“ከሥር አድምጡኝ የሚለው ሕዝብ ካልተሠማ ከላይ ያለው ብቻ ተነጋግሮ ችግር አይፈታም”

0
900

እመቤት መንግሥቴ ይባላሉ። ኢትዮጵያ ተወልደውና አድገው ያለፉትን 30 ዓመታት በውጭ አገር የኖሩ ናቸው። አራት መጻሕፍትን ለንባብ ያበቁት እኚህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ፣ ለበርካታ ዓመታት በሚዲያ ዘርፍ አገልግለዋል። ዕውቀታቸውን ከማካፈል ጀምሮ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፣ የመጨረሻ መጽሐፋቸውን ሽያጪ ለዓባይ ግድብ ገቢ ማስገኛ እንዲሆን በማበርከታቸውም ይታወቃሉ። ሠሞኑን ለዳያስፖራዎች በተደረገው ጥሪ መሠረትም አገራቸው ተገኝተው የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እያበረከቱ ካሉት እኚህ የአገር ተቆርቋሪ ጋር የአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ቆይታ አድርጓል።

ስለራስዎ ቢያስተዋውቁን?
እመቤት መንግሥቴ እባላለሁ፤ የምኖረው አትላንታ ጆርጂያ አሜሪካ ውስጥ ነው። ከዚህ ቀደም አራት መጻሕፍትን አሳትሜያለሁ። የመጨረሻው መጽሐፌ ለዓባይ ግድብ ስጦታ የተሠጠ ነው። ላለፉት ሰባት ዓመታት በሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይ አዘጋጅና አቅራቢ ሆኜ ሠርቻለሁ። እንዲሁም የሕይወት ተሞክሮ መምህር ነኝ።

እኔ በምዕራቡ ዓለም ከ30 ዓመት በላይ ኖሬያለሁ። መጀመሪያ የሔድኩት ለትምህርት ነበር። የተማርኩት አካውንቲንግ ነው። ትምህርቴን ጨርሼ በአካባቢዬ የነበረ ባንክ ውስጥ ተቀጥሬ ሠርቻለሁ። አሁን ደግሞ የቀን ቀን ሥራዬ ትሬዠሪ ዲፓርትመንት ውስጥ ነው። በግሌ ደግሞ የሬዲዮ ሥራዎችን እሠራለሁ። የጽሑፍ ሥራዎችንም አከናውናለሁ። እንዲሁም አንዳንድ ችግር የገጠማቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ምክር በመስጠት አገለግላለሁ።

ከመጻሕፍቶቸ የመጀመሪያው “የሕልም ሕልም” የተሰኘ ሲሆን፣ የግጥም መድብል ነው። ኹለተኛው “የንጉስ ልጅ” የተሰኘ አጭር መጽሐፍ ነው። ሦስተኛው ደግሞ “አትሔጂም” የተሰኘ ነው። አራተኛውና “ዝም ከምል ብዬ” የተሰኘውና በቅርቡ የወጣው መጽሐፌ የማኅበረሰብ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ነው። ተደጋግመው የምሰማቸውን የማኅበረሰብ ጉዳዮች እንደ አጫጭር ጽሑፎች ወይም መጣጥፍ እንደሚባለው አድርጌ የፃፍኳቸው የተለያዩ 54 ሐሳቦች ናቸው። ሰዎች ለመነጋገሪያ የሚሆኗቸው በር የሚከፍቱ ናቸው ብዬ አስባለሁ። ከመነጋገር እየራቅን ስለሆነ፣ ችግሮቻችንም ተደጋጋሚ ስለሆኑ፣ እንዲሁም እርስ በርሳችን መደጋገፍ ያስፈልገናል ብዬ ስለማምን ነው የፃፍኳቸው። በተለያዩ ጊዜ እየመጡ ያዋዩኝ ሰዎች የነገሩኝ የተለያዩ የማኅበረሰብ ጉዳዮች ላይ በመነሳትም እንደትረካና መጣጥፍ አድርጌ አቅርቤያለሁ።

ከመጡ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ እስካሁን ጽፈው ካበረከቷቸው መጻሕፍት አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የማንበብ ባህል በፊት ከነበረው ጋር እንዴት ያነጻጽሩታል?
ማንበብ መዳበር ያለበት ባህል ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አንባቢ የለም ለማለት ሳይሆን፣ ከዚህ የተሻለ መሆን ይቻላል ስለምል ነው። ብዙ ጊዜ አንድ ጸሐፊ ወይም ደራሲ ይጽፍና አሳትሞ በማከፋፈሉ ሥራ ላይ አንዳንድ እክሎች ተፈጥረውበት ሥራው ወደአንባቢዎች በፈለገው መጠን ላይደርስለት ይችላል። ብዙ ሰው የተጻፈለትን የማያነበው ባህሉ ገና ስላልዳበረ ነው። እኔ አሁን በምኖርበት የምዕራቡ ዓለም ልጆቻቸው ገና ሳይወለዱ ነው ማንበብ የሚያስለምዷቸው። ገና እናታቸው ማህፀን ውስጥ ሆነው ጀምሮ ይነበብላቸዋል። ከተወለዱ በኋላም ራሳቸውን ችለው እስኪያነቡ ድረስ የተለያዩ መጻሕፍትን ያለማቋረጥ ያነቡላቸዋል። ዕድሜያቸው ሲደርስም ቁጭ ብለው እንዲያነቡ ይደረጋሉ። በዚህ ምክንያት ከልጅነታቸው ጀምሮ የነበረውን ይዘው ስለሚያድጉ በቀላሉ ባህላቸው ይሆናል። እኛም ወደእዚህ አይነት ባህል ማዝገም እንዳለብን ተረድቻለሁ።

አዲስ አበባ ከመጣሁ ገና ጥቂት ቀናት ቢሆነኝም፣ ተዘዋውሬ እንዳየሁት ጥሩ ጅምር አይቻለሁ። ጥበብ ከፍ እያለ ነው። መጻሕፍት በየጊዜው እየተመረቁ እንደሆነም ተመልክቻለሁ። ጅምሩ አስደሳች የሆነ ይበል የሚያሰኝ ነው።

አንዳንዶች ቤተ-መጻሕፍት መገንባቱ ብቻ የሚያነብ ከሌለ ጥቅም የለውም ይላሉ። ይህን አመለካከት ለመቀየርና ባህሉን ለማምጣት በልጅነት ከማስለመድ ውጭ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
‹ላይብረሪ› ካለአንባቢ ዝም ብሎ ትልቅ ቤት ነው የሚሆነው። የማንበብ ባህላችንን ማዳበር አስፈላጊ ነው። ከአንባቢ ማነስ ብቻ ሳይሆን የመጻሕፍትም ዕጥረት ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ፣ ምንም ነገር አንብቤ አላውቅም የሚለን ሰው ፍላጎቱ ምን አይነት መጽሐፍ እንደሆነ አውቆ የሚፈልገው ዓይነት ቢሰጠው አንባቢ እንደሚሆን ሊታወቅ ይገባል። ልቦለድ የሚወዱ የሚወዱትን ዓይነት፣ ታሪክንም ለሚመርጡ እንደፍላጎታቸው በቀላሉ እንዲያገኙ ቢደረግ ባህሉን ማምጣት ይቻላል። የማንበብን ልማድ ለማዳበር በርከት ያሉ የተለያየ ይዘት ያላቸውን መጻሕፍት ማቅረብ ያስፈልጋል። ትልልቅ ላይብረሪዎች መክፈት የነበረውን ዕጥረት በመቅረፍ ለውጥ ያመጣል የሚል ዕምነት አለኝ። በልጅነትም የማንበብ ባህልን ሕፃናት እንዲያዳብሩ ከፍላጎታቸው ጋር የተገናኘ መጽሐፍ እንዲያገኙ መደረግ ይኖርበታል።

በአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ሕብረተሰቡ መጻሕፍትን እንዲያነብ የተለያዩ ማበረታቻዎች ይደረጋሉ። ይህን መሠል መንገዶች ባገራችን ውጤታማ ይሆናሉ ይላሉ?
ኹሉም ነገር ከፍላጎት መጀመር አለበት። ሰው ፍላጎት ከሌለው ማበረታቻ ቢሰጠውም በዘላቂነት አንባቢ የሚያደርገው መንገድ አይኖርም። የማበረታቻና የማስተዋወቂያ ነገሮች ሊጠቅሙ ይችላሉ። እኔ በነበርኩበት አካባቢ የነበሩ ቤተ-መጻሕፍት አንባቢ ለመሳብ ብዙ ነገሮችን ያደርጋሉ። ለምሳሌ ለልጆች የሚነበብበት ፕሮግራም አላቸው። ደራሲዎቹ ቁጭ ብለው መጽሐፋቸውን የሚያነቡበት ፕሮግራም ይያዝላቸዋል። ለልጆቻቸው የሕፃናት መጻሕፍት በሚነበብበት ወቅት ለወላጆችም የሚሆኑ በቅርብ እንደየፍላጎታቸው ይዘጋጃል። ይህ ዓይነት የንባብ ዝግጅት ለአዋቂዎችም ይዘጋጃል። ሕብረተሰቡን ወደውስጥ ሊስቡ የሚችሉ ነገሮች በቤተ-መጻሕፍት በኩል ሊታሰብባቸው ይገባል። እንዲህ ብታነቡ እንዲህ ይደረግላችኋል የሚል ሙስና የመሰለ መንገድ ሳይሆን የሚያዋጣው፣ ሰውን ስበው የሚያስገቡና በዘላቂነት ባህሉ እንዲያደርጋቸው የሚያደርጉ መሆን አለባቸው።

ከዋጋ ረገድ የወረቀት መወደድ የመጻሕፍት ዋጋ እንዲወደድ አድርጓል በማለት መንግሥት አቅሙ የሌለው በቀላሉ ገዝቶ እንዲያነብ የሚያስችለው የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ አለበት የሚሉ አሉ። በዚህ ረገድ ከነበሩበት አካባቢና ከሌላው ዓለም ሲነጻጸር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
በዚህ ረገድ ገና መምጣቴም ስለሆነና ዕውቀቱ ብዙም ስለሌለኝ የምናገረው አይኖርም። የሰው ልጅ ለሚወደው ነገር ሁልጊዜ ገንዘብ ይኖረዋል። መጠጥም ሆነ አልባሳት የሚወድ ተወደደ ብሎ አይተወውም። የመጻሕፍት ፍቅር ያለውም ሰው የምርጫ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ይገዛል ብዬ ነው የማምነው። ስለውድነቱ ግን ግንዛቤዬ ብዙም ስላልሆነ መናገር አልችልም።

ሠሞኑ በዓል እንደመሆኑ ስጦታ መሰጣጠት እየተለመደ መጥቷል። መጻሕፍትን ማበርከትስ ሊለመድ ይገባል ይላሉ?
መጽሐፍ የዕውቀት በር ስለሆነ በሥጦታ መልክ መስጠት መለመድ አለበት። መጻሕፍት ሕይወታችንን ልንቀይርበት ከፍም ልንልበት የምንችልባቸው ትልቅ ሀብቶች ናቸው። ስለዚህ መጻሕፍትን በሥጦታ መልክ መስጠት በተለይ ለልጆች እጅግ ጠቃሚ ነው። በቀናት ውስጥ የሚበላሽ አሻንጉሊትና መጫወቻ ብቻ ከመስጠት እንዲሁም ከወራት በላይ የማይገለገሉበት አልባሳት ላይ ከማተኮር መጻሕፍትን መስጠት ብንጀምር ትውልድን በቀላሉ እስከዘላለሙ መቀየር እንችላለን።

ወደ መጽሐፎችዎ እንምጣና፣ የመጨረሻውን ለዓባይ ግድብ ለማበርከት ምን አነሳሳዎት? ያስገኘውስ ገቢ ምን ያህል ነው? ለሌላውስ ምን መልዕክት ያስተላልፋል ይላሉ?
እኔ አራተኛ መጽሐፌን ለዓባይ ግድብ ልሰጥበት የቻልኩበት ዋናው ምክንያት፣ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ምን መደረግ አለበት ከሚል ሐሳብ ተነስቼ ነው። ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብዬም ሳይሆን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አንድ የራሴን ድርሻ ለማበርከት ነው። የራሴን ጠብታ እንዴት ነው ማስቀመጥ የምችለው ብዬ አስቤ ነው የወሰንኩት። ሦስት ጥቅሞችን ይዤ ነው የሰጠሁት። በመጀመሪያ፣ የሚገዛው ሰው አንብቦ አንድ ኹለት ፍሬ ነገር ያገኝበታል ብዬ ነው። ኹለተኛ፣ ትንሽም ብትሆን እንደጠብታ ግድቡን ይጠቅማል። ሦስተኛ ደግሞ፣ ለካ እንዲህ ማድረግ ይቻላል የሚልን ሌላ ሰው ልቆሰቁስ እችላለሁ ብዬ ነው።

እስካሁን ምን ያህል ገንዘብ አስገብቷል የሚለውን በተመለከተ እንግዲህ እስካሁን በአውሮፓና አሜሪካ ከ12 ሺሕ እስከ 15 ሺሕ ዶላር ገቢ ተደርጓል። አዲስ አበባ ግን ገና አልተከፋፈለም። በየኤንባሲው ተሸጦ ዕዛው ነው የተሰጠው። በየቦታው ገና ያልተሸጡ ይኖራሉ እነሱም ተሸጠው ገቢ ይደረጋሉ። አገር ውስጥ መጽሐፉ ጥሩ ሽፋን ስላገኘ ልናከፋፍል አስበናል። ከአንድ ወኪል ጋር ሽያጩን አሰባስቦ ለግድቡ ገቢ እንዲያደርግልን እየተስማማን እንገኛለን።

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ የ “#በቃ” ዘመቻን በማካሄድም ሆነ ስለኢትዮጵያ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር እስካሁን ያደረገውን እንዴት ያዩታል?
ዳያስፖራው እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል ብል መልካም ይመስለኛል። ድጋፉም ሆነ እንቅስቃሴው በአንድ ዙር አልቆ ይቆማል የሚል ግምት የለኝም። አሁን ከተከሰቱት ችግሮች አኳያ ሥራ ተጀምሯል፣ ሕዝቡም ተሰባስቦ እየተደጋገፈ ነው። ብዙ መልካም ነገሮች እየተሠሩ ነው። ይህ መልካም ጅምር እንጂ የስኬት መጨረሻ አይደለም። ኢትዮጵያችንን ከምዕራቡ ዓለም ለማላቀቅ ገና ብዙ መጓዝ ይኖርብናል። በምንም ነገር ጥገኛ ላለመሆን ብዙ መሠራት አለበት። ኢትዮጵያን ይለውጣሉ ብለን ካሰብናቸው ነገሮች አንዱ ግድቡ እንደመሆኑም ድጋፋችን ይቀጥላል።

በውጭ አገር ባሉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አለ የሚባለውን ክፍፍል ለማስቀረትና ወደ አንድ ለማምጣት እንዲህ ዓይነት አገራዊ እንቅስቃሴዎች ይጠቅማሉ ይላሉ?
ክፍፍሉ ነበር በሚል መታረም ይገባዋል። አሁን “#በቃ” በሚለው እንቅስቃሴም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች እንዳየነው ከሆነ መከፋፈሉ ቀርቷል። አሁን አንድነታችን በይፋ እየታየ ነው። ስንሰባሰብ አቅማችን ጠንካራ እየሆነ ነው። ብዙ መልካም ነገሮችን በኅብረት እያደረግን ነው።
የ”#በቃ” እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረ፣ ፈጣን ሠደድ እሳት ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ይጀምሩት እንጂ አሁን የአፍሪካ አገሮችም እየተከተሉት ይገኛሉ። በካረቢያን ያሉት ጃማይካን የመሳሰሉ የምዕራባውያን ተጽዕኖ ያለባቸው አገር ዜጎችም እየተቀላቀሉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያውያኖች የጀመሩት የሚያኮራ እሳት ነው ማለት ይቻላል። ጠላት፣ ተከፋፍለዋል አንድ መሆን አይችሉም እያለ ስለነበር አሁን የገጠማቸው ያልጠበቁትና ያሳፈራቸው ነው። ይህ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያውያኖች ብቻ ሆኖ ተወስኖ እንደማይቀር፣ ሁሉንም የሚያጠናክር እንደሚሆን ዕምነት አለኝ።

ሠሞኑን ጥሪ በተደረገው መሠረት ዳያስፖራው ወደአገር ቤት መጥቷል፤ እየመጣም ይገኛል። ሒደቱ እንደከዚህ ቀደሙ ቤተሰብ ጋር ቆይቶ መመለስ ብቻ ይሆናል ወይስ የተለየ ይሆናል ይላሉ?
ሁሉም ሲመጣ የያዘውን ከጣለ ጥሩ ነው። ጠብታ ሲጠራቀም ኩሬ ይሆናል። ቀስም እያለ ወደ ሐይቅነት ይቀየራል። ለአገራቸው ብዙ ማድረግ የሚችሉትን ያህል፣ አቅም ባይኖረኝ እንኳን አገሬ ጠርታኛለች ደርሼም ቢሆን እመለሳለሁ የሚሉ አሉ። ተሰባስበው በቡድን ሆነው የሚመጡም አሉ። እኔ የማውቃቸው ሐኪሞች ተሰብስበው መምጣት የሚችሉት የሙያ ግልጋሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አውቃለሁ። ሌሎች ደግሞ ከቱሪስት መዳረሻዎች በተጨማሪ የተጎዱ ማኅበረሰቦችንና የወደሙ አካባቢዎችን የሚጎበኙ አሉ። በተለያየ መንገድ ለማገዝ የተሰባሰቡ፣ በግልም የሚመጡ ስላሉ በዚህ የተወሰነ ነው ለማለት አያስችልም። ለምሳሌ ወንድሜ አገሬ ስለጠራችኝ አልቀርም ብሎ 20 ሰዓት በሮ፣ ያመጣውን ገንዘብ አስረክቦ ሥራ ስለሚኖርበት ከበዓሉ አስቀድሞ ተመልሷል። የተለያዩ የአገር ፍቅር ውስጣቸው እየነደደ በቻሉት መንገድ የሚደግፉ አሉ። ሁሉም ሌላ ቦታ ዞርዞር ብሎ ለማየት አቅሙና ጊዜው ላይኖረው ይችላል።

ከዚህ ቀደም በዘመቻ መልክ ተጀምሮ እንደነበረው የአንድ ዶላር እንቅስቃሴ የአሁኑም ጊዜያዊ ሆኖ እንዳይቀር ምን መደረግ ይኖርበታል?
አሁን የመጣንበትን የመጀመሪያውን ነገር ከጨረስን በኋላ የምናስብበት ይሆናል። በትላልቅ ውይይቶች መታቀድ ያለበት ነው የሚሆነው። የአሁኑ ጅምር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያደርገውን ነገር አገሬ ጠርታኛለች ብሎ ወደጎን አስቀምጦ ነው የመጣው። ይህ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። እዚህ የመጣ ሰው ሁሉ ሆቴል ሲጠቀምም ሆነ ገበያ ዕቃ ሲገዛ ለአገሩ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። ይዞት የሚመጣው ሐብት ኢኮኖሚውን ያነቃቃል። ይህ የአሁን የመጀመሪያ ዙር ነው። ከዚህ በኋላ ቁጭ ተብሎ ታቅዶ ዘላቂ እንቅስቃሴ እንዲሆን መሠራት ያስፈልጋል።
በቀን አንድ ዶላር ሲሰበሰብ የነበረው የቀረ አይመስለኝም። ከነበረው ሰፋ አድርጎ ለመቀጠል ግን ሰፊ ንግግር የሚፈልግ ነው። አሁን ዛሬ ላይ ሆነን ለወደፊት ይሄ ይደረግ ለማለት ያስቸግራል። ዕቅዶች መውጣትና ብዙ ለውጦች መደረግ እንዳለባቸው ኹላችንንም የምናምንበት ነው። ኢትዮጵያዊ ኹሉ ዜጋ ነኝ ብሎ ያመነ ሁሉ ማንም የእንጀራ ልጅ ሳይኖር ኹላችንንም ኢትዮጵያ የምታስተናግድበት ቀን እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ።

በርካታ ዳያስፖራዎች ለቤተሰባቸው ብር ሲልኩ ከሕጋዊው መንገድ ይልቅ የተከለከለውን እንደሚጠቀሙ ይነገራል። ይህ ዓይነት አሠራር አገርን እንደመጉዳቱ ቀስ በቀስ ለማቆም ምን መደረግ ያለበት ይመስሎታል?
ይህ በተደጋጋሚ የተነገረ ነገር ነው። ለውጦች ሊኖሩ ይገባቸዋል። አሁን በዚህ ሰዓት እንኳን ብዙዎች በባንክ እየመነዘሩ ይመስለኛል። ስለዚህ ጉዳይ፣ “መፆም አማረኝ” የሚል አንድ ጽሑፍ አስተላልፌ ነበር። ቢያንስ ለአንድ ለኹለት ዓመታት ገንዘቡ ቢያጓጓም በሕገወጥ መንገድ መጠቀምን ለአገራችን ስንል እንደፆም ፈልገን እንተወው ለማለት ፈልጌ ነበር የፃፍኩት። ባንክ 45 ብር እየመነዘረ 65 የሚመነዝሩ ሰዎች ስላሉ አቅም የሌለው ሰው ያንን ሊመርጥ ይችላል። መብላት እያማረን እንደምንፆመው በተከለከለ መንገድም ገንዘብን ከማግኘትም እንቆጠብ የሚል ሐሳብ ነበር። እኔ ብቻ ሳልሆን ይህን ሐሳብ ብዙዎች ጽፈውታል፤ ተናግረውታል፤ ሐሳቡንም ይደግፉታል። በዚህ ረገድ የተለመደውን አሠራር ልናሻሽለው የምንችለው በምን መንገድ ነው ብለን ማሰብ ይኖርብናል። ከበፊቱ ብዙ የተቀየረ ነገር ቢኖርም ገና በሒደት መለወጥ ያለበትም አለ። ላኪውም ሆነ የሚቀበለው ቤተሰብ አቅሙ ሳይጎዳ ለውጡን ለማምጣት መንግሥት ምንዛሬውን ከፍ ማድረግም ይሁን አስፈላጊ መሻሻያዎችን ማድረግ ይጠበቅበት ይሆናል።

ለውጥ ለማምጣት ካላችሁ ዕቅድ አኳያ ዘላቂ የሆነ ዓላማችሁን የሚያስፈጽም ተቋም ለመመሥረት የታቀደ ነገር አለ?
ኹሉም ሰው አገር አለኝ እመለሳለሁ ብሎ ነው የሚያስበው። ለአገሬ ይህን አበረክታለሁ፤ ይህን አደርጋለሁ፤ ይህንን ወደፊት አራምዳለሁ እያልን ነው ኹላችንም የምንኖረው። በጋራ ዓላማን ለማሳካትና ዕቅድን እውን ለማድረግ ትልቅ ፋይናንስና ጊዜ ይፈልጋል። በጊዜ ሒደት ማስተካካል ያለብንን ነገሮች እያረምን ተግባራዊ የማናደርገው ነገር አይኖርም። ከብዙ ሰዎች ጋር በኅብረት የሚሠሩ ሥራዎች ሁሌም ሊኖሩ ይችላሉ። አሁን በዚህ ሰዓት ግን በአገራዊ ጥሪው መሠረት አንገብጋቢውን ችግር ከፈታን ለሌላው እንደርስበታለን ብዬ ነው የማስበው።

በመጽሐፎችዎ ያነሷቸው ሐሳቦች መወያያ የሚሆኑ ሐሳቦች እንደሆኑ ነግረውናል። ከዚህ አንፃር ሰሞኑን በመንግሥት የተጀመረውን አገራዊ የውይይት ሒደት እንዴት ይገመግሙታል? መካተት አለባቸው የሚሏቸው ሐሳቦችና ግለሰቦች አሉ?
አዎ በእርግጥ ይኖራሉ። “ፕርሴፕሽን ኢዝ ሪያሊቲ” የሚሉት ነገር አለ። እኔ ከመጣሁ በኋላ በዚህ ጉዳይ ጥቂት ሰዎችን ባገኘሁዋቸው አጋጣሚዎች አነጋግሬያለሁ። ብዙ የተለያዩ ሐሳቦችን የሚሰጡ ሰዎች እንዳሉ ተመልክቻለሁ። አመለካከታችን ወደ እውነቱ ከመቀየሩ በፊት መነጋገር ያስፈልጋል። ይህ ማለት እኔ ቆስዬ አሞኛል የሚልን ሰው አይ ያንተ ቁስል አይሰማኝምና የኔ ይሰማህ የሚለው ነገር መቅረት አለበት። ኹሉም ሰው እንደኢትዮጵያዊነቱ እኩል ተሰምቶ፣ ተከብሮ፣ ታክሞ የሚኖርባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር አሁን የተጀመረው የመወያያ መድረክ ሰፋ ብሎ ኹሉንም አቅፎ መያዝ ይኖርበታል። ከሥር አድምጡኝ የሚለው ሕዝብ ካልተሰማ ከላይ ያለው ብቻ ተነጋግሮ ችግር አይፈታም። ዳያስፖራውም የንግግሩ አካል መሆን ይጠበቅበታል። በሙያው መሳተፍ የሚችለውም መካተት ይኖርበታል። ውይይቱ ላይ ገንቢ ሚና ሊኖራቸው የሚችሉ በርካታ ሰዎች አሉ።

ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ኹሉም ራሳቸውን እንደአምባሳደር ቆጥረው ለአገራቸው እንዲያስቡ ለማድረግ ምን ያስፈልጋል?
ኢትዮጵያውያኖች እንደሁሉም የዓለም ዜጋ መደረግ ያለበትን ነገር እያደረጉ ቢሆንም፣ የበለጠ ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል። ለምሳሌ፣ ሕንዳውያን ውጭ አገር ሆነው ወደ አገራቸው ማዘዋወር የሚችሉትን በሙሉ አሻግረው በማሠራትም ሆነ አገራቸውን በመጥቀም ይታወቃሉ። ጊዜያቸውን የሚቆጥብላቸው መሆኑ ብቻ ሳይሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዜጋቸውን የሚጠቅም ነገር ላይ ይሳተፋሉ። ሥራን ባሉበት ኹነው ያሠራሉ። እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች አሁን ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው። ብዙ የኢንጂነሪንግ፣ የፕላኒንግና የመሳሰሉ ሥራዎችን ወደ ኢትዮጵያ ልከው የሚያሠሩ እንዳሉ አውቃለሁ።

ወቅቱን አስመልክተው ማስተላለፍ የሚፈልጉት ነገር ካለ?
ለመላው ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ እላለሁ። ከኔ በፊት ኢትዮጵያን ብለው በየጥሻውና በዱር በገደሉ አገር ድንበር እያስከበሩ ላሉ ወገኖችና ለቤተሰቦቻቸውም እንደዚሁ እንኳን አደረሳችሁ እላለሁ። ለአገር ሲሉ ላለፉ ወገኖች ቤተሰቦች በዚህ አጋጣሚ አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን ለማለት እፈልጋለሁ። አመሰግናለሁ።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here