በደቡብ ኦሞ የኮሌራን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የኬሚካል እጥረት አጋጥሟል

Views: 151

በደቡብ ኦሞ ዞን አራት ወረዳዎች ከታኅሳስ 15/2012 ጀምሮ የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ውሃን ለማከም የሚያገለግሉ ኬሚካሎችን ለማግኘት እና የትራንስፖርት አቅርቦት ላይ ችግር እንደገጠመው ዞኑ አስታወቀ።

ወረርሽኙ በዞኑ ማሌ፣ ሀመር፣ ሰላማቦ እና ፀማይ በተሰኙ ወረዳዎች ላይ ከተከሰተ ከአንድ ወር 15 ቀን በላይ ሆኖታል። በበሽታው ከ 1ሺሕ 500 በላይ ሰዎች ተይዘው ሕክምና እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ የ20 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ከዞኑ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

መከሰቱ ከታወቀበት ከታኅሳስ 15/2012 ጀምሮ የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ እና ውሃን ለማከም የሚያገለግሉ ኬሚካሎች እጥረት መኖሩን በዞኑ የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል።

የባለሙያዎችን አበል እንዲሁም የትራንስፖርት ወጪ ለመሸፈን የገንዘብ ዕጥረት እንደገጠመም ለማወቅ ተችሏል።

ወረርሽኙ በተበከለ ውሃ ምክንያት መምጣቱን የገለፁት የዞኑ ጤና መምሪያ የድንገተኛ በሽታዎች ቅኝት እና መከላከል አስተባባሪ ዳንኤል ታምራት፣ በዞኑ የንፁህ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ምክንያት ሰዎች ምንጮችን እና ኩሬዎችን ለመጠጥ ውሃ ምንጭነት እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል።

ውሃን ለማከም የሚያገለግሉ ኬሚካሎች እንደ ልብ አለመገኘታቸው ወረርሽኙን በዘላቂነት ለማስወገድ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ችግር መፍጠሩንም ገልፀው፣ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

አሁን በዞኑ ውሃን ለተወሰኑ ጊዜያት ለማከም የሚያስችል ኬሚካል ተሰራጭቷል። ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቂ ባለመሆኑ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል።

በአካባቢው ያለው ሞቃታማ የአየር ንብረት ጋር ተዳምሮ ሥራዎችን አስቸጋሪ አድርጓል የሚሉት ዳንኤል፣ ተሽከርካሪዎችን ለማሰማራት የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር እንዳለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል የመጠጥ ውሃ ተቋማት አስተዳደር እና ጥገና ዋና ኃላፊ ካሳሁን ወልደጊዮርጊስ፣ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የውሃ ማከሚያ ኬሚካል ለማዳረስ እየተሠራ ነው ብለዋል። ጨምረውም በአንዳንድ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ውሃን በኬሚካል አክሞ ለመጠቀም ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

የኬሚካል ስርጭቱ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች አቅርቦቱን የተሟላ ለማድረግ መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ድጋፍ የሚያገኝበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በቢሮ ጥናት መሰረትም በደቡብ ኦሞ የሚገኝ ‹በርዞ› የተሰኘ ወንዝ ለወረርሽኙ ምክንያት እንደሆነ ተነስቷል። በወንዙ ላይ ማጣሪያ መሣሪያ እንዲገጠም ተደርጓል የተባለ ሲሆን፣ ሌሎች የውሃ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

አካባቢዎቹ አርብቶ አደሮች የሚኖርባቸው በመሆናቸው ሰዎችን በአንድ አካባቢ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ማኅበረሰቡ መፀዳጃ ቤቶች የመጠቀም ልማዱ አነስተኛ መሆኑ እንዲሁም የታከመ ውሃን ለመጠቀም ፈቃደኛ አለመሆኑ በችግርነት ተነስተዋል።

የሟቾችን እና በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር መንግሥት እና ዞኑ ይደብቃል የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ ይህ ግን የተሳሰተ መረጃ ነው ያሉት ዳንኤል፣ ዞኑ ለክልሉም ሆነ ለፌዴራል መንግሥት ትክክለኛውን ቁጥር በማሳወቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር በሰላማቦ ወረዳ ላይ ተመዝግቧል። በሽታውን መቆጣጠር ቢቻልም፣ አሁንም አልፎ አልፎ ተይዘው የሚመጡ ሰዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
የደቡብ ጤና ቢሮ ጤና እና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት እና ምላሽ አስተባባሪ እንደሻው ሽብሩ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በሽታው በተከሰተበት ቀን ብቻ 4 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

ወረዳዎች ተጎራባች መሆናቸውን ተከትሎ በነበረው ባህላዊ የቀብር ሥነ ስርዓት ምክንያትም ወደ አራቱ ወረዳዎቸ ሊስፋፋ እንደቻለ አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር በሰላማቦ ወረዳ ላይ ተመዝግቧል። አስተባባሪውም በቁጥርም 11 ናቸው ያሉ ሲሆን፣ የበሽታውን ስርጭት መቆጣጠር ቢቻልም፣ አልፎ አልፎ ተይዘው የሚመጡ ሰዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

የባለሙያዎችን ወጪ ለመሸፈን ከአጋር ድርጅቶች እና ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመሥራት ላይ እንገኛለን ያሉ ሲሆን፣ ‹‹እስከ አሁንም ክፍያ ያልተከፈለው ባለሙያ የለም። ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሄ ካላገኘ ግን የገንዘብ ዕጥረት ማጋጠሙ የማይቀር ነው›› ብለዋል።

የበሽታው መከሰት ከታወቀ ከ50 ቀናት በላይ ተቆጥረዋል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም በቀን ከ80 እስከ 90 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ሪፖርት ሲደረግ ነበር። ባለፉት 15 ቀናት ግን በአራቱም ወረዳዎች ከ 10 በታች ነው። በሀመር ወረዳ ደግሞ ባለፉት 15 ቀናት ምንም አይነት አዲስ የተያዘ ሰው አልነበረም። የካቲት 3/2012 ኹለት ሰዎች ብቻ በበሽታው ተይዘው መጥተዋል ብለዋል።

በዞኑ ዩኒሴፍ (UNICEF) እና ዩኤንዲፒ (UNDP) በሽታውን ለመከላከል ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆኑም ተጠቅሷል። ስርጭቱን ለመቆጣጠር እስከ አሁን ከ 10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆኗል።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com