በየመንደሩ በሚካሄድ እርድ ምክንያት አዲስ አበባ በየዓመቱ 1 ነጥብ 53 ቢሊየን ብር እንደምታጣ ተገለፀ

0
1137

ማክሰኞ ታህሳስ 26/2014 (አዲስ ማለዳ) በየመንደሩ በሚካሄድ ደኅንነቱ ያልተጠበቀ እርድ ምክንያት አዲስ አበባ በየዓመቱ 1 ነጥብ 53 ቢሊየን ብር እንደምታጣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አስታወቀ፡፡

ለመጪው የገና በዓልም ከተማው የሚፈልገውን የከብቶች እርድ ለመፈፀም ዝግጁ መሆኑን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ተናግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጀት ከአዲስ አበባ ሉካንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ጋር በመሆን ለገና በዓል ያደረጉትን ዝግጅት በተመለከተ ዛሬ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያና ተወካይ ርብቃ ማስረሻ እንደተናገሩት፣ ድርጅቱ ለገና በዓል ከ2 ሺህ 500 እስከ 3ሺህ የዳልጋ ከብቶች ይመጣሉ ብሎ እየተጠባበቀ ነው፡፡

በዚሁ ጊዜ ውስጥም ከ1 ሺህ 500 እስከ 2ሺህ የበግና የፍየል እርድ ለመፈፀም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ደኅንነቱ ያልተጠበቀ እና በየመንደሩ የሚደረግ እርድ አሁንም የተቋሙ ፈተና መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ፣ ድርጅታቸው ባሉት 40 ባለሙያዎች የቅድመ እና ድኅረ እርድ ምርመራ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የኮቪድ ሥርጭትን ታሳቢ በማድረግም ባለሙያዎች፣ ተሽከርካሪዎች እና የእርድ መፈፀሚያ ቦታዎች በሙሉ በኬሚካል እንዲፀዱ ተደርጓል ተብሏል፡፡

በየመንደሩ በሚፈፀም እርድ ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በታክስ ሊሰበስብ የሚገባውን እስከ 1 ነጥብ 53 ቢሊየን ብር ያጣል መባሉን ሰምተናል ሲል ሸገር ራዲዮ ዘግቧል፡፡

550 ያህል አባል የሉካንዳ ቤቶች በሥሩ እንዳሉ የተናገሩት የአዲስ አበባ ሉካንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አየለ ሳህሌ በበኩላቸው፣ የዘንድሮ የገና በዓል ከመጪው አርብ እስከ ረቡዕ ከፆም ውጪ ሆኖ የሚዘልቅ በመሆኑ በዚህ ጊዜ የሚፈፀመው እርድ ከተጠበቀው በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here