የድንጋይ ከሰል ከውጪ ማስገባት ሊቆም ነው

Views: 381

በአገር ውስጥ ያለውን የድንጋይ ከሰል ሀብት ለመጠቀም እና ከወጪ አገራት የሚገባውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ለመተካት በመታሰቡ የድንጋይ ከሰል ከውጪ አገራት እንዳይገባ ሊደረግ ነው።

ከውጪ አገራት የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል ምርት ማስቆም ያስፈለገው፣ ኢንዱስትሪዎች በአገር ውስጥ ያለውን የድንጋይ ከሰል ሀብት መጠቀም እንዲችሉ ለማድረግ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅረቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታደሰ ኃይለማርያም፣ ከሰል ድንጋይ ወደ አገር ውስጥ የማስገባቱ ሥራ በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በኩል ሲፈፀም ቆይቷል ብለዋል። የማዕድን፣ የነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከውጪ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ለመተካት እንዲሁም የከሰል ድንጋዩ ባለው ኬሚካላዊ ይዘት ላይ ጥናት በማድረግ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

አክለውም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ለመተካት በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ የሚውለውን የድንጋይ ከሰል የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ የገለፁ ሲሆን፣ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች በናሽናል ኦይል በኩልም እንደሚከፋፈል ጠቁመዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ የድንጋይ ከሰልን ከደቡብ አፍሪካ በማስገባት ትጠቀማለች ያሉ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ሊለማ እና አገልግሎት ላይ ሊውል የሚችል ሀብት አለ ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሀበሻ ሲሚንቶ ምንጮች፣ ከውጪ አገሮች የሚገባው የድንጋይ ከስል አቅርቦት ሊቆም እንደሆነ ሰምተናል ብለዋል።

ጨምረውም በአገር ውስጥ የሚመረተው የድንጋይ ከሰል ላይ ማሻሻያ ሳይደረግ ሐሰቡ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲቆሙ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዋናነትም ከደቡብ አፍሪካ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የድንጋይ ከሰል ምርት ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን ደረጃ የሚያሟላ ነው ያሉ ሲሆን፣ በአንድ ኪሎ የድንጋይ ከሰል ውስጥ እስከ 6 ሺሕ ኪሎ ካሎሪ የሚደርስ ኃይል ይገኝበታል። በአንፃሩ የአገር ውስጡ ከ3 ሺሕ እስከ 4 ሺሕ 500 የሚደርስ በመሆኑ ተመሳሳይ ምርት ለማምረት የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ምርት ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ እንደሆነ አብራርተዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ባለፈው በጀት ዓመት 13 በመቶ የሚሆነውን የድንጋይ ከሰል ፍላጎት በአገር ውስጥ ለማድረግ ሞክረናል ያሉ ሲሆን፣ ያለው የጥራት እና ኃይል የመያዝ ልዩነት ከውጪ የሚመጣው በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል እንዳደረገው ጠቅሰዋል። ከውጪ የሚመጣው ያለ በቂ ዝግጅት ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ፋብሪካዎችን እና የግንባታ ዘርፉን ይጎዳልም ብለዋል።

አገር ውስጥ የሚመረተው የድንጋይ ከሰል በባህላዊ መንገድ የሚመረት መሆኑ የሚጠበቀውን ያህል ተመራጭ እንዲሆን አላደረገውም። በትኩረት ቢሠራበት እስከ 50 ዓመት የሚሆነውን መተካት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ናሽናል ኦይል በበኩሉ፣ ከደቡብ አፍሪካ በየዓመቱ ከ500 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚደርስ የድንጋይ ከሰል ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ገልጿል። ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እና ለሌሎች ፋብሪካዎች በማቅረብ ላይ መሆኑንም አስታውቋል።

አሁን በአገር ውስጥ ያለው ምርት ደረጃውን የሚያሟላ አለመሆኑን የገለፁት የናሽናል ኦይል ዋና ሥራ አስኪያጅ ታደሰ፣ የድንጋይ ከሰል ዋጋ ከነዳጅ ዘይት ምርቶች ዋጋ እስከ 50 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ አለው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከውጪ የሚገባውን ምርት መተካት የሚችል የኃይል ምንጭ እስኪገኝ ከውጪ የሚገባውን ማቆም የሚለው ሐሳብ አዋጭ አይደለም። ከውጪ ማስገባቱ ይቀጥላል ብዬ አስባለሁም ሲሉ አክለዋል።

የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት በበኩሉ፣ እስከ አሁን የድንጋይ ከሰልን ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማቅረብ አለመጀመሩን ገልጾ በቀጣዩ በጀት ዓመት ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ እገኛለሁ ብሏል።

አዲስ ማለዳ የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የማእድን ዘርፍ ፈቃድ ኃላፊ አበበ ደባሳን እና ሌሎች ባለሙያዎችን በጉዳዩ ላይ መረጃ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com