽ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ አባላት እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ያሉ ፓርቲዎች ከውጭ የመጡ ሰዎች በአመራር ላይ እንደሚገኙባቸው ሲታሰብ ቁጥራቸውም ትንሽ የሚባል እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡

እነዚህ ሰዎች ከአገር ውጭ ቢሆኑ ፖለቲካው ምንም አይቀየርም ወይም በመግባታቸው ምንም አልተቀየረም ማለት ከባድ ነው፡፡ ለተወሰኑ ቡድኖች በጥሩ፣ ለሌሎች ደግሞ በመጥፎም ቢሆን ሰዎቹ ያላቸው ተጽዖኖ ግን የሚካድ አይደለም፡፡ በተለያዩ ፅንፎች የቆሙ አመለካከቶች እንዳሏቸው የሚታወቁት እነዚህ መሪዎች የፖለቲካ ምህዳሩ ላይ የሚንፀባረቁትን የሃሳቦች ቡፌ የሚወክሉ ናቸው፡፡ የእነሱ ከፖለቲካ መወገድ ምህዳሩ ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚኖረው እሙን ነው፡፡

ግርማ ሰይፉ ያነሱት ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል ነጥብ ቢኖር የኢትዮጵያ ፖለቲካ መመራት ያለበት በኢትዮጵያዊያን ነው የሚለው ነው፡፡ የውጭ አገር ዜጎች አገሪቷን እንዲመሩ ሊፈቀድ አይገባም፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮቹ የሌላ አገር ፓስፖርታቸውን መልሰዋል አልመለሱም በሚል እያንዳንዳቸው ላይ ያነጣጠረ ጥርጣሬ መፍጠር እና ሁሉንም እንደማሸማቀቂያ መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡ በመሆኑም የአገሪቷን ሕግ በጠበቀ መልኩ ሕጋዊነታቸውን አረጋግጦ የአገሪቷ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ማስቀጠሉ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com