ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የመንግስትን ሥራዎች የሚከታተሉ የትይዩ ካቢኔ አባላት አዋቅረው ወደ ሥራ መግባታቸውን ኢዜማ ገለፀ

0
456

ማክሰኞ ታህሳስ 26/2014 (አዲስ ማለዳ) ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በሕገ ደንቡ መሰረት የመንግስትን ሥራዎች የሚከታተሉ የትይዩ ካቢኔ አባላት አዋቅረውና መድበው ወደ ሥራ መግባታቸውን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡

ፓርቲው ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የትይዩ ካቢኔ አባላቱ ከሚከውኗቸው ዋና ዋና ሥራዎች መካከል ሪቂቅ ሕጎችን መተቸት፣ በፓርላማ ሀሳብ የሚያቀርቡት አባላትን መደገፍና ማሠልጠን፣ የእያንዳንዱን የሚንስትር መሥሪያ ቤቶች ሥራ መከታተል፣ የተፎካካሪ ፓርቲውን የልዩነት ነጥቦች በየወቅቱ ማስገንዘብ፣ መንግሥትን የሚገዳደር የፖሊሲ ንድፍ ማዘጋጀት፣ በእያንዳንዱ ዘርፍ የተሰየሙት የካቢኔ ሚኒስትሮች ቡድኖቻቸውን በማዋቀርና ኃላፊነታቸውን በማከፋፈል ፓርቲውን ተፎካካሪ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።

በተጨማሪም ትይዩ ካቢኔ የሚለው እሳቤ ከተዘረዘሩ ተግባሮቹ ባሻገር ከጀርባው ሌሎች ወሳኝ ውጤቶችን ይይዛል ብሏል፡፡

በዚህም በስልጣን ላይ ያሉት ሕግ አውጪዎች ተፎካካሪዬ ምን አለ? የሚለውን እንዲያውቁ የሚያደርግ ሲሆን፤ ለመራጩ ደግሞ ለወቅታዊ ተግዳሮቶች ከአንድ በላይ መፍትሔ አለ የሚለውን ማሳየቱ ነው፡፡

ሌላኛው ውጤት ሀሳብ አልባ የሆነ ፉክክርን መቀየሩ ሲሆን፤ ተፎካካሪ የሚባሉ ፓርቲዎችን ወደ አንድ በመሰብሰብ አላማቸውን ለመቀናጀት ዕድል ይሰጣል ሲል ፓርቲው ገልጿል፡፡

የኢዜማ ትይዩ/ጥላ ካቢኔ በምንም መልኩ የተጠባባቂ መንግስትነትና የባለአደራነት ስብስብ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል ያለው ኢዜማ፤ አዎንታዊ ሚናውንም በመለየት የዴሞክራሲ መሣሪያ፣ የሰላምና የልማት መገልገያ አድርጎ ለውጥ አምጪ ማድረግ ይጠበቃልም ብሏል፡፡

ነገር ግን የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ”ካቢኔውን አዋቅረውና መድበው” ወደ ሥራ ስለመግባታቸው ይገለፅ እንጂ በሀላፊነት እነማን እንደተሾሙ በመግለጫው የተጠቀሰ የሥም ዝርዝር የለም፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here