የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከማላዊው አቻው ውድቀት ይማር!

Views: 390

ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ጫናዎች ስር ነው። ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነጻ እንደሆነ ቢነገርና ምርጫውም ነጻና ፍትሐዊ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም፣ አካሄዱ ግን ወደዛ እንዳልሆነና እንደማይመስል ያብራራሉ። ጠቅላይ ሚስትሩ በተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉትን ንግግርና የሰጡትንም ምላሽ፣ ይልቁንም ከምርጫ ጋር የሚገናኙ ነጥቦች አወዛጋቢ ከመሆናቸው ላይ ቦርዱ ላይ ተጽእኖ ሊኖር እንደሚችል ማሳያዎችም እንዳሉ ግዛቸው ያነሳሉ። ነገር ግን ቦርዱ በማላዊ የሆነውን ሁኔታ አጢኖ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሲሉ በማላዊ የሆነውን አብራርተዋል።

ምርጫ ቦርድ ከባድ ውሳኔ የሚሻ የምርጫ ሂደት እንደሚጠብቀው የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። ቦርዱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶባት በማታውቀው በኢትዮጵያችን፣ የተሻለ ዴሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ ለመሆን ተቃርቦ መጨረሻ ላይ በስርዓቱ አምባገነንነት የጨነገፈ (ምርጫ 1997) መራር ተሞክሮ ለቀመሰችው ለኢትዮጵያችን፣ ቁም ነገር ሠርቶ የሚወደስበት ወይም የቀድሞውን የምርጫ ቦርድ ሥራ ደግሞ ሠርቶ አንገቱን የሚደፋበት ጊዜ ከፊት ለፊቱ እየጠበቀው ነው።

በሕዝብ አመጽ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በኢትዮጵያ ትክክለኛና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበረ። የብርቱካና ሚደቅሳ የምርጫ ቦርዱ መሪ መደረግ በራሱ ምርጫው ነጻና ፍትኀዊ እንዲሆን ያለውን ፍላጎት ማሳያ ተደርጎ በመወሰዱም ተስፈው የጎላ ነበረ። ነገር ግን ለውጡ ውሎ አድሮ ከተስፋ ሰጪነት ወደ ዝርክርክ ትርምስ ውስጥ ገብቶ በተስፋ አስቆራጭ ገጠመኞች እየተሞላ ነው። የወቅቱ ሁኔታ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ይቅርና የአገሪቱን ሕልውናና የሕዝቦቿን ሰላም ማስከበሩን ፈተና ላይ የጣለ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ቀርበው የምርጫው ጉዳዮችን ስለ መወሰን የተናገሩት ነገር ግራ አጋቢና ጥንቃቄ የጎደለው ይመስላል። በአንድ በኩል ራሳቸውን ገለልተኛ አድርገው ስለ ምርጫ ቦርድ ውሳኔዎች ከመገናኛ ብዙኀን ከሕዝቡ ጋር እየሰሙ መሆኑን ገልጸው ሲያበቁ፣ በሌላ በኩል ግን ምርጫው ከነሐሴ 2012 እልፍ አይልም ብለው የውሳኔ አቅጣጫ የመሰለ ንግግር አሰምተዋል። ቀጣዩ ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን ሕዝብ ያልመረጠውን ፓርላማ የሥራ ዘመንና ይህ ፓርላማ የመሰረተውን መንግሥት ዕድሜ ቆጥሮ መወሰኑ ከ2008 እስከ 2010 የተካሄደው ሕዝባዊ ቁጣ ዓላማ ምን እንደሆነ እንደ መሳት ይቆጠራል።

በእርግጥ የመቀሌው ሕወሐትና በቀረው ኢትዮጵያ እንደተንሰራፋ ተደርጎ የሚነገረው የብልጽግና ቡድን፣ በየፊናቸው በሕዝብ እንደተመረጡና ሕዝብ ሥልጣን የሰጣቸው እስከ 2012 መጨረሻ ብቻ እንደሆነ አድርገው በመናገር ላይ ናቸው። እነዚህ ቡድኖች ሕዝብ አደራ ሰጠን የሚሉት በግንቦት 2007 በተካሄደው ምርጫ መቶ-በ-መቶ ያስደፈነን ሕዝብ ነው ለማለት ፈልገው ነው። በዚሁ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕወሐት የትግራይ ሕዝብ ድጋፍ ያለውና በትግራይ ሕዝብ የተመረጠ ቡድን ስለሆነ አብረን እንሠራለን ሲሉም ሰምተናል።

ይህ ደግሞ ‘የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ’ የሚለውን አባባል ከማስታወሱም በጨማሪ ሕወሐቶችና ብልጽግናዎች በምርጫ ወቅት በኢሕአዴግነት ዘመናቸው የለመዱትን ‘ተባብሮና ተረባርቦ ምርጫን የመቆጣጠር’ ሥራ አብረው ለመሥራትና አንዱ የሌላውን የምርጫ ውጤት ተቀብሎ አብሮ ለመዝለቅ እንደ መዶለት የሚቆጠር በነው። አዎ! ብልጽግናዎችም ሆኑ ሕወሐቶች ምርጫው ካልተካሄደ ሞተን እንገኛለን እያሉ ነው። በእርግጥ ብርቱካን ሚደቅሳ ሕዝብ በጥይቶች መካከል እየተሽሎከሎከ ምርጫ ይካሄድ አንልም ብለዋል። ይህ አባባል በመጭው ሐምሌ ይሁን ነሐሴ ወይም በመጭው አዲስ ዓመት መስከረም ይሁን ጥቅምት ሰላም ከሌለ ምርጫ አይካሄድም ማለታቸው ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። መሆን ያለበትም እንደዚህ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ምሽቱ ጨረቃ የሌለችበት ድቅድቅ ጨለማ ቢሆንም፣ መኪናችን መብራት ባይኖራትም በከፍተኛ ፍጥነት መንዳታችንን ቀጥለን የሚገጥመንን እናያለን ብለው እየነገሩን ነው።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ‘የምርጫ ቀን’ ብሎ የሚወስነው ዕለት በትክክል ምርጫና ምርጫ ብቻ የሚካሄድበት ዕለት መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለበት። ምርጫ ቦርድ በዚያ ዕለት የዋዜማ ሳምንታት ተወዳዳሪዎች ሁሉ ባሻቸው ቦታ ሄደው የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ መቻላቸውንና ሁሉም ተወዳዳሪዎች ደጋፊዎቻቸውን በተለያየ መንገድ እያገኙ ማወያየታቸውን እርግጠኛ መሆን አለበት። በዚያ የምርጫ ዕለት የዋዜማ ቀናት ውስጥ ምርጫ ማካሄጃ ቁሳቁሶች በሰው ሠራሽም ሆነ በተፈጥሯዊ እንቅፋቶች ሳይስተጓጎሉ መጓዝ እንደሚችሉም እርግጠኛ መሆን ይጠበቅበታል። ምርጫ ቦርድ በዚያ የምርጫ ዕለት በ40 ሺሕ የምርጫ ጣቢያዎቹ አንደኛ መራጩ ሕዝብ፣ ኹለተኛ የምርጫ ታዛቢወች፣ ሦስተኛ አስመራጮች ወዘተ በነጻነትና ያለ ምንም፣ ያለ ማንም ተጽዕኖና ማስፈራሪያ የየድርሻቸውን ኃላፊነትና ግዴታ መወጣት የሚችሉ መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለበት።

በዚያ ዕለት የምርጫው ሂደት በሙሉ፣ ከቅድመ ዝግጅቱ እስከ ድምጽ አሰጣጡና አስከ ቆጠራው ሰላማዊ ሆኖ መካሄድ ይችል ዘንድ የሚያስችል ጸጥታ እንዲሰፍን የሚያደርግ ገለልተኛ የጸጥታ ኃይል በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ሊሰማራ እንደሚችልም ምርጫ ቦርድ እርግጠኛ መሆን ይገባዋል። ምርጫ ቦርድ በሙሉ እርግጠኛነት ተገቢውን የምርጫ ዕለት ለመወሰን የግለሰቦችን ወይም የቡድኖችን ተጽዕኖ ሳይሆን በምድር ላይ የሚታየውን ነባራዊ ሃቅ መሰረት አድርጎ ውሳኔ መስጠት ይገባዋል።
ምርጫ ቦርድ ይህን ለማድረግ ከማእከላዊ አቻው ያልታሰበ ውደቀት ትምህርት ሊኮርጅ ይገባዋል። በእርግጥ ምርጫን እና ዴሞክራሲን በሚመለከት የኢትዮጵያና የማላዊ ልምድ የሰማይና የምድር ያህል የሚራራቅ ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ የግድ ቆራጥ፣ ገለልተኛነቱን የማያስደፍርና ከምርጫ ጋር የተያየዙ የኢትዮጵያ ሕጎችንና መመሪያዎችን ለመተግበር ጽኑ አቋም ያለው መሆን ይጠበቅበታል።

በ1964 ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ የወጣችው ማላዊ፣ በካሙዙ ባንዳ ፕሬዘዳንትነት ከ1966 እስከ 1994 ተመርታለች። ካሙዙ ባንዳ በቅኝ ግዛቱ ዘመንም ከእንግሊዟ ንግሥት ኤልዛቤት 2ኛ አገዛዝ ስር፣ መጀመሪያ የእንግሊዝ አይስላንድ ቀጥሎም ማላዊ የተባለች አገራቸውን ይመራል የሚባለው ፈረንጅ ሠራሽ ዲፋክቶ መንግሥት ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል። ካሙዙ ባንዳ በቅኝ ግዛትና በነጻት ዘመን ለ33 ዓመታት ሥልጣን ላይ ቆይተዋል።

በ1994 (ከዚህ ጀምሮ የተጠቀሰው የቀን አቆጣጠር በሙሉ የፈረንጆች ነው) በተካሄደው ምርጫ ካሙዙ ባንዳን ያሸነፉት ባኪሊ ሙሉዚ ኹለት ጊዜ በምርጫ በማሸነፍ እስከ 2004 የማላዊ ፕሬዘደንት ሆነዋል። በ2004 በተካሄደው ምርጫ ያሸነፉት ቢንጉ ዋ ሙተሪካ የተከታዩ ምርጫም አሸናፊ ሆነው በሞት ከሥልጣናቸው እስከተለዩበት እስከ 2012 የማላዊ ፕሬዘደንት ነበሩ። የቢንጉን ሞት ተከትሎ ምክትል ፕሬዘደንት የነበሩት ወይዘሮ ጆሲ ባንዳ፣ ከ2012 እስከ 2014 የማላዊ ሴት ፕሬዘደንት ሆነው አገልግለዋል። የ2014 ምርጫ ወደ ፕሬዘደንትነት ያመጣቸው ፒተር ሙተሪካ እስከዚህ ጊዜ ማላዊን መርተዋል።

ምርጫ በማካሄድ መሪዋን (ፕሬዘደንት) ለመቀያየር አዲስ ያልሆነችው ማላዊ፣ ከስድስት ወራት በፊት ግንቦት 21/2019 ያካሄደችውና ውጤቱን ያወጀችለት፣ በሥልጣን ላይ የቆዩትና በምርጫው አሸናፊ የተባሉት ፒተር ሙተሪካ ቃላ መሀላ የፈጸሙለት፣ ፒተር ሙተሪካ አገር ሊመሩ ቃል የገቡለት የምርጫ ውጤት ግን ከስድስት ወራት በላይ መጽናት አልቻለም። የዚህ ምርጫ ውጤት ተቃዋሚዎችን ከአሸናፊው ጋር እያነታረከና እያከራከረ እስከ ትናንቱ ማክሰኞ የካቲት 3/2020 ድረስ ዘልቋል። የማላዊ ምርጫ ኮሚሽን ምርጫውን በማጭበርበር ዋናው ተጠያቂ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎችና ምስክሮች በብዛት ቀርበዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የማላዊ ሕዝብ ጆሮውን በማላዊ መገኛና ብዙኀን ላይ ቀስሮ ከርሟል። የፒተር ሙተሪካ አሸናፊ መባል ሐሰተኛ መሆኑን የሚያስረዱ ምስክሮች እየቀረቡ የሚያካሄዷቸው የቀጥታ ስርጭት ምስክርነቶችን ማሰራጨት የመገናኛ ብዙኀኑ ዋነኛ ሥራ ሆኖ ነበር። ጉዳዩ ከሦስት ወራት በላይ ለዘለቀ ጊዜ በፍርድ ቤት ቢታይም፣ የፍርድ ሂደቱ በመገናኛ ብዙኀን በቀጥታ ይተላለፍ ስለነበረ ሕዝብ ሁሉንም ነገር በጽሞና እንዲከታል አስችሎታል።

በእነዚህ ጊዜያት በየቤቱ፣ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በመዝናኛ ስፍራዎች፣ በስራ ቦታዎች ወዘተ.. ብቻ ሳይሆን መጓጓዣዎች ውስጥ የተሳፈሩ ሰዎችም መገናኛ ብዙኀኑን በተለይም ሬዲዮዎችን መከታተል ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ሆኖ ነበር። በየቦታው ሰዎች ሰብሰብ ብለው ሬዲዮ ሲሰሙ ማየትም የተለመደ ነገር ሆኖ ነበረ።
ከብዙ ምርጫ ጣቢያዎች የሚመጡ የምርጫውን መጭበርበር የሚያሳዩ የተባሉ፣ በመረጃዎች የተደገፉ ክርክሮችን ሲያጤን የቆየው የአገሪቱ ፍርድ ቤት ማክሰኞ የካቲት 3/2020 በሰጠው ብያኔ፣ ከስድስት ወራት በፊት የተካሄደው ምርጫ ውጤት ተሰርዞ ከሦስት ወራት በኋላ ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል። ጉዳዩን ሲመለከተው የቆየው ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ ሄሊ ፖታኒ “…ግንቦት 21/2019 በተካሄደው ምርጫ ሙተሪካ አላሸነፉም። መጠነ ሰፊ የማጭበርበር ተግባራት መፈጸማቸውን አረጋግጠናል። የምርጫውን ውጤት ውድቅ አድርገናል…” ሲሉ የፍርድ ቤቱን ውሳኔው አሳውቀዋል። ይህን ውሳኔ ተከትሎ ማላዊ በ151 ቀናት ውስጥ ሌላ ምርጫ እንደምታካሂድ ታውቋል። ይህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ፒተር ሙተሪካ በ38.6% ድምጽ አሸነፉ መባሉን ተከትሎ ሲካሄዱ የነበሩ የተቃውሞ እንቅስቃሴወችንና ሞቅ በረድ አያለ ሲከሰት የነበረውን የአደገኛ አመጽ አዝማሚያ ያበርደዋል ተብሎ ተገምቷል። የማላዊን ሰላምና መረጋጋት በቋፍ ላይ ሊያኖረው የዳዳው አመጽ መቀዝቀዙ ለማላዊ ዜጎች ትልቅ እፎይታ ነው።

የ2019ኙ የማላዊ አገሪቱ ከእግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ወጥታ ካካሄደቻቸው ምርጫወች ውስጥ ፍርድ ቤት የደረሰ ሙግት የገጠመው የመጀመሪያው ምርጫ ሆኗል። ይህ ለስድስት ወራት የዘለቀ የምርጫ ክርክርና የፍርድ ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ ስለ ማላዊ ብዙ የሚነግረን ነገረ አለ። የማላዊ የፍትሕ ስርዓት፣ የማላዊ የመገናና ብዙሐን አሰራርና በጠቅላላው የማላዊ ዲሞክራሲ በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆኑን መረዳት ይቻላል። በእርግጠኝነት የማላዊ ጦር ለሕገ-መንግሥታዊ ስርዓት፣ ለአገርና ለሕዝብ መቆም ማለት ምን ማለት መሆኑን ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ፣ በጣም ትልቅና አኩሪ የሆነ ሥራ ሠርቷል።

እርግጥ ነው ማላዊ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ሰላምና መረጋጋት ያላት አገር ናት። ከማላዊ የነጻነት ዘመናት ውስጥ ፈታኝና አስቸጋሪ ጉዳዮች ከመንግሥት በኩል ሲጋረጡ የነበሩት በካሙዙ ባንዳ ዘመን ነበረ።

በመጀመሪያ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ፣ ከዚያም ከካሙዙ ባንዳ አምባገነናዊ ቀንበር ነጻ ወጥታ በጥሩ ጎዳና ላይ ስትጓዝ የኖረችው ማላዊ በ2019 ራሷን መንታ መንገድ ላይ አግኝታው ነበር። ነገር ግን የዳበረ ልምዷ ሁሉም ወገኖች ቆም ብለው ነገሮችን ያዩ ዘንድ ስላበቃቻው የካቲት 3/2020 የመፍትሔው እርምጃ አንድ ተብሎ ተጀምሯል።

በኢትዮጵያችን ተካሄደ በተባለው ምርጫ-2007 ታዛቢዎችን ከማባረር ጀምሮ በምስጢር ድምጽ በሚሰጥበት ክፍል ውስጥ ካድሬ አስቀምጦ መራጩ ማንን እንደሚመርጥ ትዕዛዝ እስከ መስጠት የደረሱ ምርጫን የሚያዛቡ፣ ምርጫውን ነጻነትና ፍትሐዊነት የሚያጓድሉ ተግባራት ተፈጽመዋል። ተቃዋሚ ተወዳዳሪዎች፣ የምርጫ ታዛቢዎችና መራጮች በስርዓቱ ጸጥታ ኃይሎች የተሳደዱባቸው፣ የታሰሩባቸው፣ የቆሰሉባቸው፣ የተገደሉባቸው አካባቢዎች በርካታ ናቸው። ምርጫ ቦርድ እነዚህን መሰል ድርጊቶችን የፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚጋለጡባቸውን ስብሰባዎች በየአካባቢው አካሂዶ ትምህርት አግኝቶ ትምህርት መስጠት ካልቻለ፣ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ ካልቻለ ስህተቶች ላለመደገማቸው ምንም ዋስትና የለም።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com