በሕገ-ወጥ መንገድ ወደአገር ቤት ገብተው ገበያ ላይ የሚውሉ ምርቶች ላይ ዕርምጃ ሊወሰድ ነው

0
756

በሕገ ወጥ መንገድ ወደአገር ቤት የሚገቡ የመድኃኒት እና መድኃኒትነት ይዘት ያላቸው ምርቶች፣ ሳይመዘገቡ እና ሕጋዊነታቸው ሳይረጋገጥ ገበያ ላይ ቢገኙ ዕርምጃ እንደሚወስድ ኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።
ከተለያዩ አገራት በተለይም ከዩናየትድ አረብ ኢምሬትስ፣ ቱርክ እና ቻይና ለንግድ በሚጓዙ ተመላላሽ ነጋዴዎች አማካይነት፣ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚገቡ የተለያዩ መድኃኒት እና የመድኃኒትነት ይዘት ያላቸው ምርቶች የኅብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተሉ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ምርቶቹ የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ከሚመለከታቸው የሕግ አካላት ጋር በመተባበር ዕርምጃ ለመውሰድ እየሠራ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

የተጨማሪ አልሚ ምግቦች፣ የሰውነት ቅርጽ ማስተካከያ፣ የጸጉር እና ጺም ማሳደጊያ፣ የጠባሳ ማጥፊያ፣ የወሲብ ቆይታ ማርዘሚያ እና የመሳሰሉ ምርቶች አግባብነት ባለው አካል ሳይፈቅዱ እና ጤናማነታቸው ሳይረጋገጥ ወደ አገር ውስጥ ስለሚገቡ፣ ሕብረተሰቡ ሊጠነቀቅ እንደሚገባ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

‹ሲሪየስ ማስ›፣ ‹ሐይፐር ቦልድ›፣ ‹ፒዩር›፣ ‹ሑዌይ› የሚል ሥያሜ ተሰጥቷቸው በሻንጣ ተጓጉዘው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የሰውነት ማጎልመሻ እና ቅርጽ ማስተካከያ ምርቶች፣ ከሦስት ሺሕ 500 እስከ ከስድስት ሺሕ ብር ድረስ ለገበያ እንደሚቀርቡ ለማወቅ ተችሏል።
የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የምግብ ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ ዳግም ንጋቱ፣ የምግብን ድርሻ ይተካሉ፣ የሰውነት ጡንቻ ያጠነክራሉ፣ እንዲሁም ቅርጽ ይሰጣሉ እየተባለ በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ማስታወቂያ የሚነገርላቸው እንደ ‹ሲሪየስ ማስ ፐሮቲን› ያሉ ምርቶች ተቋሙ ዕወቅና እንዳልሰጣቸው አውስተው፣ የምርቶቹን ማስታወቂያ በማንኛውም መንገድ ማስተላለፍ በሕግ የተከለከለ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

እንደ ‹ቀፊራ ዶት ኮም› እና በርካታ ተከታይ ያላቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎችና ድረ ገጾች እነዚህ ሕገ ወጥ ምርቶች ሲያስተዋዉቁ ይታያሉ። በሚመለከተው ባለስልጣን ፈቃድ ያልተሰጠው ምርትን በዚህ መልክ ማስተዋቅ ሕገ ወጥ ድርጊት መሆኑ ተገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ፣ የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑት ንጹህ ወርቅአፈስ፣ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የተለያዩ በቆዳ ላይ የሚቀቡና በአፍ የሚወሰዱ እንክብል ማስታወቂያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ መምጣታቸውን መታዘባቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸው፣ በተለይ በቆዳ ላይ የሚቀቡ መድኃኒቶችን ፣በተለይም የጸጉር ማሳደጊያ ክሬሞች፣ ተጠቅመው ጸጉራቸው ከመምለጥ አንስቶ የተለያዩ ‹ኢንፌክሽኖ ች› የተከሠቱባቸው ታካሚዎች እንደገጠሟቸው ተናግረዋል።

የባለሥልጣኑ ባለሙያ በተለይ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በፋብሪካ ውስጥ ተመርተው የወጡ የምግብ እና አጋዥ ምርቶች፣ ሰው ሠራሽ ንጥረነገሮች ተጨምሮባቸው የሚቀርቡ በመሆናቸው ተፈጥሯዊ ምግቦችን ሊተኩ አይችሉም። አክለውም፣ የሰውነት ቅርጽ የሚያስተካክሉ እንደሆነ በሚመስል መልኩ ለጡንቻ መዳበር ወይም መጠንከር የሚወሰዱ ኬሚካሎች፣ እራሳቸውን ችለው ሰውነትን በቅርጽ እና በጥንካሬ የሚያጎለብቱ መስለው መቅረባቸው ፍጹም አሳሳች እና አግባብነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

በሕክምና ባለሙያ ሳይታዘዙ፣ ማኅበረሰቡ በተለይም ወንዶች ለወሲብ ችግር እና ለብልት መጠን ማሳደጊያነት የሚጠቀሟቸው እንደ ‹ታይታን ጄል› እና ‹ቪማክስ› የተሰኙ ምርቶች፣ ከኹለት ሺሕ ብር እስከ ስምንት ሺሕ ብር ድረስ ነው በገበያ ላይ የሚሸጡት። ምርቶቹ በፋርማሲ ደረጃ የማይሸጡት ሕጋዊነታቸው አጠራጣሪ ስለሆነ ሊሆን ይችላል የሚሉት ባለሙያዋ፣ ምርቶቹ የረጅም ጊዜ የጎንዮሽ ጉዳት ስለሚያስከትሉ ማኅበረሰቡ በቅድሚያ የሕክምና ባለሙያዎች ቢያማክር፣ ከገንዘብ ኪሳራው በላይ ጤናውን አደጋ ላይ ከመጣል ሊድን ይችላል ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here