በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ የተከሠተ የእሳት ቃጠሎ እየተባባሰ መሆኑ ተገለጸ

0
1594

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉትን፣ ለሊ ማርያም በተሰኘ ቦታ የእሳት ቃጠሎ መነሳቱን እና አሁን ላይ ቃጠሎው ይበልጥ እየተባባሰ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ከታኅሣሥ ወር ሦስተኛ ሳምንት ጀምሮ በአንገር ጉትን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ለሊ ማርያም ተብሎ በሚጠራው ቦታ የእሳት ቃጠሎ በመነሳቱ፣ በርካታ ቤቶችና ንብረቶች መቃጠላቸውን ነው አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ መረዳት የቻለችው።

በጊዳ አያና ወረዳ ያለው ሠላም የተረጋጋ ባለመሆኑ በቃጠሎው ምክንያት ምን ያህል ቤትና ንብረት እንደወደመ ትክክለኛውን ቁጥር ቀርቦ ማወቅ ባይቻልም፣ በርካታ ቤቶች፣ ንብረቶች የምግብ እህሎች እንደወደሙ ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ የቃጠሎው መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ የጠየቀች ሲሆን፣ የአካባቢው ሰዎችም መንስኤውን በሚከተለው መልኩ አብራርተዋል።

አሁን ካለንበት የታኅሣሥ ወር ጀምሮ አካባቢው የፀሐይ ቃጠሎ ስለሚበረታበትና ሳሩም ቅጠሉም ስለሚደርቅ የእሳት ቃጠሎ የመነሳት ዕድሉ ሠፊ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ሰሞኑን የተከሠተውን የእሳት ቃጠሎ ከእስካሁኑ የባሰ አውዳሚ የሚያደርገው በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች በመፈናቀላቸው ቃጠሎውን የሚከላከል ባለመኖሩ መሆኑን አብራርተዋል።

የአካባቢው አርሶ አደሮች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ ከሚያደርስባቸው ጥቃት ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከአካባቢያቸው በመፈናቀላቸው ሰብላቸውን መሰብሰብ እንዳለቻሉና ችግሩ በእንደዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ሰብሎቹ ሲደርቁ የበለጠ ቃጠሎውን ሊያባብሱት እንደሚችሉ ሲያሳስቡ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

በመሆኑም፣ በጊዳ አያና ወረዳ የኦነግ ሸኔ ተላላኪዎች ንጹኃንን በመግደል፣ ንብረትን በመዝረፍ፣ እንዲሁም የቀለብ እህል የሚያሸሹትን በማገት ከሚያደርሱት ጥቃት በተጨማሪ፣ የእሳት ቃጠሎው መነሳት የበለጠ ችግሮቹን እያባባሰ መምጣቱን ነው ነዋሪዎቹ ያብራሩት።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካካል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት ግለሰብ፣ በጊዳ አያና ወረዳ የእሳት ቃጠሎ በመከሰቱ ቁጥሩ በትክክል ያልታወቀ ቤትና ንብርት ወድሟል ሲሉ መስክረዋል። ግለሰቡ አያይዘውም፣ ከቃጠሎው በተጨማሪ በአካባቢው ኦነግ ሸኔ የሚሠዝረው ጥቃት ባለመቆሙ ‹‹ከባድ›› ጦርነት እንዳለና ሰዎች እየሞቱና እየቆሰሉ መሆኑን ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

የአካባቢው አርሶ አደሮች ሰብላቸውን ለመሰብሰብ ከታጣቂዎች ጋር ተደራጅተው ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም፣ ሰብላቸው ከመዘረፍ፣ ሕይወታቸውም አደጋ ላይ ከመውደቅ አላለፈም ሲሉ ነው በቦታው የተከሠተውን ችግር ነዋሪው ያብራሩት።
ግለሰቡ አክለውም፣ ሰብል ለመሰብሰብ ወጥተው ከነበሩት መካካል ዋለ ፈንቴ የተባሉት የጉትን ነዋሪ አርሶ አደር ኦነግ ሸኔ በከፈተባቸው ተኩስ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው አመላክተዋል።
ግለሰቡ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ የጸጥታ ችግሩ እየተባባሰ ያለው በጊዳ አያና ወረዳ ብቻ ሳይሆን በሀሮ ሊሙ ወረዳም ጭምር መሆኑን ነው።

ከአዲስ ማለዳ ምንጮች መካከል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት ሌላኛው ግለሰብ በበኩላቸው፣ በአንገር ጉትንና ሊሙ ወረዳ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እየወደቀ፣ ንብረት እየተዘረፈ፣ አካበቢያቸውን ለቀው የሚወጡ ሰዎች እየታገቱ መሆናቸው እና ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

መንግሥት ጩኸታችንን የማይሰማን እስከመቼ ድረስ ነው? ሲሉ የሚጠይቁት ነዋሪዎቹ፣ ከኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችና የህውሓት ተላላኪዎቻቸው፣ ከ‹‹የቤኒ ታጣቂዎች›› ጋር በመተባባር የግድያና የዘረፋ ጥቃት እያደረሱባቸው መሆኑን አመላክተው አፋጣኝ መፍትሔ እንዲቸራቸው አሳስበዋል።

አዲስ ማለዳ ከኹለት ሣምንት በፊት ባስነበበችው ዕትሟ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን አንገር ጉትን ከተማ ታኅሣሥ 11/2014፣ 60 በሚሆኑ የጋሪ በቅሎዎች ተጭኖ በመጓጓዝ ላይ የነበረ 400 ኩንታል የተፈናቃዮች እህል ‹‹አሮየ›› ከተማ ሲደርስ በኦነግ ሸኔ እንደተወረሰባቸው መዘገቧ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here