የቀድሞ የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሥራውን በአዲስ መልኩ ሊጀምር መሆኑን ገለጸ

0
990

በ2014 በተደረገው የመንግሥት ምሥረታ ወደ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት የተቀየረው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ እስካሁን ተቋርጦ የነበረውን ሥራውን በአዲስ መልኩ ሊጀምር መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
መጠሪያ ሥያሜው ወደ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት የተቀየረው ይኸው ተቋም አስቀድሞ ተጠሪነቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የነበረ ሲሆን፣ በአዲስ መልክ መዋቀሩን ተከትሎ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር መሆኑም ተመላክቷል።

በዚህ የለውጥ ሒደት መካከልም ኢንስቲትዩቱ በጀት እንዳያንቀሳቅስና ሥራውን እንዲያቆም ተደርጎ ቆይቷል። ነገር ግን ከታኅሣሥ 30/2014 ጀምሮ በጀቱን በማንቀሳቀስ የተቋረጠ ሥራውን እንደሚጀምር በቀድሞው ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የነበሩት ደበሌ ለማ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ሲሠጣቸው የነበሩ ሥልጠናዎችን፣ የ‹ላብራቶሪ› ሥራዎችንና ሌሎች ሲያከናውናቸው የነበሩ ኹሉንም ተግባራት ጨምሮ፣ ሙሉ ለሙሉ ሥራ አቁሞ መቆየቱን ደበሌ አክለው አብራርተዋል።
‹‹በጀት የማንቀሳቀስ ሥልጣን የላችሁም ተብለን ሥራችንን ስላቆምን እስከ አሁን ቁጭ ብለን ነው ደሞዛችንን ስንበላ የቆየነው›› ያሉት ደበሌ፣ ከታኅሣሥ 30/2014 በኋላ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችን በየሥራ መስካቸው መድቦ ሥራ እንደሚጀመር ነው የገለጹት።
በተያያዘም፣ ተቋሙ እስካሁን ሲያገለግልባቸው የነበሩ ሥልጣንና ተግባራት እንዳሉ ሆነው፣ ሌሎች ተጨማሪ የሥራ መስኮችና ኃላፊነቶች እንደተሠጠው የቀድሞ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

ደበሌ እንደሚሉት ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንስቲትዩት ተጠሪነቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በነበረበት ወቅት በዋናነት ሲሠራ የነበረው ሥጋ፣ ወተት፣ ማር፣ መኖ እና አሳን ለምርት ሒደት ማዘጋጀት (ፕሮሰሲንግ) እንደነበር የገለጹ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ደግሞ በተጨማሪ የምርት የማምረት (production) ሥራንም ይጨምራል።

ከእስካሁኑ ጋር ሲነጻጸር ተቋሙ አሁን የተሠጠው የሥራ ኃላፊነትና ሥልጣን ሠፊና አዲስ አቅጣጫ አለው የተባለ ሲሆን፣ በተያዘለት የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ወደ ሥራ ሲገባ በሥጋና ወተት ግብይት ጥራት ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ከወዲሁ ተስፋ ተጥሎበታል ተብሏል።
አዲስ ማለዳ የተቋሙ ሥራ አቋርጦ መቆየት በታኅሣሥ 29/2014 ከሚከበረው ገና በዓል ጋር በተያያዘ ከሥጋና ወተት አቅርቦት አንጻር ምን አይነት አሉታዊ ተጸዕኖ አለው ስትል የጠየቀች ሲሆን፣ የቀድሞው ዳይሬክተርም ቀደም ሲል ኢንስቲትዩቱ የማምረት ሥራ ላይ ተሳትፎ እንዳልነበረው በማውሳት፣ ለጊዜው ከበዓሉ ጋር በተያያዘ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ሚና እንደማይኖረው ገልጸዋል።

አይይዘው፣ በዓሉ ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው ከቁም እንስሳት አቅርቦት ጋር በተገናኘ የሚሠራው የግብርና ሚኒስቴር ነው ያሉ ሲሆን፣ ከአሁን በኋላ ግን ይህ የሥራ ድርሻ ሙሉ ለሙሉ በአዲስ መልክ ሥራውን የሚጀምረው ኢንስቲትዩቱ ኃላፊነት እንደሚሆን ነው ያመላከቱት።
ግብርና ሚኒስቴር ከታኅሣሥ 30/2014 ጀምሮ የአዲሱን መዋቅር ኃላፊዎች እንደሚመድብ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ኢንስቲትዩቱም በአንድ ወር ውስጥ በቀጥታ ወደ ሥራ ይገባል። ኢንስቲትዩቱም ከዚህ በኋላ ከእስካሁኑ በተለየ መልኩ የቁም እንሰሳት ዝርያ ማሻሻልና ቄራዎች ጋር በተያያዘ ሥራ ይሠራል ተብሏል።

በተቋሙ አሠራር ላይ አስቀድሞ ሲስተዋል የነበረው ዋናው ችግር የዝርያ ዕጥረት ነበር የሚሉት ደበሌ፣ አዲሱ ተቋም በሆለታ፣ በቢሾፍቱ፣ በቃሊቲና በሌሎች ማዕከላት የወተትና የሥጋ ዝርያ ማሻሻያ ስለሚደረግ፣ እስካሁን የነበረው ችግር ሊቀረፍ እንደሚችል ተናግረዋል።
የቀድሞ ኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በአዲስ መንግሥት ምሥረታ ምክንያት ሥራ ማቆሙን ተከትሎ በወተት ምርት ላይ የሚስተዋለውን የጥራትና የግብይት ችግር ለመፍታት የሚያስችል የአራት ዓመት ረቂቅ ዐዋጅ ሳያጸድቅ እንደቆየ አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here