“የውጭ ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ሱዳን የራሷን ችግር በራሷ መፍታት ይኖርባታል”፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

0
849

ሰኞ ታህሳስ 25/2014 (አዲስ ማለዳ) ሱዳን ያለ ማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንዳለባት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በመግባት ሰላምና መረጋጋት ተስኗት በቀጠለችው ሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ስልጣናቸውን ለቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቅምት ወር አጋማሽ ከሌሎች ከፍተኛ ሹማምንቶች ጋር በወታደራዊ ሃይሉ በቁም እስር ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ኢትዮጵያ በጎረቤት አገር ሱዳን ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሱዳናውያን ያሉባቸውን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲፈቱ ኢትዮጵያ ትሻለች ብለዋል።

በሱዳን ያለው ቀውስ የሚፈታው በሱዳን ሕዝብ ፍላጎት ሊሆን ይገባል፤ጣልቃ ገብነትንም አጥብቀው ሊቃወሙ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ሁልጊዜም የምትፈልገውና ማየት የምትሻው የሱዳንን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ነው ሲሉም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሁለቱ አገራት የድንበር ጉዳይ በውይይት ብቻ እንደሚፈታ ከዚህ ቀደም ስትገልጽ መቋየቷን አስታውሰው አሁንም ይህንኑ አቋም ይዛ ትቀጥላለች ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ከቱርኩ የዜና አገልግሎት አናዶሉ ጋር ከጥቂት ሳምንታት በፊት በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ኢትዮጵያንና ሱዳን የድንበር ጉዳዩን በውይይት በመፍታት ሰላማቸውንና ወንድማማችነታቸውን ያስጠብቃሉ፤ በጋራም ይሰራሉ ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያና ሱዳን አንድ ሕዝብ ነን፤ የፖለቲካ ድንበሩ ሰው ሰራሽ ነው፤ እኛ ለሚሰነዘሩብን ማንኛውም አይነት ማጥቃቶችና ድርጊቶች አሉታዊ የአጸፋ ምላሽ መስጠት አንፈልግም ብለዋል።

ለዚህም አሁን በሱዳን ካለው አስተዳደር በተለይም በሽግግር መንግስቱ የወታደራዊ ክንፍ በኩል እኛን ለግጭት ለማነሳሳት ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ምላሽ ከመስጠት የተቆጠብነው ከዚህ ጉዳይ ጀርባ ሆኖ ግፊት የሚያደርገውን አካል ስለምናውቅ ነው ነበር ያሉት አምባሳደር ሬድዋን በቃለ መጠይቁ ወቅት።

እ.አ.አ በ2019 የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አል-በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትርዐቢይ አህመድ አማካኝነት የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ወሳኝ ሚና መጫወቷን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here