በኢትየጵያ ከሚከበሩ ዐበይት በዓላት ውስጥ ቀደሞ ወደ አእምሮ ከሚመጡት አንዱ፣ ታኅሣሥ 29 የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሆነው የገና በዓል ነው።
ገና የሚለው ቃል ከግሪክ ቋንቋ የተገኘ ሆኖ ትርጉሙም ልደት ማለት ነው። የክርስቶስ የልደት በዓል በመላው ዓለም በተለያዩ አገራት የሚከበር ሲሆን፣ የጎርጎሮስያኑን የዘመን አቆጣጠር በሚከተሉ አገራት ታኅሣሥ 16 (December 25) ይከበራል።
ሌሎች ጥቂት አገራት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ታኅሣሥ 29 ያከብሩታል። በዚህም ሕንድ፣ እስክንድርያ፣ ግብጽ፣ ሶሪያ እና አርመንያ የመሳሰሉት ከኢትዮጵያ ጋር በተመሳሳይ ቀን የገና በዓልን የሚያከብሩ አገሮች ናቸው።
በኢትዮጵያ የክርስቶስ ልደት በዓል አከባበር ሲነሳ ደግሞ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን አለማሰብ የሚቻል አይደለም።
ውቅር አብያተ-ክርስትያናቱን በ13ኛው ክፍለ ዘመን የዛጉዌ ሥርወ-መንግሥት ንጉሠ ነገሥት የነበረው ላሊበላ ከአንድ ወጥ ቋጥኝ ጠርቦ የሠራቸው እንደሆነ ይታመናል።
መምህር ደረጀ ነጋሽ በዚህ ላይ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ሐሳብ፣ ቅዱስ ላሊበላ ከአስራ አንዱ የዛግዌ ሥርወ-መንግሥት ነገሥታት አንዱ ሲሆኑ፣ ለአርባ ዓመት ከነገሡት ሰባቱ ውስጥም አንዱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን ከአራቱ ቅድስናን ከተላበሱ የዛጉዌ ሥርወ-መንግሥት ነገሥታት አንዱም ነበሩ ይላሉ።
ንጉሥ ላሊበላ ለኃይማኖታዊ ጉዞ በተደጋጋሚ ወደ እየሩሳሌም ያቀኑ እንደነበር አንስተው፣ እየሩሳሌምን ንጉሥ ላሊበላ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢትዮጵያውያንም መሳለም ይፈልጉ ስለነበር፣ በግብጽ በረሃ ይደርስባቸው የነበረውን ችግር ለማስቀረት የእየሩሳሌምን አምሳያ በኢትዮጵያ እንደተከሉ ነው የገለጹት።
በዚህም ንጉሥ ላሊበላ 11 ውቅር አብያተ-ክርስትያናት ያሳነጹ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ቤተ-መድኃኔዓለም ከኹሉም ትልቁ እና 72 አዕማዳት ያሉት ነው።
ቤተ-ማርያም ደግሞ ንጉሡ አብዝተው ይወዱት የነበረና በቀን ለብዙ ጊዜ የሚመላለሱበት፣ ቤዛ ኩሉ ያሬዳዊ ዜማም የሚቀርብበት ነው ሲሉ ይገልጻሉ መምህሩ። ቀሪዎችም ቤተ-ደናግል፣ ቤተ-መስቀል፣ ቤተ-ደብረ ሲና፣ ቤተ-ጎለጎታ፣ ቤተ-አማኑኤል፣ ቤተ-አባ ሊባኖስ፣ ቤተ-መርቆሪዎስ፣ ቤተ-ገብርኤል ወሩፋኤል እና ቤተ-ጊዮርጊስ (ባለ መስቀል ቅርጹ) ናቸው።
በላሊበላ የገና በዓል ታኅሣሥ 29 በልዩ ድምቀት ይከበራል። ዕለቱ ንጉሥ ላሊበላ የተወለዱበት ቀንም ነው። ቤዛ ኩሉ ተብሎ የሚጠራው በነግህ የሚደረገው ያሬዳዊ ዝማሬ ደግሞ በዚሁ በዓል የሚቀርብ ልዩ እና ታላቅ መንፈሳዊ ትዕይንት ነው።
ዝማሬው የሚደረገውም ከቅዳሴ በኋላ በቤተ-ማርያም ሲሆን፣ ከታች ባለ ነጭ ካባ ካህናት፣ ከላይ ደግሞ ባለ ጥቁር ካባ ካህናት፣ እንዲሁም ዲያቆናትና ምዕመናን ተደርድረው በቅዱስ ያሬድ ዜማ ቤዛ ኩሉ እያሉ ይዘምራሉ። ይህም ክርስቶስ በቤተልሔም ሲወለድ በሰማይ መላዕክት፣ በምድር ደግሞ እረኞች (ሰብዕ) በአንድነት ሆነው መዘመራቸውን ለማሳየት መሆኑን አስረድተዋል።
የክርስቶስ ልደት በዓልን በኢትዮጵያ ማክበር የተጀመረው ጥንት ክርስቶስ ሲወለድ ጀምሮ መሆኑን የሚገልጹት መምህር ደረጀ፣ ክርስቶስ ሲወለድ እጅ መንሻ ይዘው ወደ ቤተልሔም ከሔዱት ሰብዓ-ሰገል ከሚባሉት የጥበብ ሰዎች አንዱ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ባዜን ነው፤ ይህም ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ልደት ጋር የተለየ ቁርኝት ያላት አገር መሆኗን ያሳያል ባይ ናቸው።
አክለውም፣ በንጉሥ ባዜን አማካይነት የተመሠረተውና ከአሥመራ በቅርብ ርቀት ወደ ምጽዋ በሚወስደው መንገድ፣ ልዩ ስሙ ንፋሲት በሚባለው ቦታ የሚገኘውን የደብረ ቢዘን አቡነ ፊሊጶስ ገዳም ያነሳሉ። በዚህም ገዳሙ የገና በዓል በኢትዮጵያ እንዲከበር ትልቅ ሚና እንደነበረውም ነው የገለጹት።
በመቀጠልም፣ በ330 ገደማ በአብርሃና አጽብሃ ዘመን፣ አባ ፍሬምናጦስ በጣና ዙሪያ የሚኖሩትን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል እንዲሸጋገሩ በማድረግም፣ ከበፊቱ ሠፋ ባለ ኹኔታ እንዲከበር ሥራዎች መሥራታቸውን ጠቁመዋል። በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመንም እንዲሁ በአጼ ካሌብ አማካይነት ገና በኢትዮጵያ በሥፋት እንዲከበር ሙከራ ተደርጓል ነው ያሉት።
አይይዘውም፣ ገና እና ኢትዮጵያን መነጣጠል አይቻልም ያሉ ሲሆን፣ እንደማሳያም ብዙ አገራት ለዘመን አቆጣጠራቸው ጣኦትን መሠረት ሲያደርጉ እኛ የፈጣሪን መወለድ ነው መሠረት የምናደርገው ብለዋል።
በዚህ ዓመት ላሊበላ ላይ የሚከበረው የገና በዓል፣ ከወትሮ በተለየ ቦታው ከህወሓት ኃይሎች ነጻ ከወጣ በኋላ የሚከበር በመሆኑ የክብረ በዓሉን ድባብ ለየት ያደርገዋል።
ከዚህ በፊትም በተለያዩ የወረራ ጊዜያት በዓላትን አካባቢው ላይ ለማክበር ችግር ያጋጥም እንደነበር ያነሱት መምህሩ፣ የአሁኑን እጅግ የከፋ የሚያደርገው እርስ በርስ የተደረገ እና ታይቶ የማያውቅ ጭካኔ የተሞላበት ግፍ የተፈጸመበት መሆኑ ነው ብለዋል። ከዚህ ሠቆቃ ማግስት በውጭ አገራት የሚኖሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጥሪ ተደርጎላቸውና ወደ አገር ቤት መጥተው የሚከበር በዓል በመሆኑ የዘንድሮው ለየት ይላል ሲሉ ተናግረዋል።
ከተማዋ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ሆና ለወራት ብትዘልቅ ኖሮ የገና በዓል በቦታው አይከበርም ነበር። አሁን ላይ አካባቢው ነጻ ሆኖ በዓሉን ማክበር መቻሉ በርካቶች በደስታ ወደ ቦታው እንዲያቀኑ ያደርጋቸዋል የሚል ዕምነት አለ።
የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ እምቢያለ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹትም፣ በውጭ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ከመጡ በኋላ ከበዓሉ ይዘት ጋር በተገናኘ ብቻ ሳይሆን፣ ከነበረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ የገና በዓልን ለማክበር ብዙዎች ላሊበላ ላይ ይገኛሉ የሚል ዕምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ይህም በኮሮና ወረርሽኝና በጦርነት ክፉኛ ተጎድቶ የነበረውን የክልሉን ቱሪዝም ለማነቃቃት ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር፣ በተለይ ግፍ ሲፈጸምበት የቆየው የአካባቢው ማኅበረሰብ ወገንተኝነት እና አይዞህ ባይ ስሜት እንዲያድርበት ያደርጋል ነው ያሉት።
በዚህም፣ በዓሉ በድምቀት ተከብሮ በሠላም እንዲጠናቀቅ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የሚመራ ዐብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ከላሊበላ ከተማ ከንቲባ፣ ከጎንደር ከተማ ከንቲባ፣ ከታክሲ ማኅበራት፣ ከባለ ሆቴሎች፣ ከአስጎብኝ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በሰፊው ምክክር እንደተካሔደ አንስተዋል።
ላሊበላ ከተማም በህወሓት ኃይሎች በርካታ መሠረተ ልማቶቿ መውደማቸውን ጠቅሰው፣ አሁን ላይ የስልክ አገልግሎት ቢኖርም፣ መብራት እና ውኃም በጣም አስፈላጊ በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል። የላሊበላ አየር ማረፊያ ከወደሙ መሠረተ ልማቶች አንዱ መሆኑ እና ነገር ግን ጥገና ተደርጎለት ታኅሣሥ 24/2014 ቀን ጀምሮ የበረራ አገልግሎት መጀመሩን ገልጸዋል። በዕለቱም ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን በመያዝ ኹለት ጊዜ በረራ ያደረገ ሲሆን፣ ከዚያ ቀን ጀምሮ እንግዶች ወደ ከተማዋ እየገቡ እንደሆነ አመላክተዋል።
ከገና በዓል በተጨማሪ በቅርብ ቀን ለሚከበረው የጥምቀት በዓልም ዝግጅቶች እየተደረጉ በመሆናቸው፣ የሙያተኞች ቡድን ተቋቁሞ ወደ ጎንደርና ላሊበላ ከተሞች በማቅናት እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ ያለውን ዝግጅት በማስተዋል ክፍተቶች እንዲሟሉ ይደረጋል ሲሉም ኃላፊው ተናግረዋል።
ይህ የሙያተኛ ቡድን ባጣራው መሠረትም፣ ቅድሚያ ለሚከበረው የገና በዓል በላሊበላ ከተማ ውስጥ 25 መካከለኛ እና ዘጠኝ ትላልቅ ሆቴሎች መኖራቸውንም ቡድኑ አረጋግጧል ብለዋል። በዚህም በድምሩ 34 ሆቴሎች አገልግሎት ለመስጠት የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ያመላከቱት።
ሌሎች አራት ሆቴሎች በወራሪ ቡድኑ ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ የተዘረፈ በመሆኑ አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው ያሉት ኃላፊው፣ 34ቱ ሆቱሎች ግን እንግዶችን በአግባቡ ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን፣ መጠነኛ ቅናሽ (30 በመቶ) እንዲያደርጉም ይጠበቃል ሲሉ አብራርተዋል።
ሆኖም ያሉት ሆቴሎች ውሱን በመሆናቸው ኹሉም ሰው ሆቴል ያርፋል ተብሎ አይጠበቅም፣ ለዚህ ደግሞ የከተማው እና ትንሽ ወጣ ብሎ የሚገኘው የአካባቢው ማኅበረሰብ በየቤቱ ድንኳን በመትከል ለእንግዶች ማረፊያ እንዲያዘጋጅ ከወጣቶች፣ ከኃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ውይይት መደረጉን አመላክተዋል። እንግዶችም ያሉት ሆቴሎች በቂ ስላልሆኑ ይህ በየዓመቱ የተለመደ ተግባር መሆኑን ያውቃሉ ነው ያሉት።
ባለፉት ኹለት ዓመታት በከተማዋ የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ በጣም የተዳከመ ስለነበር፣ የአሁኑ የገና በዓል ከፍተኛ ገንዘብ ለማግኘት ወይም ያለፈውን ለማካካስ ሳይሆን የቱሪስት እንቅስቃሴውን ለማነቃቃት ነው ልንጠቀምበት የሚገባው ባይ ናቸው።
ከታኅሣሥ 28 ጀምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የአገር ውስጥ እና የአገር ውጭ ሚዲያዎች በቦታው በመገኘት ዘገባ ይሠራሉ። ይህም በርካታ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚሠነዝሩትን የተዛባ አመለካከት እንዲያስተካክሉም ያግዛቸዋል ብለዋል።
የላሊበላ ከተማና ዙሪያውን ያለው ቀጠና ሠላማዊ በመሆኑ፣ የሚችል ኹሉ በቦታው ተገኝቶ በዓሉን በሠላም አክብሮ ይመለሳል ሲሉ ገልጸዋል።
በክልሉ ከገና በዓል በኋላ ጥምቀት እና ሌሎች የሚከበሩ በዓላት በመኖራቸው፣ ከውጭ የሚመጡ ኢትዮጵያውያንን ቆይታ የሚያራዝም ሲሆን፣ በዚህም በጦርነቱ ሳቢያ የተጎዳውን ማኅበረሰብ በኢኮኖሚ፣ በሥነ-ልቦና እንዲሁም በማኅበራዊ ሕይወቱ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳደር እንደሚረዳ ተመላክቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014



