በመዲናዋ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ህግን በተላለፉ ከ130 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

0
723

አርብ ታህሳስ 22/2014 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ህግ ለማስከበር በሰራው ሥራ በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ህግን በተላለፉ 130 ሺህ 472 አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡

ቢሮው በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ህግን በአግባቡ በመቆጣጠር ነዋሪዎችን ከእንግልትና ተጨማሪ ክፍያ ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

በነዚህ ጥፋተኞች ላይ በተወሰደ እርምጃም 19 ሚሊዮን 630 ሺህ ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉንም ነው ቢሮው የገለፀው፡፡

ቅጣቱ የተጣለው ትርፍ በመጫን፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል፣ ከተመደቡበት ርቀት በታች አቆራርጠው በመጫን፣ ታፔላ ባለመስቀል እንዲሁም ተያያዥ ጥፋቶችን በመፈፀማቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ይህም የክትትልና ቁጥጥር ሥራው በስፋት እየተሰራ መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን፥ በቀጣይም የክትትልና ቁጥጥር ስራውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር በመዘርጋት አሰራሩን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

በተለይ በበዓላትና በምሽት ወቅት መመሪያን በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የተቀመጠውን መመሪያ በመተግበር የትራንስፖርት እጥረት እንዳይከሰት አሽከርካሪዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቢሮው አሳስቧል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ህግን በተላለፉ ከ96 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ይታወሳል፡፡

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here