የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠውን ትምህርት ልጀምር ነው አለ

0
1255

የባከነውን ጊዜ ለማካካስ ቅዳሜ የትምህርት ቀን ይሆናል ተብሏል

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በጦርነቱ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን በመጠገን ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት ሊያስጀምር መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ትምህርት ቢሮው እንደገለጸው ከሆነ፣ ምንም እንኳን በጦርነቱ አካባቢ የነበሩ ትምህርት ቤቶች ቢወድሙም፣ ያለውን ጠግኖ የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሒደት ለማስቀጠል ተማሪዎችን የመመዝገብ ሥራ ተጀምሯል።

የተቋረጠውን ትምህርት ለማስጀመር ይቻል ዘንድ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ተማሪዎች እየተመዘገቡ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት ለማስጀመር ተቋማቱን የመጠገንና የማጽዳት ሥራ እየተከናወነ ነው የሚሉት ኃላፊው፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮም ለተማሪዎች አገልግሎት የሚውል መቀመጫና ወንበር በመግዛት ላይ ነው ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተገኙና ከዘረፋ የተረፉ የትምህርት ግብዓቶችን ለተማሪዎቹ ማሠራጨት እንደሚጀመር አመላክተዋል።
ኃላፊው አያይዘውም፣ ከጦርነቱ ነጻ በወጡ አካባቢዎች ያሉ ትምህርት ቤቶች እንደፀዱና ተማሪዎች እንደተመዘገቡ ያመላከቱ ሲሆን፣ ለአብነትም በሰሜንና ደቡብ ወሎ ያሉ ተማሪዎችን ትምህርት ለማስጀመር ምዝገባ ተካሂዷል ነው ያሉት።

በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ፣ በደቡብ ወሎ ዞን በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች፣ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ አካባቢ ያሉ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን መዝግበው ትምህርት ለመጀመር ቀሪ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ኃላፊው አብራርተዋል።
በተመሳሳይም፣ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ የነበሩ የደሴ ከተማ እና የሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳዎች በበኩላቸው ተማሪዎችን መዝግበው ትምህርት ለማስጀመር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸው ተመላክቷል።

ትምህርት ቢሮው የተቋረጠውን ትምህርት ለማስጀመር የወሠነው ኹሉም ነገሮች ተማልተውለት ሳይሆን፣ ህወሓት ተቋማቱ ላይ ያደረሰው ውድመት ከፍተኛ በመሆኑ፣ የትምህርት ተቋማቱ ሙሉ ለሙሉ እስከሚቋቋሙ ድረስ መጠበቁ እስካሁን ከባከነው ጊዜ በተጨማሪ የትምህርት አሰጣጡን ያስተጓጉለዋል በሚል ሥጋት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም፣ እስከሁን የባከነውን ጊዜ ለማማካካስ ቅዳሜን እንደሌሎቹ የሥራ ቀናት በማሠብ መማር-ማስተማሩ እንደሚከናወን ትምህርት ቢሮው አስታውቋል።
ያለውን በማደራጀትና ከዜሮ በመነሳት ችግሩን መጋፈጥ እንዳለብን በማመን ነው እንጅ፣ በትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት በመድረሱ የተሟላ አገልግሎት መስጠት ይከብዳል ያሉት ኃላፊው፣ በተለይም አንዳንድ ቦታዎች ላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ነው የገለጹት።

ኃላፊው፣ ህወሓት ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ከአራት ሺሕ በላይ የሚደርሱ የትምህርት ተቋማት በአስከፊ ሁኔታ መውደማቸውን እስከ ራያ ቆቦ ድረስ በአካል ሔደው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
ትምህርት ቢሮው ከአሁን በፊት በክልሉ ያሉት ትምህርት ቤቶች በጦርነት ቀጠና ውስጥ በመሆናቸው፣ ሠላም ባለበት አካባቢ ያለ ማንኛውም የትምህርት ተቋም ተማሪዎችን ተቀብሎ እንዲያስተምር ጥሪ ሲያስተላልፍ መቆየቱ ይታወሳል።
እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት፣ ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል እንዳልቻሉ ጌታቸው ገልጸዋል።

መምህራንን በሚመለከትም፣ ከ16 ሺሕ በላይ መምህራን ከሥራ ገበታቸው እንደተፈናቀሉ ያመላከቱት ኃላፊው፣ በዚህ ወቅት ቢሮው እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው እነዚህን ተማሪዎችና መምህራን ወደ ትምህርት ገበታ በመመለስ ላይ ነው ብለዋል።
በጦርነቱ የወደሙትን ከአራት ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመቋቋም እስካሁን ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ የተገመተ ሲሆን፣ ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ጥናት እያደረገ ነው ተብሏል።

ጥናት የሚያደርገው ግብረ ኃይል ሥራውን ሲያጠናቅቅ መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገው ብር መጠን ከተገመተው በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ኃላፊው ጠቁመዋል። የቢሮ ኃላፊው አያይዘውም፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውን ችግሩን በጋራ ለመፍታት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here