የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት ከፍተኛ መጠን ያለው የስንዴና ዘይት ግዢ መፈፀሙ ተገለፀ

0
963

ማክሰኞ ታህሳስ 26/2014 (አዲስ ማለዳ) የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ከማስፍን አንጻር የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠርና የገበያ ዋጋን የማረጋጋት ፋይዳ ያለው የ4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴና የ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ መፈጸሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የመቶ ቀን እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት እንደተገጸው ባለፉት ጥቅምትና ህዳር ወራት የ4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ግዥ የተከናወነ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 1 ሚሊ ዮን 51 ሺህ 160 ኩንታል ስንዴ ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።

ይህም የስንዴ ዋጋ ከፍ እንዳይል የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የታመነበት ሲሆን፤ የተቀረውም ስንዴ በተቻለ ፍጥነት ተጓጉዞ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በዚሁ ወቅት የ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑም ተመልክታቷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የምግብ ዘይትና ዱቄት ከውጭ በፍራንኮ ቫሉታ (አስመጪዎች በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ) እንዲያስገቡ በመደረጉ የሸቀጦች ዋጋ ባለበት እንዲቀጥል ማስቻሉም ተገልጽዋል፡፡

በመሆኑም በጥቅምት ወር 2014 34 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በህዳር ወር ወደ 33 በመቶ ዝቅ ብሏል።

የሕዳር 2014 ወርሀዊ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ጥቅምት 2014 ጋር ሲነጻጸር በ1 ነጥብ 8 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት 1.0 ከመቶ የጨመረ መሆኑን መረጃው ያሳያል ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here