ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰልፈር ይዘት ያለውን ነጭ ናፍጣ ማስገባት ልታቆም መሆኑ ተገለፀ

0
847

ሰኞ ታህሳስ 25/2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰልፈር ይዘት ያለውን ነጭ ናፍጣ ማስገባት ልታቆም መሆኑን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አስታወቀ።

የኢትዮጲያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታደሠ ሀ/ማርያም ከኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ በዓመት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የነዳጅ ፍጆታ ያላት ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 65 በመቶ ነጭ ናፍጣ፣ 18 በመቶ ቤንዚን እና 17 በመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዓመት አገሪቱ ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ግዢ ወጪ እንደምታደርግ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰአት የአገሪቱ እለታዊ የነዳጅ ፍጆታ 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ነጭ ናፍጣ፣ 3 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን እንዲሁም ከ1 ነጥብ 5 እስከ 2 ሚሊዮን ሊትር የአውሮፕላን ነዳጅ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ የፍጆታ መጠን ያለው ነጭ ናፍጣ ከትራንስፖርት በተጨማሪ ለዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች፣ ለማሽኖች እንዲሁም ለተለያዩ ግልጋሎቶች እንደሚውል ይታወቃል፡፡

ድርጅቱ ነጭ ናፍጣ የሚረከበው ትራፊ ጉራ ከተባለ አለም አቀፍ የሎጀስቲክስ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ እንደሆነ ያብራሩት ታደሰ፤ ይህም የሰልፈር ይዘቱ ከፍተኛ ወይም 500ppm መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ የነጭ ናፍጣ ነዳጅ አይነት የአካባቢ ብክለት እና የጤና ችግር የሚያስከትል በመሆኑ በአውሮፓ እንዲሁም በጎረቤት አገራትም ጥቅም ላይ መዋል ካቆመ ቆይቷል ሲሉም ታደሰ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያም የሚፈጥረውን ተጽእኖ ለማስቀረት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የነጭ ናፍጣ ነዳጅን ማስገባት እንደምታቆም አስታውቀዋል፡፡

በምትኩ ዝቅተኛ የሰልፈር ይዘት ያለው ነጭ ናፍጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በዋጋ ተመን ላይ እንዲሁም አጠቃቀምን በተመለከተ ሁሉም ባለድርሻ አስፈላጊው ግንዛቤ ሊኖረው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here